1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግብፅን ትርክት በእውቀት የምትሞግተው ወጣት

ዓርብ፣ ሐምሌ 17 2012

ኢትዮጵያ በዚህ ሳምንት የመጀመሪያዉን ዙር የሕዳሴ ግድብ ውኃ ሙሌት ማጠናቀቅዋን አብስራለች። አባይ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ ገንዘብ ከመለገስ ባሻገር ስለግድቡ ፍትሃዊነት በዓለም አቀፍ መድረኮች በማስረዳት እና በመከራከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ ኢትዮጵያዉያን ጥቂቶች አይደሉም።

https://p.dw.com/p/3fsH9
Mekdelawit Messay
ምስል Privat

«አባይ ከኢትዮጵያ እንደሚመነጭ የሚያውቀው ሰው ጥቂት ነው»

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ታላቁን የህዳሴ ግድብ መገንባት ከጀመረች ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ  ለግድቡ ግንባታ ገንዘብ ከመለገስ ባሻገር  «የግብፅ  ብቸኛ የወንዙ ተጠቃሚ ነኝ» ትርክት ለመመከት በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ መድረኮች የኢትዮጵያን በወንዙ የመልማት መብት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስረዳት ላይ ይገኛሉ።ከነዚህም መካከል ወጣት መቅደላዊት መሳይ አንዷ ነች። መቅደላዊት በሃያዎቹ መጨረሻ የምትገኝ  መምህርትና ተመራማሪ ወጣት ነች።የመጀመሪያ ዲግሪዋን በሲቪል ምህንድስና የሁለተኛ ዲግሪዋን ደግሞ በዉኃ ምህንድስና ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ አግኝታለች።ሌላ ሁለተኛ የማስተርስ ዲግሪዋን ደግሞ ኔዘርላንድ ከሚገኘው የዋግኒገን ዩንቨርሲቲ በአካባቢ ሳይንስ ተከታትላለች።ወጣቷ በአባይ ተፋሰስና በፍትሃዊ የዉኃ ክፍፍል ላይ ጥናቶችን ሰርታለች። በትምህርትና በጥናት ያገኘችውን ዕውቀት መሰረት አድርጋም በተለያዩ መድረኮች ስለ ፍትሃዊ የአባይ ውኃ ተጠቃሚነትና ኢትዮጵያ ስለተገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ አስፈላጊነት እንዲሁም የኢትዮጵያን በአባይ የመልማት መብት በተለያዩ የውጭ የመገናኛ ብዙሃን ያለመታከት እዉነቱን በማስረዳትና በመሞገት ላይ ትገኛለች። 
ለመጀሪያ ጊዜ አውስትራሊያ ውስጥ ከሚገኝ  SBS ከሚባል ሬዲዮ ጋር በግድቡ እንዲሁም በፍትሃዊና ምክንያታዊ የውኃ ተጠቃሚነት ዙሪያ ውይይት አድርጋለች። ቀጥላም  ከአልጀዚራ፣France 24 ጋርና ከሌሎች የውጭ የመገናኛ ብዙሃን ጋር ቃለ-ምልልስና ከግብፃውያን ጋር ክርክር አድርጋለች።
መቅደላዊት  በልጅነት ጊዜዋ «አባይ አባይ የሀገር ሲሳይ»ን ዘምራ ብታድግም የአባይ ውኃ ጥቅምና ጉዳቱ  የገባትና  ፍላጎቷ ወደ ዉኃ ሳይንሱ ማዘንበል የጀመረው ግን፤ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በያዘችበት የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ አምስት ኪሎ ግቢ የመጀመሪያ አመት ተማሪ በነበረችበት ወቅት ነው። የሁለተኛ ዓመት ተማሪ እያለች የታላቁ የህዳሴ ግድብ መጀመር ደግሞ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከመደሰት ባለፈ በሙያዋ የበኩሏን ለማበርከት  መነሳሳትን ፈጥሮላታል።እናም የሁለተኛ ዲግሪዋን የመመሪቂያ ፅሁፍ  በህዳሴው ግድብ ላይ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ይደረግ በነበረው ድርድር ያለውን የመረጃ ክፍተት ሊሞላ ይችላል በሚል «በአባይ ተፋሰስ ሀገራት ፍትሃዊና ምክንያታዊ የዉኃ ተጠቃሚነት» ዙሪያ ጥናት አካሂዳለች።ከዚያም ይህንን መረጃ ወደ ህብረተሰቡ ለማድረስና ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘውን የዲፕሎማቲክ ማህበሰብ ለማስረዳት በግድቡ ዙሪያ ሙያዊ አስተያየቶቿን በእንግሊዝኛ ቋንቋ በኢትዮጵያን ሄራልድ፣ በፎርቹን፣በአዲስ ስታንዳርድ ፣በሪፖርተርና በሌሎች በበርካታ ጋዜጦች ፅፋለች።
የአባይ ተፋሰስ 70 በመቶ  የሚሆነውን የኢትዮጵያ የገፀ-ምድር ዉኃ የያዘ  ሲሆን የሀገሪቱ ሁለት ሶስተኛ የመስኖና ሀይል የማመንጨት አቅም ያለውም  በዚሁ ተፋሰስ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።በዚህ የተነሳ የዚህ ተፋሰስ መልማት ህዝቡን ከድህነት ለማውጣትና ሀገሪቱን ለማሳደግ የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም። ሆኖም ግን ይህንን እውነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ  በተገቢው ሁኔታ ማስረዳት ባለመቻሉ የህዳሴው ግድብ ለቅንጦትና ሀይልን ለማሳየት እየተገነባ ያለ የሚመስላቸውና ኢትዮጵያን እንደ ጥፋተኛ የሚቆጥሩ መኖራቸውን  በውጭ የመገናኛ ብዙሃን በቀረበችበት ወቅት መገንዘቧን ታስረዳለች።
«በኛ በኩል የኢትዮጵያ ትርክት ምንድነው።ኢትዮጵያ ለምንድነው አባይ የሚያስፈልጋት ።የህዳሴው ግድብ ለምንድነው እየገነባን ያለነው የሚለውንና እኛ እዚህ ዉኃ ላይ ምን ያህል ዲፐንደት ነን የሚለውን በማሳየት ላይ  በጣም ትልቅ ችግር አለ።አባይ ከኢትዮጵያ እንደሚመነጭ የሚያውቀው ሰው ጥቂት ነው።አባይን ሁልጊዜ ሰው ከግብፅ ጋር ነው የሚያያይዘው።በሳይንሱም፣በህጉም በሞራል ልዕልናውም ትክክለኛውን መንገድ ይዘን እየተጓዝን እያለን እንደ ጥፋተኛች ነው የምንቆጠረው። ለምን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተንሰራፋው ትርክት የግብፅ ትርክት ነው።ኢትዮጵያ የህዳሴው ግድብን መገንባቷ ወይም አባይን መንካቷ የግብፅ ህዝብን ዉኃ ለማስጠማት ወይም ለማስራብ ተደርጎ ስለሚነገር «ኢንተርናሽናል ሚዲያው»ላይ እኛ ወጥተን ስንናገር ለቅንጦት የምንሰራው ወይም ዉኃው ላይ የበላይነትን ለማግኘት ወይም በምስራቅ አፍሪቃ ትልቅ «ፓወር ሀውስ» ለመሆን እንደምንሰራው አድርገው ያቀርቡታል።» በማለት ገልፃለች።
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካትም የአባይ ወንዝ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተፋሰሱ ሀገራት ለሚገኙና በአብዛኛው በድህነት ለሚኖሩ 400 ሚሊዮን ህዝቦች  የሚኖረውን ጠቀሜታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳትም እንደ ወጣቷ ሌላው ቁልፍ ጉዳይ ነው።ሆኖም ግን በኢትዮጵያ በኩል ብዙ አልተሰራበትም።የዓባይ ዉሃን ተጠቃሚነት በተመለከተ በዓለም አቀፉ መድረክ ግብፃውያን የሀገራቸውን ጥቅም ለማስከበር ብዙ ርቀት መሄዳቸውን ጠቁማ፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊም  የሀገሩን ጥቅም ለማስከበር በሙያው የሚቻለውን ሁሉ ማበርከት ይገባዋል ባይ ነች።
« ለኔ የሚታየኝ ሁሉም በያለበት ሙያ የበኩሉን ማበርከት አለበት ነው።ሁሉም በሙያው ማድረግ የሚችለውን የመጨረሻውን ነገር ማድረግ ቢችል ፤ ሁላችንም  ያንን  ማድረግ ስንችል ሀገራችን ወደ ፊት ፈቀቅ ትላለች።ሁላችንም ባለን ሙያ  የምንችለውን በቅን ልቡናና በሀገር ተቆርቋሪነት ማድረግ ከቻልን በቃ ሀገር ማለት ህዝብ ነው።የእያንዳንዱ ሰው ድምር ነው ሀገር የሚፈጥረው ለኔ የሚሰማኝ ያ ነው።»
የመምህርነት ሙያ የነብስ ጥሪዋ መሆኑን የምትናገረው ወጣት መቅደላዊት መሳይ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲና በኔዘርላንዱ ዋግኒገን  ዩንቨርሲቲ በረዳት መምህርነት ሰርታለች።በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአሜሪካ ፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ዩንቨርሲቲ የዶክትሪት ዲግሪዋን በመጭው ነሀሴ ወር ለመጀመር በመጠባበቅ ላይ ነች።ለወደፊቱም በማስተማር ስራው እንዲሁም ሀገርና ህዝብን ሊጠቅሙ የሚችሉ የጥናትና የምርምር ስራዎች ማካሄዷን እንደምትገፋበትም አጫውታናለች።

Mekdelawit Messay
ምስል Privat


ፀሐይ ጫኔ
ሂሩት መለሰ