የጊኒ የምርጫ ዉዝግብ
ረቡዕ፣ ጥቅምት 3 2008የኅብረቱ ታዛቢ ቡድን ምርጫዉ ተዓማኒ ነዉ ቢልም በሂደቱ ላይ የታዩ ጉድለቶችንም ጠቁሟል። ያም ቢሆን ግን የእሁዱን ምርጫ አጠቃላይ ዉጤት ጥያቄ ላይ የሚጥል እንደማይሆን አመልክቷል። የአፍሪቃ ኅብረት ታዛቢ ቡድንም ተመሳሳይ መግለጫ ነዉ የሰጠዉ።
ጊኒ አመፅ በተቀላቀለዉ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የምትታወቅ ምዕራብ አፍሪቃዊት ሃገር ናት። በፈረንሳይ ቅኝ በመገዛትዋም ቀደም ባሉት ጊዜያት የፈረንሳይ ጊኒ ስትባል ኖራለች። ከጊኒ ቢሳዎ እና ከኢኳቶሪያል ጊኒ እንድትለይ ደግሞ ጊኒ ኮናክሪ በመባል ትታወቃለች። ከፈረንሳይ የቅኝ ተገዢነት በጎርጎሪሳዊዉ 1958ዓ,ም ነፃ ከወጣች ወዲህ ጊኒ ኮናክሪ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስታካሂደ ሁለተኛዋ መሆኑ ነዉ።ፈረንሳይኛን ለብሔራዊ ቋንቋነት የምትጠቀመዉ ይህች ሀገር የራሷ የሆኑ 24 ቋንቋዎችም ይነገሩባታል።
እሁድ ዕለት በሀገሪቱ የተካሄደዉን ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የተከታተለዉ የአዉሮጳ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን የድምፅ መስጫ ቁሳቁሶች እጥረት እና የምርጫ ጣቢያዎች ዘግይተዉ መከፋቸዉን እንደእንከን ይጠቅሳል። የኅብረቱ ታዛቢ ቡድን መሪ ፍራንክ ኤንግልስ ሁለት ሶስተኛዉ የምርጫ ጣቢያ በአስፈላጊ ቁሳቁሶች እጥረት ዘግይቶ መከፈቱን፤ አንዳንዱም ጋየድምጽመክተቻሳጥንእንዳልነበርአመልክተዋል። ያ ማለት ግን የተካሄደዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ተጭበርብሯል በሚል ዉጤቱን ጥያቄ ላይ የሚጥል አይደለም እንደኤንግልስ።ምክንያቱ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች በአብዛኛዉ የምርጫ ጣቢያ ተገኝተዋል፤ ድምፅ ቆጠራዉም በአመዛኙ ግልፅ ነበር ሲሉ እማኝነታቸዉን ሰጥተዋል።የአፍሪቃ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድንም የአዉሮጳ ኅብረት ታዛቢ ቡድን የሰጠዉን አስተያየትና ትዝብት እንደሚጋራ አስታዉቋል።የሀገሪቱ የተቃዉሞ ፖለቲካ አባላትና ደጋፊዎች ግን ምርጫዉ ተጭበርብሯል ተቀባይነት የለዉም እያሉ ነዉ።የቻተም ሃዉሱ የፖለቲካ ተንታኝ ፖል ሜሊ ተቃዋሚዎቹ አጠቃላይ የምርጫዉ ዉጤት ከመነገሩ አስቀድመዉ ተጭበርብሯል በሚል ያወገዙበት ምክንያት ታሪካዊ ይዘት አለዉ ይላሉ።
«አንደኛዉ የጊኒ ታሪክ ነዉ። ይህ በታሪኳ ሁለተኛዉ ዴሞክራሲ መሰል ምርጫ ነዉ። እስከ 2009 እና 2010 ድረስ ጊኒ አምባገነት መንግሥት ነበረች፤ ከአምስት አሰርት ዓመታት በላይም ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ የነበራት፣ምርጫ ቢካሄድም ሙሉ በሙሉ የሚጭበረበር፤ ያን ያህል የፖለቲካ ምርጫ እንዲኖር የማይፈቅድ ነፃነት የሌለባት ነበረች።ስለዚህ በተቋማቱ ላይ እምነት ለማሳደር ሂደቱ በጣም አዝጋሚ ነዉ።»
በዚህም ላይ ይላሉ ሜሊ ፕሬዝደንት ኮንዴ ራሳቸዉ ነገሮችን አቻችሎ ለመስማማት ከመቅረብ ይልቅ ጫና የሚያደርጉም ይመስላል። የዛሬ አምስት ዓመት ከተመረጡ በኋላም መድበለ ፓርቲን የሚፈቅዱ ዓይነትም አልሆኑም። የምርጫ ኮሚሽኑ አወቃቀርም ፖለቲከኞቹን ሲያጨቃጭቅ የቆየ ጉዳይ ነዉ። ምንም እንኳን የምርጫዉ ታዛቢዎች ሂደቱን ተከታትለዉ አስተያየታቸዉን ቢሰጡም፣ እንደፖል ሜሊ አባባል፣ ምርጫ ላይ የሚፈፀመዉ ጫና አስቀድሞ የሚከናወን ነዉ።
«ታዛቢዎች በእርግጥ በምርጫዉ ወቅት የሚከናወኑ ተግባራትን እና የምርጫዉንም ቴክኒካዊ አካሄድ መከታተል ቢችሉም ምርጫ ላይ የሚፈፀም አብዛኛዉ ተፅዕኖ የሚከናወነዉ እጅግ አስቀድሞ ነዉ። የፖለቲካ ተሳታፊና እጩዎች ማግኘት የሚገባቸዉ መገናኛ ብዙሃንን መጠቀምን በተመለከተም ስልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዝደንት አልፋ ኮንዴ በጣም ሰፊና ጠንካራ ሽፋን ተሰጥቷቸዋል።»
በሀገሪቱ ራዲዮ ጣቢያዎች ሰኞ ዕለት ይፋ የሆነዉ የምርጫዉ የመጀመሪያ ዉጤት ስልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዝደንት አልፋ ኮንዴ ተፎካካሪዎቻቸዉን በሰፊ ልዩነት እንደሚመሩ አመልክቷል። የምርጫ ታዛቢዎችም ተቃዋሚዎች ምርጫዉ ተጭበርብሯል ሲሉ ያቀረቡትን አቤቱታ ወደጎን በማድረግ ተዓማኒ እንደሆነ ገልጸዋል። በሌላ በኩል ግን ምናልባት የመለያ ምርጫ ሊካሄድ ይችል ልሆናል የሚል ግምት አለ። አጠቃላይ ዉጤቱ ይፋ ከመሆኑ በፊት የቀረበዉ የታዛቢዎቹ አስተያየት ተፅዕኖ ማስከተሉ እንደማይቀር ሜሊ ይናገራሉ።
«አንደኛ ተቃዋሚዎች በተሳትፏቸዉ እንዲቀጥሉ ያደርጋል። ድጋሚ ምርጫ ማካሄድ የሚያስፈልግ ከሆነ ዋነኛዉ ተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች አንሳተፍም ለማለት አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። አልፋ ኮንዴን ድጋሚ ለመፎካከር አንሳተፍም ካሉ የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ድጋፍ እንደሌላቸዉ ያዉቃሉ።»
የዛሬ አምስት ዓመት በተካሄደዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የዋናዉ የተቃዉሞ ፖለቲካ ፓርቲ የጊኒ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት እጩ ሴሉ ዳላን ዲያሎ እና ፕሬዝደንት አልፋ ኮንዴ በድጋሚ ተፎካክረዋል። በአሁኑ ምርጫ ግን እስካሁን ግልፅ የወጣ ነገር የለም። ሰባት የተቃዋሚ ፓርቲ እጪዎች ናቸዉ የተወዳደሩት። 10,5 ሚሊዮን ሕዝብ እንዳላት የሚነርላት ጊኒ ከአንድ ዓመት በላይ በምዕራብ አፍሪቃ በኤቦላ ተሐዋሲ ክፉኛ ከተጎዱ ሃገራት አንዷ ናት።
ሸዋዬ ለገሠ
አርያም ተክሌ