1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለም በ2017

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 16 2010

ከኮሪያ ልሳነ ምድር እስከ ቅድስቲቱ ከተማ እየሩሳሌም፤ ከአፍቃኒስታን እስከ ኢራቅ፤ከሶሪያ እስከ ዩክሬን፤ከሊቢያ እስከ የመን  በግጭት፤ ግድያ የወደሙበት፤ በዉጊያ ቀረርቶ የተካለቡበት፤ምያንማር ላይ ዘር የማፅዳት ዘመቻ የተፋፋበት የጎርጎሪያኑ ዘንድሮ ዓምና ሊሆን ሳምንት ቀረዉ

https://p.dw.com/p/2pw34
USA UN Generalversamlung in New York Saal
ምስል dapd

ማኅደረ ዜና የጎርጎሮሳዊው 2017 አበይት ጉዳዮች

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአስር ዓመት መሪዉን በአዲስ የተካበት።ግን እንዳሮጌዉ ዘመን የዓለምን ሠላም የማስከበር ዓላማዉ የተሽመደመደበት፤በታሪኩ ብዙ ስደተኛ ለመቁጠር-የባተለበት ዓመት ነበር። የጎርጎሪያኑ 2017።ዩናይትድ ስቴትስ 1922ቷን ኢጣሊያን፤ አለያም 1933ቷን ጀርመንን እንዳትሆን ብዙ የተሰጋበት፤ ከቅርብ ወዳጆችዋ የተነጠለችበት ዓመት ነበር።ከኮሪያ ልሳነ ምድር እስከ ቅድስቲቱ ከተማ እየሩሳሌም፤ ከአፍቃኒስታን እስከ ኢራቅ፤ከሶሪያ እስከ ዩክሬን፤ከሊቢያ እስከ የመን  በግጭት፤ ግድያ የወደሙበት፤ በዉጊያ ቀረርቶ የተካለቡበት፤ምያንማር ላይ ዘር የማፅዳት ዘመቻ የተፋፋበት የጎርጎሪያኑ ዘንድሮ ዓምና ሊሆን ሳምንት ቀረዉ።ከአዉሮጳ እና አፍሪቃ በስተቀር በተቀረዉ ዓለም የተከናወኑ አበይት ፖለቲካዊ ሁነቶችን ላፍታ ዘክረን እንሸኘዉ።

ደቡብ ኮሪያዊዉ ዲፕሎማት ባን ጊ ሙን የጦርነትን ዘግናኝ ዉጤት ከመፀሐፍ፤ ከፊልም ወይም ከተራኪ ሳይሆን እንደ ሕፃን አድገዉበት ያዉቁታል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ዓላማ እና ዉለታ እንደ ወጣት ተጠቅመዉበት አይተዉታል።አረሱትምም።

                  

«የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልጅ ነኝ።ከኮሪያ ጦርነት በኋላ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እርዳታ ቀልቦናል።በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መፅሐፍት ተምረናል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ ትብብር ብቻችንን እንዳልሆንን አሳይቶናል።ለኔ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኃይል ረቂቅ አይደለም።የትምሕርት ጉዳይ አይደለም።»

Chile Zerstörung durch Erdbeben in  Los Vilos  Der Klimawandel schreckt auch Versicherer
ምስል picture alliance/dpa/A. Marinkovic

የዩናይትድ ስቴትሱ ፖለቲከኛ ባራክ ሁሴይን ኦባማ በቀለም፤በእምነት፤ ድሕነት ምክንያት መገፋትን አድገዉበታል።ባንጊሙን የትልቁን የዓለም ድርጅት ጠቅላይ ፀሐፊነት ሥልጣን በ2007፤ ኦባማ የዓለም ልዕለ ኃያሊቱን ሐገር የፕሬዝደትነት ሥልጣን በ2009 ሲይዙ፤ ለዓለም ሠላም መከበር እንደሚጥሩ፤ ዓለምን እንደሚያስተባብሩ ቃል ገብተዉ፤ ጥቂት ሞክረዉም ነበር።ዓለምም ልምድ፤ቃላቸዉን አምኖ ትልቅ ተስፋ አድርጎ ነበር።

ቃል ተስፋዉ በዓለም በናኘበት አመት ፤ ኦባማ እንደ ምርጥ የሠላም ተሟጋች የዓለምን ታላቅ የሠላም ሽልማት ኖቤል በተረከቡ ማግሥት ሊቢያ በኃያላኑ መንግሥታት ጦር ቦምብ፤ሚሳዬል ትወድም ገባች።ሶሪያ ተደገመች።ምሥራቃዊ ዩክሬን ትነድ ያዘች።ደቡብ ሱዳን ባንዲራ በሰቀለች ባመቱ ታንክ-መንድፍ ይፈቀፈቅባት ያዘ።የመን ከሠላማዊ ሕዝባዊ አመፅ አስተናጋጅነት ወደ ሕዝብ መርገፊያነት ተቀየረች።

ባንጊሙን አስር ዓመት የቆዩበትን ሥልጣን ሲያስረክቡም እሳቸዉ ያላደረጉትን ወይም ያልተሳካላቸዉን ተከታዮቻቸዉ እንዲያደርጉት መከሩ።

                            

«በትረ ሥልጣኑን ለዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ አስረክባለሁ።በሳል አስተሳሰብ፤ ጥልቅ ዕዉቀት እና መርሕ ሥላላቸዉ፤ በርካታ የተወሳሰቡ ፈተናዎችን በማለፍ ዓለም አቀፉን ድርጅት ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚያደርሱት እምነቴ የፀና ነዉ።

2017ም አንድ አለ።የተባበሩት መንግሥታትን ድርጅትን የዋና ፀሐፊነት ሥልጣን  የተረከቡት የፖርቱጋሉ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር መልዕክት በርግጥ ዘመኑ የሚጠይቀዉ ነበር።

                        

«ግጭቶች ከዚሕ ቀደም ከነበረዉ ይበልጥ ተወሳስበዋል።አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ጋር ተገናኝተዋል።የዓለም አቀፍ ሰብአዊ ሕጎች እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን አስከትለዋል። ለብዙ ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ  ቁጥር ያላቸዉ ሰዎች ከየቀያቸዉ ተፈናቅለዋል።አዲስ ሥጋትም ብቅ ብሏል።ዓለም አቀፍ አሸባሪነት።»

Irak - IS Islamischer Staat in Fallujah
ምስል picture alliance/AP Photo

የዓለም ትኩረት ግን ከኒዮርክ ይልቅ ዋሽግተን ላይ ነበር።አንዳዶች ዩናይትድ ስቴትስ የ1922ቷን ኢጣሊያን ወይም የ1933ቷን ጀርመንን ሆነች እያሉ መናገር፤መስጋት እና ማስጋታቸዉን እንደቀጠሉ ቢሊየነሩ ቱጃር፤ የቴሌቪዥን ዝግጅት አቅራቢዉ ሰዉዬ ፖለቲከኛ በሆኑ በሁለተኛ ዓመቱ የትልቂቱን ሐገር ትልቅ ሥልጣን ተረከቡ።ጥር 20።

                      

ዶናልድ ጆን ትራምፕ «አሜሪካ ትቅደም» ይሉ ገቡ።በማግሥቱ የትራምፕ መፈክር፤ መርሕ እና ንግግር ያስጋ፤ ያስቆጣ-ያስፈራዉ ሕዝብ የዓለም አደባባዮችን በተቃዉሞ ሰልፍ አጥለቀለቀዉ።ጥር 21።

                       

የሴቶች ሠልፍ ተብሎ በሚጠራዉ ሰልፍ ዕለት በመላዉ ዓለም አደባባይ የወጣዉ ሕዝብ ከ2 ሚሊዮን በላይ ተገምቷል። በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ በአንድ ቀን በርካታ ሕዝብ አደባባይ ሲወጣ የዚያን ቀኑ የመጀመሪያዉ ነዉ።ርዕሠ-ከተማ ዋሽግተን ብቻ ከ500 000ሺሕ በላይ ሕዝብ  ተሰልፏል።

የሰልፎኞቹ ጥያቄ እና ቁጣ ለትራምፕ ከ«ጫጫታ» ያለፈ አልነበረም።አሜሪካን ለማስቀደም የሰባት የሙስሊም ሐገራት ዜጎች አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያግደዉን የመጀመሪያዉን ደንብ ፈረሙ።ደንቡ በፍርድ ቤት ሲወድቅ፤ እንደገና ሲፈረም፤ እንደገና ሲወድቅ፤ እንደገና ሲፈረም፤የመጨረሻዉ ፀደቀ።ሕዳር።

ለትራምፕ የመጀመሪያዉ ጠንካራ ፈተና የተሰማዉ ከኮሪያ ልሳነ ምድር ነዉ።ሰሜን ኮሪያ የሩቅ ርቀርት ተምዘግዛጊ ሚሳዬል አወነጨፈች።የካቲት 11።ዶናልድ ትራምፕ ዛቱ።ሰሜን ኮሪያ የሚሳዬል እና የሐይድሮጂን ቦምብ ሙከራዋን እንደቀጠለች፤ ዩናይትድ ስቴትስ እንደፎከረች፤ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን እንደተሸማቀቁ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰሜን ኮሪያን በማዕቀብ እንደቀጣ ዓመቱ ነገደ።

Jemen Ali Abdullah Saleh und George W. Bush 2007
ምስል Reuters/K. Lamarque

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ዓመቱ መጀመሪያ ላይ እንደተፈራዉ በ1922 የሮምን፤ በ1933 የበርሊንን አብያተ መንግሥታት እንደተቆጣጠሩት መሪዎች አልሆኑም።ነሐሴ መጀመሪያ ላይ ያሰሙት ዛቻ ግን፤ ሔሮሺማን እና ናጋሳኪን በአዉቶሚክ ቦምብ ያንጨረጨሩትን የሐሪ ኤስ ትሩማንን አይነት ነበር።

                                 

«ሰሜን ኮሪያ ዩናይትድ ስቴትስን ማስፈራራቷን ብታቆም ይሻላታል።ዓለም ከዚሕ ቀደም አይቶት የማያዉቀዉ እሳት እና መዓት ይወርድባቸዋል።»

ትራምፕ እና የሰሜን ኮሪያዉ መሪ እንደ ሐገር መሪ ሳይሆን እንደ መሸተኛ «አንተ-አንቺ» ተባብለዋል።ሰሜን ኮሪያ 16 ሚሳዬሎች እና ሁለት የኑክሌር ቦምቦች ሞክራለች።ዩናይትድ ስቴትስ በርካታ ጦር እና የጦር መሳሪያ ወደ ኮሪያ ልሳነ ምድር አዝምታለች።

ፈርጣማ ጡንቻዋን የፈተሸችዉ ግን ሰሜን ኮሪያ ላይ ሳይሆን ወትሮም በወደመችዉ ሶሪያ ላይ ነበር።ሚያዚያ 6፤ ባንድ ለሊት አንድ የሶሪያ አዉሮፕላንን ማረፊያን በ59 ቶም ሐዋክ ክሩዝ ሚሳዬል ቀጠቀጠች።ምክንያት የሶሪያ መንግሥት ጦር ኬሚካዊ ጦር መሳሪያ ተኩሷል የሚል ነበር።ሩሲያ ጥቃቱን «ወረራ» በማለት አዉግዛዋለች።

ሁለተኛዉ የአሜሪካ ጠንካራ ዱላ ያረፈዉ ከ2001 አንድ ጀምሮ የአሜሪካ ጦር በሚያዳሽቃት አፍቃኒስታን ላይ ነበር።ሚያዚያ 13።ISIS በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ አሸባሪ ድርጅት መሽጎበታል የተባለዉን የናንጋርሐር አካባቢ GBU-43/B MOAB በተባለዉ ቦምብ ጋየ።ዓለም ከኑክሌር ቦምብ በስተቀር ናንጋርሐር ላይ የወረደዉን ዓይነት ትልቅ ቦምብ አያዉቅም።

ዓለም ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወዲሕ በርካታ ሕዝብ የተሰደደ እና የተፈናቀለባት ዘንድሮ ነዉ።ወደ ስልሳ ሚሊዮን ገደማ።በርካታ ሕዝብ የተራበዉም ዘንድሮ ነዉ።20 ሚሊዮን።የመን፤ ደቡብ ሱዳን፤ ናጄሪያ የመጀመሪያዉን ሥፍራ ይይዛሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘንድሮ አዲስ ዋና ፀሐፊ ብቻ አይደለም የተመረጠለት።የድርጅቱ ጤና ክፍልም አዲስ መሪ መርጧል።ኢትዮጵያዊዉ ፖለቲከኛ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሐኖም ከጠንካራ ፉክክር በኋላ የዓለም ጤና ድርጅት የበላይ ኃላፊ ሆነዉ ተመረጡ።ግንቦት 23።

                                

ዶክተር ቴዎድሮስ የአለም አቀፉን የጤና ድርጅት ከፍተኛ ሥልጣን በመያዝ የመጀመሪያዉ ኢትዮጵያዊ፤ የመጀመሪያዉ አፍሪቃዊም ናቸዉ።

በ2016 የዓለም የሙቀት መጠን ከመቼዉም ጊዜ በላይ መጨመሩን NASA እና NOAA የተባሉ ሁለት የዩናይትድ ስቴትስ የጠፈረ እና የከባቢ አየር ጥናት ተቋማት ጥር 2017 አስታዉቀዉ ነበር።በስድስተኛ ወሩ ሰኔ ዩናይትድ ስቴትስ የዓለምን የሙቀት መጠን ለመቀነስ ካለመዉ ከፓሪሱ ስምምነት እንደምትወጣ አስታወቀች።

Irak - Mossul - IS
ምስል Getty Images/AFP/A. Al-Rubaye

የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ሊዮንደን ጆንሰን ምዕራብ  አዉሮጳን ሙሉበሙሉ የአሜሪካ ታዛዥ ለማድረግ መሞከራቸዉን የያኔዉን የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ሻርልስ ደጎልን ያክል በግልፅ የተቃወመ አልነበረም።ደጎል የያኔዎቹን የዋሽግተንና የለንደን መሪዎች ሴራ በመቃወም ፈረንሳይ ከሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ወታደራዊ ትብብብር እንድትወጣ ወሰኑ።ሰኔ 21 1966።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽና የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሕግን ጥሰዉ፤ የዓለም ሕዝብ እና መንግስታትን ተቃዉሞ ንቀዉ፤ የሐሰት ፊልምና ፎቶ መረጃ ብለዉ ኢራቅን  በ2003 ሲወሩ ወረራዉን አጥብቀዉ ከተቃወሙ የአሜሪካ ወዳጅ ሐገራት መሪዎች ግንባር ቀደሙ የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ዣክ ሺራክ ነበሩ።

አሜሪካ ከዓለም አቀፉ የተፈጥሮ ጥበቃ ዉል መዉጣትዋን ድፍን ዓለም ተቃዉመዎታል።የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በርግጥ ደጎልን ወይም ሺራክን አይደሉም።አሜሪካንን በመቃወም ግን የቀዳሚዎቻቸዉን ታሪካ ደገሙት።

                              

«ፈረንሳይ ትግሏን እንደማታቆም አረጋግጥላችኋለሁ።የፓሪሱ ስምምነት ጨርሶ አይታጠፍም።ገቢራዊ ይሆናል።በፈረንሳይ ብቻ ሳይሆን በተቀሩት መንግስታት በሙሉ ሥራ ላይ ይወላል።»

በርግጥም ትራምፕ አሜሪካን ከዓለም ነጠሉ እንጂ የፓሪሱ ዉል አልፈረሰም።ሕዳር፤ እዚሕ ቦን በተደረገዉ ጉባኤም ዓለም ይሕንኑ አረጋግጧል።

ሰኔ ሰባት።ሽብር ጦርነት በሚነዉጠዉ መካከለኛዉ ምሥራቅ ከአደጋ ትርምሱ ገለል ብላ የኖረችዉ ኢራን ተሸበረች።እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግስት (ISIS) ብሎ የሚጠራዉ ቡድን አባላት ናቸዉ የተባሉ ሁለት አሸባሪዎች በኢራን ምክር ቤት ሕንፃ እና በቀድሞዉ የሐገሪቱ መሪ በአያቱላሕ ሆሚኒ ቀብር ላይ በከፈቱት ጥቃት 17 ሰዉ ገደሉ።43 አቆሰሉ።የኢራን ጦር ሶሪያ የሚገኘዉን የISIS ምሽግን በሚሳዬል ደብድቦ ጥቃቱን ተበቀለ።ሰኔ 18።

Frankreich Klimagipfel in Paris - Präsident Emmanuel Macron
ምስል Getty ImagesAFP/P. Wojazer

ሰኔ 21፤ ሳዑዲ አረቢያ የምትመራቸዉ የአረብ ተባባሪ ሐገራት ለሰወስተኛ ዓመት የሚደድቧት የመንን ከቦምብ፤ሚሳዬል ጥይት የተረፈው ሕዝቧ በኮሌራ እያለቀ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት የጤና ድርጅት አስታወቀ።

ዩናይትድ ስቴትስ መራሹ ጦር በ2003 ከወረራት ወዲሕ የእልቂት፤ዉድመት፤የሽብር ጥፋት ምድር የሆነችዉ ኢራቅ ከዉድመት ጥፋቷ አንዱ የሆነዉን ጦርነት ድል አደረገች።ከዩናይትድ ስቴትስ እስከ ኢራን፤ ከአዉሮጳ እስከ አረብ ሐገራት በተሳተፉበት ጦርነት ሞሱል ላይ ድል አደረጉ።የኢራቅ እና የተባባሪዎችዋ ሐገራት ጦር የሐገሪቱን ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ከISIS እጅ ማረከ።ኃምሌ 10።ታሕሳስ 9ኝ ላይ ኢራቅ መንግስት ጦር ISIS ይቆጣጠራቸዉ የነበሩ አካባቢዎችን በሙሉ መማረኩን አስታወቀ።

ነሐሴ ለምያንማር ሙስሊሞች የምድር ገሐነም በር የተከፈተበት ወር ነበር።የርዳታ ድርጅቶች እንዳመለከቱት የምያንማር ጦር በከፈተዉ ዘመቻ ባንድ ወር ጊዜ ዉስጥ ብቻ ከ6700 በላይ ሙስሊሞችን ገድሏል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ አቁስሏል።ሴቶችን ደፍሯል። ከነሐሴ በኋላ ብቻ ከስድስት መቶ ሺሕ በላይ ሮሒንጂያዎች ወደ ባንግላዴሽ ተሰደዋል።

መስከረም ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽን ጋዜጠኛዉ ጠየቀ።«በሮሒንጂላይ የሚፈፀመዉ  ግድያ እና ግፍ፤  ዘር የማፅዳት ዘመቻ ነዉ ብለዉ ያምናሉ» ብሎ። የዋና ፀሐፊዉ መልስ፤ «ጥያቄሕን በሌላ ጥያቄ ልመልሰዉ።ከአጠቃላዩ የሮሂንጂያ ሕዝብ አንድ ሰወስተኛዉ ከሐገሩ ሸሽቶ---ጥፋቱን ለመግለፅ ከዚሕ የተሻለ ቃል ታገኛለሕ።» የሚል ነበር።

ዓለም ብዙ አወራ።አወገዘ።እልቂት ስደት፤ግፉን ለማስቆም  ግን የወሰደዉ እርምጃ ሳይኖር አዲስ አስከሬን እና ስደተኛ ለመቁጠር አዲስ ዓመት ሊል ሳምንት ቀረዉ።

ዩናይትድ ስቴትስ እና የካረቢክ አካባቢ ሐገራት የአዉሎንፋስ፤የወጀቦ እና ጎርፍ ማአት እንደወረደባቸዉ ነሐሴና መስከረም ተሰናበቱ።አደጋዉ ወደ ሰባት መቶ ሰዉ ገድሏል።ከሰወስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የተገመተ ሐብት እና ንብረት አዉድሟል።መስከረም የዩናይትድ ስቴትስና የሩሲያ ጠብ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት ወርም ነበር።መስከረም 1 ሩሲያ፤ 755 የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን አባረረች።

ኢራን እንደ አሜሪካ፤ እንደ እስራኤልና ሳዑዲ አረቢያ ሁሉ ተፈጥሮም ጨከን ብሎባት ነበር።ከኢራቅ ጋር የሚጎራበት ግዛትዋን የመታዉ የመሬት መንቀጥቀጥ 530 ሰዉ ገደለ።ሕዳር 12።

የዩናይትድ ስቴትሱን ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ግንቦት ማብቂያ ሪያድን መጎብኘታቸዉ በነዳጅ ዘይት ሐብት ለሚቀማጠሉት ለሳዑዲ አረቢያ ነገስታት የልብ ልብ ነዉ የሰጠዉ።ትራምፕ ሪያድን በጎበኙ በሰወስተኛ ወሩ የሪያድ ገዢዎች፤ታማኞቻቸዉን አስከትለዉ ትንሺቱ ጎረቤታቸዉ ቀጠር ላይ የአየር፤ የየብስና የባሕር መስመራቸዉን ዘጉ።ማዕቀብ ጣሉም።ኢራንን ማዉገዛቸዉን አጠናከሩ።የመንን ማጥፋታቸዉን ቀጠሉ።

Den Haag Schlusszeremonie des UN-Kriegsverbrechertribunals für Ex-Jugoslawien | UN-GeneralSekretär Antonio Guterres
ምስል Reuters/United Photos/T. Kluiters

የየመኑ ጦርነት  የሐገሪቱን ሕዝብ ከመፍጀት በተጨማሪ፤ ዳፋዉ ለሐገሪቱ ሰላሳ ዓመት ገዢ ሕይወትም ነዉ የተረፈዉ።የቀድሞዉ የሐገሪቱ ፕሬዝደንት ዓሊ አብደላ ሳሌሕ ሁቲዎችን ከድተዉ ለሳዑዲ አረቢያ በማደራቸዉ ተገደሉ።ታሕሳስ 4።

ሕዳር አራት። ሳዑዲ አረቢያ የሐገሪቱን ልዑላን፤ ሚኒስትሮች እና  ቢሊየነሮችን በሙስና ጠርጥረናቸዋል ብለዉ አሰሩ።እስካሁን የታሰሩት ከ200 በልጠዋል።አንዱ ኢትዮጵያ ዉስጥ በርካታ ኩባንዮች ያሏቸዉ ሼኽ መሐመድ ሁሴይን አል አሙዲን ናቸዉ።

ታሕሳስ ስድስት።ዋሽግተን።«ስለዚሕ እየሩሳሌም እንደ እስራኤል ዋና ከተማነት በይፋ እዉቅና ለመስጠት ጊዜዉ አሁን መሆኑን ወስኛለሁ።»

እስራኤል ተደሰተች።ዛሬ ደግሞ ጓቲማለ መደገፏን አስታወቀች።አብዛኞቹ የዓለም መንግሥታት አወገዙት።የተቀሩት ተቃወሙት።የሙስሊምና የክርቲያን ኃይማኖት መሪዎች ኮነኑት።ፍልስጤሞች ሰባ ዓመት የዘለቀ ትግላቸዉን በአደባባይ ሰልፍ ቀጠሉ።እንደ አያት፤ ቅድመ አያቶቻቸዉ ይገደሉ፤ በጢስ ጠለስ ይታፈኑ ገቡ።

ዘመኑን በጎርጎሪያኑ  ቀመር የሚያሰላዉ ዓለም ለገና በዓል ሲታደም ፊሊፒንስ ሐዘን ተቀመጠች።እስያቱን ሐገር ያጥለቀለዉ ጎርፍ ከሁለት መቶ በላይ ሰዉ ገደለ።ከ10 ሺሕ በላይ አፈናቀለ።ዘመኑ ግን በዘመን ሊተካ ጉዞዉ ቀጠለ።መልካም በዓል።መልካም አዲስ ዓመት።

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ