1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግብፅ አብዮት ድል-2ኛ ዓመትና ፈተናዉ

ሰኞ፣ የካቲት 4 2005

የሶሪያዉ ሕዝባዊ አመፅ-ባፍታ ወደ ነፍጥ ዉጊያ ተቀይሯል።የየመንና፥ የሊቢያ ሕዝባዊ አመፅም አፈፀፃሙ-እንዳጀማመሩ አይደለም።የሁሉም የሕዝባዊ አመፅ መነሻ በርግጥ ቱኒዚያ ናት።አብነቱ ግን የግብፆች።ለሌሎቹ አብነታዊዉ ሕዝባዊ አብዮት ዛሬም በሁለተኛ ዓመቱ የሕዝቡን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ አለመመለሱ እንጂ ድቀቱ

https://p.dw.com/p/17cM4
Protesters gather at Tahrir square in Cairo November 23, 2012. Angry youths hurled rocks at security forces and burned a police truck as thousands gathered in central Cairo to protest at Egyptian President Mohamed Mursi's decision to grab sweeping new powers. Police fired tear gas near Tahrir Square, heart of the 2011 uprising that toppled Hosni Mubarak at the height of the Arab Spring. Thousands demanded that Mursi should quit and accused him of launching a "coup". REUTERS/Mohamed Abd El Ghany (EGYPT - Tags: POLITICS CIVIL UNREST)
ተሕሪር አደባባይ-ፀረ ሙባረክ ተቃዉሞምስል Reuters



የግብፅ ሕዝባዊ አብዮት የፕሬዝዳት ሆስኒ ሙባረክን የሠላሳ ዘመን አምባገነናዊ አገዛዝ ካስወገደ እነሆ ዛሬ-ሁለተኛ አመቱን ደፈነ።የጥንታዊቱ፥ የሥልታዊቱ፥ የጠንካራዊቱ ሐገር ጀግና ሕዝብ አብዮት ከግብ መድረስ አለመድረሱ ግን ዛሬም አጠያያቂ ነዉ።ሙባረክ ሥልጣን የለቀቁበት ሁለተኛ ዓመት መነሻ፥ የአብዮቱ ሒደትና ዉጤት ማጣቃሻ፥ እንድምታዉ መድረሻችን ነዉ ።

የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቬለ በቅርቡ እንዳሉት ካይሮ ላይ የሚደረግ የሚሆነዉ የድፍን መካከለኛዉ ምሥራቅን ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ፣ ወታደራዊና ማሕበራዊ ጉዞን ባይወስን መጫኑ አይቀርም።«ግብፆች ለኛ ትርጉም ያላት ወዳጅ ሐገር ናት።ከዚሕም በተጨማሪ ግብፅ በአረቡ ዓለም የተቀጣጠለዉ አብዮት እንዲሳካ ቁልፍ ሐገርም ናት።»

ያቺ ሐገር ጥንት-ድሮ በመሐሉም ከዛሬ በላይ ለብዙዉ ዓለም በብዙ ምክንያት እጅግ ጠቃሚ፥ አስፈላጊ አሻሚም ነበረች።በጣም በራቀዉ ዘመን አዉሬ አድኖ፣ የመመገብ ብልጠትን የነ ሉሲ የልጅ ልጆች ከዛሬዋ ኢትዮጵያ ወይም ሌላ ሥፍራ አዉቀዉት፣ ጀምረዉት ይሆን ይሆናል።

አሳ ማስገርን ለዓለም ያሳወቁት ግን አባይ ግራና ቀኝ ሠፍረዉ የነበሩት የዛሬዋ ግብፅ ጥንታዊ ነዋሪዎች ናቸዉ።ከክርስቶስ ልደት በፊት በአስረኛዉ ዓመአት ቅጠል፣ ጥራጥሬን ወቅጦ ወይም ፈጭቶ መመገብ እንደሚቻል በተቀረዉ ዓለም ለሚኖረዉ ሰዉ ያሳዩትም እነሱዉ ነበሩ።

ከስድስት ሺሕ ዓመተ-ዓለም ጀምሮ ኒሎቲኮች፣ ባዳሪያዎች፣ናቃዳዎች፣ ሜናሶች፣ ፈርኦኖች፣ ግሪኮች፣ ሮሞች፣ ፋርሶች፣ አረቦች፣ ቱርኮች፣ አዉሮጶች የሰዉ ልጅን አሰለጠኑም-አሰየጠኑም፣ አይሁዶች፣ ክርስቲያኖች፣ ሙስሊሞች ሐይማኖትን-አስተማሩም-አስመረሩም ግብፅ አንድም መነሻ፣ ሁለትም መረማማጃ፥ ሰወስትም መድረሻቸዉ ነበረች።


የዘመነ-ዘመናት ሥልጣኔ፣ የፅሁፍ፣ የሕንፃ፣ የሕክምና፣ የጦር እዉቀት፣ የእምነት ሐይማኖት አስተምሕሮት በየቤተ-መዘክሩ፣ በየቤተ-ዕመነቱ፣ የታጨቀ፣ በየፒራሚድ-ሐዉልቱ እየተጠናቀረ-የሐገር ጎብኚ አጥኚዎችን ከመማረክ ባለፍ የዛሬዋን ግብፅ ትልቅነት ለዛሬዉ ዓለም ብዙም የሚጠቁም አይደለም።

ለዘመኑ-አብዛኛዉ ግብፃዊዉ የሐገሩ ጥንታዊ ሥልጣኔ-እድገት ምጥቀት ከታሪክ መዘክርነት ባለፍ የምጣኔ ሐብት ችግሩን፥ የፖለቲካ፥ የእምነት፥ ሥራ የማግኘት ነፃነቱን ለማስከበር የተከረዉ ብዙም የለም።የያኔዉ ሃያ-ሰወስት ዓመት ወጣት ኢብራሒም ኬንደሪያ ደግሞ እንደ ብዙ የዕድሜ አቻዎቹ ሁሉ ከሙባራክ ሌላ-የሚያወቀዉ መሪ፥ ከሙባረክ ጨቋኝ ሥርዓት ባለፍ ያየዉ ሥርዓት አልነበረም።

በብዙ ነገር ብዙዉን ዓለም የቀደመችዉን ግብፅ ጨካኝ ገዢዎችን በማስወገዱ ሕዝባዊ ሠላማዊ ትግል በርግጥ በቱኒዚያ ተቀድማለች።ግን ግብፆች ፈጥነዉ ቱኒዞችን ተከተሉ።የአሌክሳንደሪያዉ ወጣት ኢብራሒም ኬንደሪያ የቱኒዚያ ወጣቶችን ፈለግ ቀድሞዉ ተከትለዉ አደባባይ ከወጡት አዕላፍ ወጣት ግብፃዉያን አንዱ ነበር።

ከፕሬዝዳት ሆስኒ ሙባረክ ታማኝ ሚሊሺያዎች፥ከሰላዮችና ከፀጥታ አስከባሪዎች የገጠማቸዉ አፀፋ ግን ኢብራሒም አሁን እንደሚተርከዉ ቀላል አልነበረም።

«ፖሊሶች ሁሉንም ነገር ፈፅመዉብናል።የፕላስቲክ ጥይት፥ እዉነተኛም ጥይት ተኩሰዉብናል። በአስለቃሽ ጢስ አጥነዉናል።ተቃዋሚ ሠልፈኛዉን በመኪና ደፍልቀዋል---»

እያለ ቀጠለ ኢብራሂም።ያም ሆኖ እስከ ጥር-ሃያ ስምንት ሁለት ሺሕ አስራ-አንድ ድረስ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከአሌክሳንደሪያ አደባባይ ተለይቶ አያዉቅም።

እስከዚያች ዕለት ድረስ ጓደኞቹን እያፈኑ-ሲወስዱ፥ ላጭር ጊዜ እያሰሩ የለቀቁት፥ ሌሎቹን ሲገድሉ እየደበደቡ የተዉት የሙባረክ ታማኝ ሰላዮች አንድ ቀን እስከ መጨረሻዉ እንደሚያስሩት ወይም እንደሚገድሉት መጠርጠሩ አልቀረም።ግን ትንሽ ጊዜ ቆይቶ፥ የጀመረዉን ሕዝባዊ ትግል ሒደት ላጭር ጊዜም ቢሆን ለመቀጠል ይሕ ቢቀር ሲቀጥል ለማየት ወደ ካይሮ ተሰደደ።

አንድም ቀን ያልተለየዉን ያደባባይ ሠልፍ አቋርጦ፣ ወላጅ፣ ወዳጅ፣ ዘመድ ጓደኞችን ተለይቶ ወደ ካይሮ የተሰደደዉ ሕይወቱን ላጭር ጊዜም ቢሆን ለማትረፍ እንጂ የዚያን ቀን ካይሮ ቤተ-መንግሥት የሆነዉ-እንዲሕ ባጭር ጊዜ ይሆናል ብሎ አስቦ፥ የሆነዉን፣ እዚያዉ ካይሮ ሆኜ እሰማለሁ፣ ተሕሪር አደባባይ ላይ እቦርቃለሁ ብሎም አልበረም።ጥር 11.2011 ማታ።

«የተከበራችሁ ዜጎች ሆይ፥ ሐገራችን በገጠማት ፈተና ምክንያት፥ ፕሬዝዳት ሆስኒ ሙባረክ የሪፐብሊኪቱን የመሪነት ሥልጣን ለመልቀቅ ወስነዋል።»

ምክትል ፕሬዝዳት ዑመር ሱለይማን።የማይሆን የሚመስለዉ ሆነ።የሰላሳ ዘመኑ ሥርዓት ተገነደሰ። የፈርዕኖቹ አብነት፥ ጠንካራዉ ገዢ፥ እንደ ፓይለት በተደነቁበት፥ እንዳዋጊ በተሞገሱበት፥ እንደ ጠንካራ መሪ በተወደሱ፥ በተፈሩበት፥ ሐገር ሥልጣንን ሙጥኝ በማለታቸዉ ተጠልተዉ፥ በጨካኝ እርምጃቸዉ ተወግዘዉ፥ ተዋርደዉ፥ ከሚወዱት ሥልጣን ተወገዱ።ተሕሪር አደባባይ ፌስታ።

ድሮና-ዘንድሮ።

ከ1948 ጀምሮ በተደጋጋሚ የተደረገዉ የእስራልና የአረቦች ዉጊያ በእስራኤል አሸናፊነት አብቅቷል።ዉጊያዉ እንጂ ጦርነቱ ግን ዛሬም አላባራም።የአበቃዉ ዉጊያም ሆነ ያላበቃዉ ጦርነት ዋና ማዕከል ግብፅ ናት።

ብርጌድየር ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ የመሩት መፈንቅለ መንግሥት በርግጥ ከሽፏል።

ከጄኔራል ፈዉዚ ሱል፣ እስከ ጄኔራል ሐፊዝ አል-አሰድ የደማስቆን፣ ከጄኔራል አብድል ከሪም ቃሲም እስከ ሳዳም ሁሴይን የባግዳድን፣ ጄኔራል ጀአፈር አል-ኑሜሪ የካርቱም፣ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ የትሪፖሊን፣ ጄኔራል አብዱላሒ አል-ሰላል-የሰነዓን፣ ጄኔራል ዚያድ ባሬ የሞቃዲሾን አብያተ-መንግሥታትን መቆጣጠራቸዉ በየዘመኑ የየሐገራቸዉን የዓለምንም ሠላም፣ ደሕንነት፣ እድገት ብልፅግና መጉዳት መጥቀሙ ብዙ ያከራክር ይሆናል።

የጦር መኮንኖቹ በሙሉ ሥልጣን የያዙት ግን ከነሱ በፊት የነበሩትን የየሐገራቸዉን መሪዎች በመፈንቅለ መንግሥት እያስወገዱ ነበር።የሁሉም ምሳሌ ደግሞ ጀኔራል መሐመድ ነጉይብን አስቀድመዉ፣የፋሩቅን ዘዉዳዊ ሥርዓት አስወግደዉ ሥልጣን የያዙት ኮሎኔል ገማል አብድናስር ነበሩ።

እነ ኢብራሒም ከታሪክ በሚያዉቁት የአያት-ቅድመ አያቶቻቸዉ ታሪክ ይኮሩ፥ ያፍሩ፥ ይደሰቱ-ያዝኑም ይሆን-ይሆናል።አንድ ሐቅ-ግን ግልፅ ነዉ።የታሪካዊቷ ሐገር ወጣቶች እነሱም በዘመናቸዉ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ያኔ-እንዳሉት ታሪክ ሠሩ።

«ፍፁም ግልፅ የሆዉ ምንድነዉ፥-ታሪክ ሲሰራ እያየን ነዉ።»

በርግጥም እንድምታዉ ብዙዉን አምባገነን ያርበደበደ ታላቅ ታሪክ።ከሞሮኮ እስከ ሳዑዲ አረቢያ፥ ከዮርዳኖስ- እስከ ኦማን፥ ከባሕሬን፥ እስከ ኩዌት የሚገኙ ነገስታት በየሐገራቸዉ የተቀጣጠለዉን ሕዝባዊ አብዮት በምዕራባዉያን ፍቃድና ድጋፍ ማዳፈናቸዉ ግልፅ ነዉ።የአልጄሪያ ገዢዎችም እንዲሁ።

የሶሪያዉ ሕዝባዊ አመፅ-ባፍታ ወደ ነፍጥ ዉጊያ ተቀይሯል።እኒያ የየሐገራቸዉን ሕዝብ ጥያቄ በሐይል የደፈለቁት የአረብ ነገስታትን እጃቸዉን የዶሉበት፥ ከዋሽግተን እስከ ቴሌ አቪቭ፥ ድፍን ምዕራባዉያን የሚሳተፉበት፥ ሞስኮ ቤጂንጎች፥ ከዋሽግተን-ብራስልሶች ጋር የተቃረኑበት የሶሪያ ዉጊያ ወዴት እንደሚያመራ አለየም።

የየመንና፥ የሊቢያ ሕዝባዊ አመፅም አፈፀፃሙ-እንዳጀማመሩ አይደለም።የሁሉም የሕዝባዊ አመፅ መነሻ በርግጥ ቱኒዚያ ናት።አብነቱ ግን የግብፆች።ለሌሎቹ አብነታዊዉ ሕዝባዊ አብዮት ዛሬም በሁለተኛ ዓመቱ የሕዝቡን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ አለመመለሱ እንጂ ድቀቱ።የያኔዉ ምክትል ፕሬዝዳት የዑመር ሱሌይማን የዚያን ቀን ምሽት ያሰሙት አዋጅ-ለተቃዋሞ ሠልፈኛዉ ከድል ብሥራትነቱ እኩል የእስከ ዛሬ ምናልባትም የከእንግዲሁንም ሒደት ፈተናዎችን ጠቋሚ ብጤ ነበር።

«የጦር ሐይሎች ጠቅላይ ምክር ቤት ሐገሪቱን የመምራት ሥልጣኑን ይይዛል።»

የጦር ጄኔራሎቹ የመሪነቱን ሥልጣን ሲሆን እንደያዙ ለመቀጠል፥ ይሕ ቢቀር ለታማኛቸዉ ለማስረከብ ያልሸረቡት ሴራ አልነበረም።እቅድ፥ እርምጃቸዉን በመቃወም አደባባይ የሚወጣዉን ሕዝብ ጥያቄ ለማፈን በተደጋጋሚ ሞክረዋል።በሺ የሚቆጠሩ ወጣቶችን አስገድለዋል።እነ ኢብራሒምን አሳስረዋል።አስገርፈዋልም።

«ወታደሮቹ ጠመንጃ ደገኑብን።በተደጋጋሚ ደበደቡን።መጨረሻ ላይ እራሴን ሳትኩ።ሌሎች መጥተዉ እንደገና እንደሚገርፉን፥ እንደሚገድሉን ሲዝቱ አቅሌን ገዛሁ።»

ያም ሆኖ ጦር ሐይሉ ለሕዝቡ ጥያቄ መበርከክ ግድ ነበረበት።በዓመት ከመንፈቅ እድሜ የግብፆች አብዮት ሌላ ድል አስመዘገበ።የግብፅ ሕዝብ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ መሪዉን በነፃነት መምረጡ ለታሪካዊቷ ሐገር ሌላ ታላቅ፥ በጎ ታሪክ መሆኑ አላነጋገረም።

ባለፈዉ ሐምሌ በተደረገዉ ምርጫ ሥልጣን የያዙት መሐመድ ሙርሲና የቀድሞ ፓርቲያቸዉ ሙስሊም ወድማማቾች በተለይ የሸሪዓ ሕግጋት ተቀይጠዉበታል የሚባለዉን ሕገ-መንግሥት ማፀደቃቸዉ ግን የሌላ ቅሬታ፥ ተቃዉሞ፥ የአመፅ፥ ግጭት-ግድያ ሰበብ-ምክንያት ሆኗል።ተሕሪር አደባባይም የሌላ ሕዝባዊ ትግል-አዉድ እንደሆነ ነዉ።

ግብፅ፥ ታሪካዊት ሐገር።የጀግና ወጣቶች ምድር።ግን ያልተቋጨ አብዮት መዘዉር።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

Protesters gather at Tahrir square in Cairo November 23, 2012. Angry youths hurled rocks at security forces and burned a police truck as thousands gathered in central Cairo to protest at Egyptian President Mohamed Mursi's decision to grab sweeping new powers. Police fired tear gas near Tahrir Square, heart of the 2011 uprising that toppled Hosni Mubarak at the height of the Arab Spring. Thousands demanded that Mursi should quit and accused him of launching a "coup". REUTERS/Mohamed Abd El Ghany (EGYPT - Tags: POLITICS CIVIL UNREST)
ተሕሪር አደባባይ-ፀረ ሙርሲምስል Reuters
Egypt's new President Mohamed Mursi is pictured before his speech at Cairo University June 30, 2012. Mursi said on Saturday the military that took charge when Hosni Mubarak was overthrown last year had kept its promise to hand over power, speaking at a ceremony to mark the formal transfer of authority. REUTERS/Stringer (EGYPT - Tags: POLITICS ELECTIONS)
ሙርሲምስል Reuters
In this photo released by Middle East News Agency, former Defense Minister Hussein Tantawi, left, receives a high medal from Egyptian President Mohammed Morsi at the Presidential Palace in Cairo, Egypt, Tuesday, Aug. 14, 2012. Egypt's president has given awards to the nation's two top military commanders, two days after he ordered their retirement. Tantawi, who ruled Egypt through his military council for 17 months after last year's popular uprising overthrew longtime President Hosni Mubarak, and his chief of staff, Anan, made their first public appearance to receive the nation's highest medal. (Foto:Middle East News Agency, HO/AP/dapd).
ማርሻል ተንታዊ-ክሙርሲ ጋርምስል dapd
Former Egyptian President Hosni Mubarak is wheeled out of a courtroom after his trial in Cairo in this June 2, 2012 file photo. Egypt's Appeals Court accepted an appeal by Mubarak and his former interior minister on January 13, 2013, allowing him to be retried over the killing of protesters in the 2011 uprising. REUTERS/Stringer/Files (EGYPT - Tags: POLITICS CRIME LAW)
ሙባረክ-ዘንድሮምስል REUTERS
Ägyptens Staatspräsident Husni Mubarak gibt am Flughafen eine Pressekonferenz. Auf den ägyptischen Staatspräsidenten Husni Mubarak ist am 26.6.95 in der äthiopischen Hauptstadt Addis Abeba ein Mordanschlag verübt worden. Mubarak blieb bei dem Attentat unverletzt und kehrte von der Gipfelkonferenz der Organisation Afrikanischer Einheit (OAU) umgehend nach Kairo zurück. In einer Pressekonferenz auf dem Flughafen erklärte er, möglicherweise sei das fundamentalistische Moslem-Regime des Sudans in den Mordversuch verwickelt.
ሙባረክ-ያኔምስል picture-alliance/dpa

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ