1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋውክ የታንዛኒያ ጉብኝት

ሐሙስ፣ ጥር 28 2007

የጀርመን ፕሬዝዳንት ዮአሂም ጋውክ የአምስት ቀናት የታንዛኒያ ጉብኝት ነገ ያበቃል ። የጉብኝታቸው ዋነኛ ዓላማ የረዥም ጊዜ ታሪክ ያለውን የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር ነው ። ጋውክ ከታንዛኒያ ባለሥልጣናት ጋር ከተወያዩባቸው ዐርዕስት ውስጥ የሁለቱ ሃገራት የኤኮኖሚ ግንኙነት ይገኝበታል ።

https://p.dw.com/p/1EWE2
Tansania Daressalam Empfang von Bundespräsident Gauck 2.2.2015
ምስል picture-alliance/dpa/Wolfgang Kumm

ጋውክ በታንዛኒያ ቆይታቸው የሁለቱ ሃገራት የግንኙነት መስመር አንዳንድ የቀድሞ ቅሬታዎችን ያስወገደ እንደነበረ አውስተዋል ። የጀርመን ፕሬዝዳንት ዮአሂም ጋውክ የታንዛኒያ ጉብኝት ከርሳቸው በፊት የጀርመን ፕሬዝዳንት የነበሩት ክርስቲያን ቩልፍ ካቆሙበት የቀጠለ ነው ። ቩልፍ ከስልጣን ከመውረዳቸው ጥቂት ቀናት አስቀድሞ እጎአ በ2012 መጀመሪያ ላይ የቀድሞ የጀርመን ቅኝ ግዛት የነበረችውን ታንዛኒያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪቃ ሃገራትን ለመጎብኘት አቅደው ነበር ። ጋውክ ቩልፍ የጀመሩትን ከፍፃሜ ማድረሳቸው የታሰበው እንዳይቀር ያህል አይደለም ይላሉ ዳሬሰላም ታንዛኒያ የሚገኘው የጀርመኑ የኮናርድ አደናወር ተቋም ቢሮ ሃላፊ ሪቻርድ ሻባ ፤ ከዚያ ይልቅ ዋናው ምክንያት ሁለቱን ሃገራት የሚያስተሳስው የጠበቀው ታሪካዊ ግንኙነት መሆኑን ሻባ ተናግረዋል ።
«የታንዛኒያንና የጀርመንን ግንኙነት ስንመለከት እንደሚመስለኝ በታሪክ እንቀራረባለን ። ታንዛኒያዎች ግንኙነቱን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ወይም ደግሞ ጀርመኖች ግንኙነቱን እንዲያሰፉት የሚያደርጉ ሌሎች ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ ።ሆኖም ታሪካዊ አሻራው ሊታለፍ አይገባም ።አዎ ጀርመን ታንዛኒያን ቅኝ ገዝታ ታሪክ ትታለች ። ሆኖም ዛሬ ታንዛኒያን ቅኝ አትገዛም ። እናም ግንኙነት እንዲኖር አያስፈልግም የሚባልበት ምክንያት አይኖርም ።»ሻባ እንደሚሉት የጀርመንና ታንዛኒያ ግንኙነት የሚጀምረው ሃገሪቱ በጀርመን ቅኝ አገዛዝ ስር ከወደቀችበት ጊዜ አንስቶ ነው ።ታንዛንያ ቅኝ መገዛቷ ግን የአሁኑን የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት አልጎዳም ። ሆኖም የጀርመን የታንዛኒያ ቅኝ አገዛዝ ካበቃ በኋላ ፣ቢያንስ ሁለት ጊዜ በሁለቱ አገራት መካከል ዲፕሎማሲያዊ ችግሮች ተከስተው ነበር ።አንደኛው የታንጋኒካና የዛንዚባር ግዛቶች እጎአ በ1964 በአንዲት ታንዛንያ ስር ከተዋሃዱ በኋላ ነበር ። ያኔ የታንጋኒካ ግንኙነት ከጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ ወይም ከያኔው ምዕራብ ጀርመን ጋር ሲሆን ዛንዚባር ደግሞ የቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን ወዳጅ ነበረች በወቅቱ የምዕራብ ጀርመን መመሪያ መንግሥታት ከምዕራብ ጀርመን ሌላ የጀርመን መንግሥት አለ ብለው ሊቀበሉ አይገባም የሚል ነበር ።በዚሁ ምክንያት የመጀመሪያው የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ጁልየስ ኔሬሬ ከቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን ጋር የነበራቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ የተደረገውን ሙከራ ውድቅ በማድረግ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ሲሉ ከጀርመን ኤምባሲ ሠራተኞች በስተቀር ታንዛኒያ የሚገኙ ጀርመናውያንን በሙሉ ማባረራቸው አንዱ ዲፕሎማሲያዊ ችግር ነበር ።ሁለተኛው አስቸጋሪ ወቅት ደግሞ እጎአ

Gauck in Tansania 03.02.2015 Daressalam
ምስል DW/M. Khelef
Gauck in Tansania mit Präsident Kikwete 03.02.2015 Daressalam
ምስል Reuters

2013 ታንዛኒያ አንዳችም ማብራሪያ ሳታቀርብ ለአዲሱ የጀርመን አምባሳደር እውቅና አለ መስጠትዋ ነበር ።ሆኖም እነዚህ ችግሮች አልፈዋል ። ታንዛኒያውያንም አሁን ፕሬዝዳንት ጋውክን ተቀብለው ለማስተናገድ በቅተዋል ይላሉ በዳሬሰላም ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነቶች ምሁር ምዌሲጋ ባሬጉ
«ታንዛንያውያን ስለጀርመንና ታንዛኒያ ግንኙነት ያውቃሉ ። ከዚህ በተጨማሪም ጀርመንና የጀርመን ተቋማት በታንዛኒያ የሲብል ማህበራት እንዲጠናከሩ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉም አሳይተዋል ።ለዚህም ነው እነዚህን እንግዶች በጥሩ ሁኔታ የተቀበሉት ።»
ባሬጉ እንደሚሉት የጀርመን ድርጅቶች በታንዛኒያ የሲብል ማህበራት ግንባታ ውስጥ ትልቅ ድርሻ አላቸው ።ታንዛኒያ በዚህ ዓመት አጠቃላይ ምርጫና ህዝበ ውሳኔ ታካሂዳለች ። ይህ በሃገሪቱ በጀት ላይ ጫና እንደሚያደርግ ይታመናል ። ለዚህ መፍትሄ ለመሻት የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ጃካያ ኪክዌቴ ድጋፍ ሳያሻቸው አይቀርም ። ለጋሽ ሃገራት ለታንዛንያ የእርዳታ ገንዘብ እንዲለቁ ጀርመን ታሳምናለች ተብሎ ይጠበቃል ።ሌላው የታንዛንያ ፍላጎት የኮናርድ አደናወሩ ሪቻርድ ሻባ እንደሚሉት በታዳሽ የኃይል ምንጮች መስክ የውጭ ባለሃብቶች ተሳትፎ ነው ።ጀርመን በዚህ ረገድ ታላቅ ሚና ልትጫወት ትችላለች ይላሉ ሻባ ።

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ