1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግብፅ አብዮትና የሙርሲ ድል

ሰኞ፣ ሰኔ 18 2004

የድሕነት መከራን ከወላጆቻቸዉ፥ በልፋት ጥረት ከድሕነት መዉጣትን ከኑሮ-ሕወታቸዉ፥ የምሕድስና እዉቀትን ከአሜሪካኖች፥ የሐይማኖት ፅናትን ከሙስሊም ወንድማማቾች፥ ፖለቲከኝነትን ከምክር ቤት እንደራሴነት ተምረዋቸዋል።ተሳክቶላቸዋልም።

https://p.dw.com/p/15LBg
25/06/12 11:42:24 1929x2800(446kb) Muslim Brotherhood's president-elect Mohamed Morsy speaks during his first televised address to the nation in Cairo Muslim Brotherhood's president-elect Mohamed Morsy speaks during his first televised address to the nation at the Egyptian Television headquarters in Cairo June 24, 2012. Morsy's victory in Egypt's presidential election takes the Muslim Brotherhood's long power struggle with the military into a new round that will be fought inside the institutions of state themselves and may force new compromises on the Islamists. Picture taken June 24, 2012. To match Analysis EGYPT-ELECTION/STRUGGLE/ REUTERS/Stringer (EGYPT - Tags: POLITICS ELECTIONS)
አዲሱ የግብፅ ፕሬዝዳንት-መሐመድ ሙርሲምስል Reuters


የግቡፁ አንጋፋ የፖለቲካ ማሕበር የሙስሊም ወንድማማቾች እጩ ዶክተር መሐመድ ሙርሲ በነፃ የሕዝብ ድምፅ የተመረጡ የመጀመሪያዉ ሲቢል የግብፅ ፕሬዝዳ ሆነዉ መመረጣቸዉ ትናንት ታዉጇል።ነጋሽ መሐመድ በዛሬዉ ማሕደረ ዜና ዝግጅቱ ብዙ የተጠበቀዉን የምርጫ ዉጤት፥ ከግብፅ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታና ከሙርሲ ማንነት ጋር አሰባጥሩ ባጭሩ ይቃኛል።ሙሉ ዝግጅቱ ይቀጥላል።


ካይሮ-ትናንት የምርጫ ኮሚሽን ፅሕፈት ቤት፦«ዶክተር መሐመድ መሐመድ ሙርሲ ኢሳ አል-አያት 13 ሚሊዮን፥ ሁለት መቶ ሠላሳ ሺሕ አንድ መቶ ሠላሳ አንድ ድምፅ በመቶኛ-----»

ተሕሪር አደባባይ።መሐመድ ሙርሲ ኢሳ አል-አያት፥ በነፃ የሕዝብ ድምፅ የተመረጡ የመጀመሪያዉ የግብፅ ፕሬዝዳት ሆኑ።የሰዉዬዉ ማንነት፥ የሚጠብቃቸዉ ፈተና እስከየትነትና የግብፅ እዉነት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ፥ አብራችሁኝ ቆዩ።


ካይሮ በዓመት ከመንፈቋ እንደገና ተደሰተች።ፈነደቀች።ተሕሪር አደባባይ ቦረቀች።ትናንት።ግብፅ ተስፋ፥ ግን የሩቅ ደግሞም በጥርጣሬ የተለወሰ ተስፋ ፈነጠቀች።የደስታ፥ ፍንደቃዉ ምክንያት፥ የፌስታ ፈንጠዝያ፥ ተስፋዉ ሰበብ ግን በተለይ ለኒያ-ወጣት አብዮተኞች፥ የካይሮዋ ወጣት ራይና ጋብር እንደምትለዉ ከሙርሲ ድል ይልቅ፥ የሻፊቅ ሽንፈት ነዉ።

«ሻፊቅ በመሸነፋቸዉ በጣም ከሚገባዉ በላይ ደስተኛ ነኝ።ሻፊቅ መሸነፋቸዉ ሙርሲ ከማሸነፋቸዉ በላይ አስደሳች ነዉ።እና የሙርሲ ድል ማለት አብዮቱ ይቀጥላል ማለት ነዉ።»

ጡረተኛዉ የአየር ሐይል ጄኔራል፥ የቀድሞዉ ፕሬዝዳት የሆስኒ ሙባረክ የመጨረሻ ጠቅላይ ሚንስትር አሕመድ ሻፊቅ የመሪነቱን ሥልጣን እንዲይዙ ሙባረክን ከተኩት የጦር ባልደረቦቻቸዉ ያልተደረገላቸዉ ድጋፍ አልነበረም።ግን ተሕሪር አደባባይን ዕለት በዕለት ያጥለቀለቀዉ ሕዝብ ተቃዉሞ፥ ቁጣ፥ የዳግም አብዮት ዝግጅት፥ዛቻ መናር፥ በሥልጣን ላይ ያለዉ የጦር ሐይሎች ጠይላይ ምክር ቤት ሻፊቅን ለሥልጣን ለማብቃት ካደረገዉ በላይ እንዳያደርግ አግዶታል።

ሐማዳ ረመዳን አብድል አዚዝ በዓመት ከመንፈቅ ለሁለተኛ ጊዜ ዉሎ አዳሩን ተሕሪር አደባባይ ካደረገዉ የካይሮ ወጣት አንዱ ነዉ።ፊልድ ማርሻል መሐመድ ሁሴይን ተንታዊ የሚመሩት የጦር ሐይሎች ጠቅላይ ምክር ቤት የወሰደና የሚወስደዉን እርምጃ በመቃወም ከዚያ ታሪካዊ የነፃነት ወይም የሠማዕታት አደባባይ ሙጥኝ ያለዉ ያ ወጣት ትናንት በብዙ ሺሕ እንደሚቆጠሩ ብጤዎቹ ሁሉ አንድም በደስታ ሊቦርቅ፥ አለያም በቁጣ ሊፈክር ሲቁነጠነጥ ነበር ያረፈደዉ።


አይን-ጆሮዉን ከተንቀሳቃሽ ሥልክ ራዲዮዉ ላይ እንደለገተ ነዉ።የምርጫ ኮሚሽኑ የበላይ ሐላፊ ፋሩቅ ሱልጣን ንግግር ጀመሩ።ሥለ ምርጫዉ ሒደት፥ የተጭበረበሩ ድምፆችን ብዛት፥ ትክክለኛዉን ድምፅ ከተጭበረበዉ ለመለየት፥ ኮሚሽኑና ባልደረቦቹ ሥላደረገዉ ማጣራት ያትታሉ።«እነዚሕ ሰዎች» አለ ሐማድ ለጓደኛዉ በተሰላቸ ስሜት «ሊያታልሉን ነዉ።» መልስ አልጠበቀም።አይን ጆሮዉን እንደገና ከሞባይሉ ሰካ።

የካይሮ ፀሐይ መጋም ጀምራለች።አርባ ዲግሪ ሴልሲየስ።እነሐማድም በንዴት-እየጋሉ፥ በላብ እየራሱ፥ ትንፋሻቸዉ ይቆራረጥ ገባ።የኮሚሽነር ሱልጣን ገለፃ፥ ንግግር እንደቀጠለ ነዉ። «ያላ፥ ያላ ሙርሲ ነዉ ሻፊቅ» ጠየቀ ከሐማድ ጓደኞች አንዱ-እሱም ሞባይሏ ላይ አፍጥጧል።ኮሚሽነሩ የሰሙት ይመስል መለሱ።

«ዶክተር አሕመድ መሐመድ ሻፊቅ ዘኪ አስራ-ሁለት ሺሕ ይቅርታ አስራ ሁለት ሚሊዮን ሰወስት መቶ አርባ ሰባት ሺሕ ሰወስት መቶ ሰማንያ፥ በመቶኛ ሲሰላ 48.27 ድምፅ፥ ዶክተር መሐመድ መሐመድ ሙርሲ ኢሳ አል-አያት 13 ሚሊዮን፥ ሁለት መቶ ሠላሳ ሺሕ አንድ መቶ ሠላሳ አንድ ድምፅ። በመቶኛ ሲሰላ 51.87-----»


ሐማድ ረመዳን አብዱል አዚዝ ፊቱን ጓደኛዉ ትከሻ ላይ ደፍቶ ተንሠቀሰቀ።የደስታ ለቅሶ፥ የምስጋና ፀሎት ያጀበዉ እንባ።

«በጣም ደስተኛ ነኝ።ይሕን ድል ላጎናፀፈን ፈታሪ ምሥጋና ይግባዉ።ይሕ እንዲሆን ለረጅም ጊዜ ሥንጠብቅ ነበር።ድሉ የመላዉ ግብፃዉያን ነዉ።»

የሙርሲ ድል ለታሪካዊቷ ሐገር አዲስ ታሪክ ነዉ።በነፃ ምርጫ በሕዝብ ድምፅ የተመረጡ የመጀመሪያዉ ሲቢል ፕሬዝዳት ናቸዉ።በአረቡ አለም ረጅም ታሪክ ያለዉ የፖለቲካ ፓርቲ የሙስሊም ወንድማማቾችም የመጀመሪያዉ ፕሬዝዳት ናቸዉ።

እኛ ወፍራም፥ ግራጫ ፀጉር፥ ፂማም የምሕንድስና ዶክተርም በድል ብሥራት ንግግራቸዉ የተሕሪር አደባባዩ ሠልፈኛ ተስፋ እንዳደረገዉ ሁሉ፥ ሁሉንም ግብፃዊ እኩል የማይ፥ እኩል የምመራ፥ እኩል የምሠራለት ነኝ አሉ።

«ታላቁን የግብፅን ሕዝብ አመሰግናለሁ።ለሕዝቡ የምችለዉን ሁሉ አደርጋለሁም።የግብፅን ጦርም አመሠግናለሁ፥ ይሕን የሐገሪቱን ፀጥታና ደሕንነት የሚያስከብረዉን ተቋም አከብራለሁም።የሁሉም ግብፃዉያን ፕሬዝዳት ነዉ-የምሆነዉ።በዉጪ የሚኖሩ፥ ሐገር ዉስጥም ያሉ፥ የሙስሊሞችም የክርስቲያኖችም የሁሉም ግብፃዉያን መሪ ነኝ።ግብፆች በአንድነት መቆም አለባቸዉ።አብዮቱ ግቡን እስኪመታም ድረስ መቀጠል አለበት።»

ግብፆች ግን ቢያንስ እስካሁን ባንድነት አልቆሙም።ሙርሲ ሸሪዓን መመሪያዉ ያደረገዉ የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ የረጅም ጊዜ ታማኝ አባል ናቸዉ።ባለፈዉ ግንቦት ለመጀመሪያዉ ዙር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሲወዳደሩ አንድ ሥፍራ ያደረጉት ንግግርም አንጋፋዉ ፓርቲ ግብፅን በሸሪዓ ለመግዛት አልሟል የሚል ትርጓሜ አሰጥቶ ነበር።

«ይቺን ሐገር ወደ ጥንታዊ እሷነቷ ልንመልሳት ይገባል»

በመለያዉ ምርጫ ግን ይሕን አልደገሙትም።ለምርጫ ዘመቻቸዉ በተደጋጋሚ ባደረጉት ንግግር የግብፅ ሕዝብ ታላቅነትን፥ የአብዮትን ፍሬዎች የመጠበቅ፥ በጋራ የመቆም ጠቃሚነትን፥ የፍትሕ እኩልነት አስተዳደር አስፈላጊነትን ነበር-የገለፁት።

እርግጥ ነዉ አንጋፋዉ የፖለቲካ ማሕበር እንደ ቱርኩ የፍትሕና ዕድገት፥ እንደ ቱኒዚያዉ አናሕዳሕ ፓርቲ እራሱን ከሐይማኖታዊ ፅፈኝነት ወደ ለዘብተኛ ሐገር መሪነት የማይቀይበርበት ምክንያት የለም ባዮች ብዙዎች ናቸዉ።ያም ሆኖ ከሕዝባዊዉን አብዮት ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች አንዷ አሚራ ሳሌም እንደምትለዉ ሙስሊም ወንድማማቾች ግብፅን እንደ ኢራን ወይም እንደ አፍቃኒስታን በሸሪዓ ሕግ ልግዛ ማለቱ አይቀርም ብለዉ ብዙ ግብፃዉያን ይሰጋሉ።

«ሙስሊም ወንድማማቾች ያስፈራኛል።ሙርሲ ለረጅም ጊዜ ሥልጣን ለመያዝ ነዉ የሚፈልጉት።ግብፅ ደግሞ እንደ ኢራን ወይም እንደ አፍቃኒስታን ልትሆን አትችልም።»

ሰዉዬዉ! የድሕነት መከራን ከወላጆቻቸዉ፥ በልፋት ጥረት ከድሕነት መዉጣትን ከኑሮ-ሕወታቸዉ፥ የምሕድስና እዉቀትን ከአሜሪካኖች፥ የሐይማኖት ፅናትን ከሙስሊም ወንድማማቾች፥ ፖለቲከኝነትን ከምክር ቤት እንደራሴነት ተምረዋቸዋል።ተሳክቶላቸዋልም።

በተመሰቃቀለዉ የዓለም የፖለቲካ ባሕር ዋኝተዉ፥ የነአሚራን ጥርጣሬ አስወግደዉ፥ በፖለቲካ ማዕበል ቀራ-ቀኝ ከሚላጋ ባሕር የምትቀዝፈዉን ሐገራቸዉን መርተዉ ከዉድቀት ያድኗት ይሆን ይሆን ወይ ነዉ የከእንግዲሁ።የቀድሞዉ የሙስሊም ወንድማማቾች ከፍተኛ ባለሥልጣን አብድል ሳተር ኤል ሜሊግ እንደሚሉት ዶክተር ሙርሲ ለአለቆቻቸዉ እሺ ባይ፥ ከአለቆቻቸዉ የቀረቡ ሐሳቦችን ገቢር አድራጊ እንጂ አዳዲስ ሐሳቦችን አፍላቂ አይደሉም።

በርግጥም ሳታር ከትልቁ የፖለቲካ ሥልጣን ራሳቸዉን ያገለሉት ቱጃሩ ፖለቲከኛ ኸይርያት ኤል ሻታር ከማሕበሩ ሁለት ምክትል ሊቃነመናብርቶች አንዱ ሆነዉ መመረጣቸዉን በመቃወም ነበር።እንደ ሳታር ሁሉ ለዘብተኛ ወይም በዘመናዩ ትምሕርት የገፉ በርካታ የፓርቲዉ አባላት የሻታርን መመረጥ በመቃወም ፓርቲዉን ሲለቁ ወይም ከስልጣናቸዉ ዝቅ ሲሉ ሙርሲይ በነበሩበት ቀጠሉ።

ኸይርያት አል-ሻታር ፓርቲዉን ወክለዉ ለፕሬዝዳትነት ለመወዳደር ሲጠይቁ እንኳን ሙርሲ የአለቃቸዉን ጥያቄ አልተቃወሙም፥ እራሳቸዉን ለእጩነት አላቀረቡምም ነበር።አል-ሻታር የመወዳደሪያዉን ነጥብ አያሟሉም በሚል ሥጋት ፓርቲዉ ሌላ እጩ ሲፈልግ ግን ፖለቲከኛዉ መሐንዲስ ብቅ አሉ።

ይሕ ሲፋጅ መተዉ፥ ሲሞቅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ አይነት ብልሐታቸዉ በቅርብ የሚያዉቋቸዉ እንደሚሉት የፖለቲካ ብሥለት ወይም ሥልታቸዉ አይደለም።የኖሩ፥ ያደጉ፥ የተማሩ ያስተማሩበት ባሕሪያቸዉ ጭምር እንጂ።


ከካይሮ በስተሰሜን በምትገኘዉ በአል-ሸርቂያ አዉራጃ፥ በአል-አድዋ መንደር በአባይ ወንዝ ዉሐ አትክልት ፍራፍሬ ከሚያበቅል ደሐ ገበሬ ቤተ-ሰብ ተወለዱ።ድሕነትን በንግድም፥ በወታደርነትም፥ በሌላም ብሎ ባንዴ ሮጦ ማምለጥ ይቻላል።ሮጦ ማምለጣ እንደሚቻል ሁሉ ሲሮጡ ተላትሞ መዉደቅ እንዳለም ከደመነብስ ግምት ባለፍ ለዚያ ሕፃን የመከረ-የነገረዉም አልነበረም።

ብቻ ለድሕነት አንገቱን የደፋ መስሎ ከድሕነት ቀስ በቀስ ለማምለጥ ጥርሱን ነክሶ ይማር ገባ።በ1975 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከካይሮ ዩኒቨርስቲ በኢንጂነሪግ ወይም በምሕንድስና የመጀመሪያ ዲግሪዉን ሲያገኝ፥ የድሕነትን ጠርዝ ተዘናገረ።ወጣቱ ሙርሲ ከዚያዉ ዩኒቨርስቲ፥ በዚያዉ መስክ ሁለተኛ ዲግሪዉን በያዘበት አመት የሙስሊም ወንድማማቾችን ፓርቲን ተቀየጠ 1978 ።

ባንዴ የተዋጣለት መሐንዲስም፥ ሐይማኖት አጥባቂም፥ ፖለቲከኛም ሆነ።ይሑንና እንደ ብዙዎቹ አክራሪ ሙስሊሞች ሐይማኖትን ሙጥኝ ብሎ መስጊድ አልመሸገም።አክራሪዎቹ የሐይማኖት፥ በጣሙን የሙስሊም ፀር እያሉ የሚኮንኗትን አሜሪካን ጠልቶ-አላወገዘም።እንዲያዉም እዉቀት ትምሕርቱን ሊያሻሽልባት ተጓዘባት።በ1982 ከዩኒቨርስቲ ኦቭ ሳዉዘርን ካሊፎርኒያ የPhD ዲግሪዉን አገኘ።እና በርድሜም በእዉቀትም አንቱ ሆነ።

ዶክተር መሐመድ ሙርሲ ኢሳ አል-ኢያት።

በአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ለሰወስት አመት አስተምረዋል።አሜሪካ እያሉ የወለዷቸዉ ሁለት ልጆቻቸዉ በትዉልድ አሜሪካዊ ናቸዉ።በ1985 ግብፅ ተመልሰዉ የካይሮዉ ዛጋዚግ ዩኒቨርስቲ የምሕድስና ፕሮፌሰር ናቸዉ።ከሁለት ሺሕ እስከ ሁለት ሺሕ አምስት ድረስ በግል ሥም ተወዳድረዉ በምክር ቤት እንደራሴነት አገልግለዋል።

በሙባረክ ዘመን እንደ ብዙዎቹ የሙስሊም ወንድማማቾች ማሕበር አባላት ሁሉ ታስረዉ ነበር።ግን ላጭር ጊዜ ።ብዙዎቹ የፓርቲዉ አባላት አምስት ስድስት አመት ሲታሰሩ እሳቸዉ ብዙ አመታት ያልታሰሩት አንድም በምልጣብልጥነታቸዉ፥ አለያም በሙሕርነታቸዉ ወይም በአጋጣሚ ሊሆን፥ ላይሆንም ይችላል።ብቻ ከስምት ወር በላይ አልታሰሩም።ሙባረክ ከተወገዱበት ከሁለት ሺሕ አስራ-አንድ ጀምሮ የሙስሊም ወንድማማቾች አባል የሆነዉ የነፃነትና የፍትሕ ፓርቲ መሪ ናቸዉ።አሁን የድፍን ግብፅ ፕሬዝዳት።የስልሳ አመት አዛዉንት።


አጋጣሚ እስኪመቻች አድፍጦ የመቀመጥ፥ ጉልበት፥ አቅም እስኪገኝ ነገሮችን በትዕግሥት የመጠበቅ ባሕሪያቸዉ በዘመነ-ፕሬዝዳትነታቸዉ የሚገጥማቸዉን ፈተና በዘዴ ለማለፍ፥ የሕዝቡን ችግር ለማቃለል ይረዳቸዋል ባዮች ብዙ ናቸዉ።በካይሮ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር አብዱል ሙናም አል-መሻት እንደሚሉት ግን ሙርሲ የሚጠበቅባቸዉን ለማድረግ አቅም ብልሐቱ ቢኖራቸዉ እንኳን የጦር ሐይሎች ምክር ቤቱ ሥልጣኑን ጠቅልሎ ይዞባቸዋል።

«ይሕ ማለት (የጦሩ ምክር ቤት እርምጃ) አዲሱ ፕሬዝዳንት በጣም ትንሽ ሥልጣን ነዉ ያለዉ ማለት ነዉ።እንዲያዉ የይስሙላ እንጂ የመወሰን ሥልጣን የለዉም።»

በርግጥ የጦር ሐይሎቹ ጠቅላይ ምክር ቤት በሕዝብ የተመረጠዉን ምክር ቤት በትኗል።ሕገ-መንግሥት የማርቀቅ፥ የማፅደቅ፥ የጦር ሐይሎች ጠቅላይ አዛዥነቱን፥ ሕግ የማስከበር የርዕሥ ብሔርነቱን ሥልጣን ሁሉ ጠቅልሎ ይዞታል።ሙርሲ ፕሬዝዳት ከመባል ሌላ ምን ቀራቸዉ? ግን «ኢንሻ አላሕ ይላል» ግብፅ።ሙርሲም።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።
ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ







epa03267748 Egyptian presidential candidate Ahmed Shafik (C) casts his vote at a polling station during the run-off presidential elections in Cairo, Egypt, 16 June 2012. Some 50 million people are eligible to vote in the two-day poll to pick a successor to former president Hosni Mubarak, who was deposed in a popular revolt last year. The two contenders; Muslim Brotherhood candidate, Mohammed Morsi, and Mubarak's last PM, Ahmed Shafiq, failed to secure an outright majority in the first round last month. EPA/KHALED ELFIQI +++(c) dpa - Bildfunk+++
ተሸናፊዉ እጩ-ሻፊቅምስል picture-alliance/dpa
Supporters of Muslim Brotherhood's presidential candidate Mohamed Morsy celebrate his victory at the election at Tahrir Square in Cairo June 24, 2012. REUTERS/Ahmed Jadallah (EGYPT - Tags: POLITICS ELECTIONS)
የሙርሲ ደጋፊዎችምስል Reuters
Bild 2: Hamada Ramadan Abdelaziz freut sich über den Sieg Mursis. Die Copyrightrechte liegt bei Mohammed Bdawi
ሐማድ ረመዳን አብዱል አዚዝና ጓደኞቹምስል Mohammed Bdawi
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ