1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የገና በዓል አከባበር በጀርመን

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 14 2008

በጀርመናዉያኑ ዘንድ በእጅጉ የሚከበረዉ የገና በዓል በገና ዛፍ ማለት ጥዱን አሽቆጥቁጦ፤ በገና ገበያ በቅርንፉድ ቀረፋ የተፈላዉን ወይን ይዞ፤ የገና አባት የተባለዉን ባለነጭ ሪዛም ሽማግሌን ስጦታ አሸክሞ፤ ቤተሰብን አሰባስቦ በመምጣቱ ከዓመት ዓመት በጉጉት ይጠበቃል።

https://p.dw.com/p/1HSik
Deutschland Hildesheimer Weihnachtsmarkt
ምስል picture-alliance/dpa/J. Stratenschulte

በጀርመን የገና በዓል አከባበር


በጎርጎሮሳዊው የቀን አቀጣጠር በሚከተለዉ ዓለም በድምቀት የሚከበረዉ የገና ወይም የክርስቶስ የልደት በዓል፤ ምሽት ላይ በቤተ-ክርስትያን የፀሎት ሥነ-ስርዓት ይጀምራል። በተለይ በጀርመናዉያኑ ዘንድ በእጅጉ የሚከበረዉ የገና በዓል በገና ዛፍ ማለት ጥዱን አሽቆጥቁጦ በገና ገበያ በቅርንፉድ የተፈላዉን ወይን ይዞ የገና አባት የተባለዉን ባለነጭ ሪዛም ሽማግሌን ስጦታ አሸክሞ፤ ቤተሰብን አሰባስቦ በመምጣቱ ከዓመት ዓመት በጉጉት ይጠበቃል። በእለቱ ዝግጅታችን ጀርመናዉያን የገና በዓል አከባበር እናያለን።

DW euromaxx Gänsebraten
ምስል DW


በጎርጎሮሳዊው የቀን ቀመር የሚከተሉ የክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች የገና ማለት የክርስቶስ ልደትን በዓአል በርጋታና በደስታ እያከበሩት ይገኛሉ። በጀርመን ዛሬ እስከ እኩለቀን የመንግሥት መስርያ ቤቶች፤ መደብሮች እንዲሁም በየዓመቱ በከተሞች አደባባይ ላይ የሚዘረጋዉ የገና ገበያ ክፍት ሆነዉ በየዘርፉ ደንበኞቻቸዉን ሲያስተናግዱ ነበር፤ እኩለ ቀን ላይ ግን መስርያ ቤትም ሆነ ሱቅ ተዘጋግቶ ከተሞች ሁሉ ረጭ በሉ የተባሉ ያህል ረጭ ብለዋል። የገና በዓል መሆኑን የሚያበስሩት በየሱቁ መስተዋት ላይ የተለጣጠፉት ተብለጭላጭ ጌጣ ጌጦችንና ከተማ አደባባይ የቆመዉ ረጅሙና ያሸበረቀዉ የገና ዛፍ የገና በዓል መሆኑን ማብሰራቸዉን እደቀጠሉ ነዉ። በገና በዓል ወቅት የተለመደዉና ባለሞያ ሴት የነደፈችዉ ጥጥ የሚመስለዉ በረዶ ግን ዘንድሮ እስከወድያኛዉ አልመጣም ያለ መስሎአል።

Weihnachten Selfie
ምስል DW/G. Fischer

በምትኩ ፀሃይ ሙቀትዋንም ባትሰጥም አረንጓዴ በለበሰዉ ሜዳ ላይ ብርኃንዋን ለቃ ከቤት ዉስጥ በመስኮት አጮልቆ ላያት በጋ የገባ ያህል የአየሩ ሁኔታ ያስደነግጣል። እደጅ ሲወጡ ቅዝቃዜ ቢኖርም። እዉነትም የከባቢ አየር ሙቀት ቢጨምር ነዉ እንጂ እንዲህ ያለ በዚህ ወቅት ታይቶ የማይታወቅ የአየር ፀባይ ያሰኛል። እንድያም ሆኖ በዚህ በአሁኑ ሰዓት የቤተ- ክርስትያን ደወሎች ይደወላሉ፤ ሕጻናትን ጨምሮ የተለያዩ መዘምራኖች በቤተ-ክርስትያናት አልያም በቤተሰብ ዙርያ ያዜማሉ፤ የአማላክን መወለድ ያበስራሉ።

ስለጥድ ዛፍ ከዓመት ዓመት አረንጓዴነት ፤ የገና ወቅት ጥዱ በዓሉን ማድመቁን የሚተርክ በገና ወቅት በጀርመን አገር በተደጋጋሚ የሚደምጥ የታወቀ መዝሙር ነዉ። በአብዛኛዉ ዓለም ክፍል በተለይ በምዕራባዉያኑ ዘንድ የገና በዓልን ለመቀበል ዝግጅቱ የሚጀምረዉ በዓሉ ከመድረሱ ከወራቶች አስቀድሞ ነዉ። የገና በዓል በጀርመን ሃብታም ሆነ ደሃዉ ወዳጅ ዘመዱን የሚያስታዉስበት ስጦታ የሚለዋወጥበትና ፍቅሩን የሚገልፅበት ነዉ። እናም በጀርመን የጎርጎርዮሳዊዉ አቆጣጠር ታህሳስ 24 ምሽት የገና በዓል መከበር ጀምሮአል። ኑረንበርግ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ካሱ ለገሰ በጀርመን ሲኖሩ ከ 20 ዓመት በላይ ሆንዋቸዋል፤ የሁለት ሴቶች ልጆች አባትም ናቸዉ ። ከልጆቻቸዉና ከቤተሰቦቻቸዉ ጋርም የጀርመናዉያኑን የገና በዓል በድምቀት ያከብራሉ። አቶ ካሱ የጀርመናዉያኑ የገና በዓል ታህሳስ 24 ምሽት ላይ ይጀምራል ሲሉ ስለ አከባበሩ ሂደት እንዲህ አጫዉተዉናል።

«የገና በዓል በ 24 ምሽት ላይ ነዉ የሚጀምረዉ በዚህ እለት ከቀትር በፊት የስራ ሰዓት ይሆንና ከሰዓት በኋላ መስርያ ቤቶች ሁሉ ይዘጋሉ። በዓሉ በቤተ-ክርስትያን ፕሮግራም ይጀምራል ማለት ነዉ። ልጆች ቤተሰቦች ወደ ቤተ-ክርስትያን በመሄድ መዝሙት በመዘመር የክርስቶስን መወለድ በመዝሙር ያበስራሉ፤ ያከብራሉ። መልካም ምኞትንም ይለዋወጣሉ። ቤተ-ክርስትያኑ ራሱ በተለያዩ ጌጦች አሸብርቆ የገና ዛፍ ተተክሎና ሸብርቆ ልዩ ድምቀት ይሰጣል። ቤተ-ክርስትያን ዉስጥ መዝሙር ብቻ ሳይሆን የሚዘመረዉ የክርስቶስ መወለድ ታሪክም ይነበባል፤ ይነገራል። ከዝያም ነዉ ቤተሰብ ወደየቤቱ በመሄድ ቀን የተዘጋጀ ቀለል ያለ ባህላዊ ምግብን በጋራ የሚመገበዉ።»

Bonn Ermekeilkaserne Weihnachten mit Flüchtlingen
ምስል Adelina Müller


በጀርመን በዓሉ የሚከበረዉ በአዉሮጳዉያኑ ታህሳስ 24 ምሽት ጀምሮ ሲሆን፤ በነጋታዉ ታህሳስ 25 ቀዳማዊ ገና፤ ታህሳስ 26 ቀንን ደግሞ ዳግማዊ ገና ሲሉ በተከታታይ ቀናት ከቤተሰብ ጋር እንደጀርመናዉያኑ አነጋገር በእርጋታ ያከብሩታል። ጀርመናዉያን በገና በዓል አከባበር ከሌሎች አዉሮጳዉያን የሚለዩት ደግሞ፤ ያዉ ከአራት ሳምንታት ጀምሮ በዓሉ እስከሚከበርበት እስከ ታህሳስ 24 ቀን ድረስ፤ በሚያቆሙት በገና ገበያቸዉ እና፤ በቀረፋ ቅርንፉድ በተቀመመዉ በተፈላዉ በወይን መጠጣቸዉ ነዉ። በኑረንበርግ ነዋሪ የሆኑት አቶ ካሱ በነጋታዉ በጎርጎርዮሳዊዉ ታህሳስ 25 ይላሉ በመቀጠል፤

Weihnachtsmarkt im Schloss Thurn
ምስል picture-alliance/dpa/A. Weigel


«በነጋታዉ በጎርጎርያኑ ታህሳስ 25 በጥሩና በባህላዊ ሁኔታ የተዘጋጀዉ የዳክዬ ጥብስ በጋራ ይበላል፤ በጥቅል ድንች ዓይነት ጋር በማድረግ። ልጆች ደስ ይላቸዋል። ቤተሰብ ዉስጥ ጥሩ የሆነ መንፈሳዊ ስብስብ ይደረጋል። በዚህ ቀን የሞቱ ቤተሰቦችም ይታወሳሉ። ቤተሰቦች መካነ መቃብር ጋር ሄደዉ፤ አበባ ያስቀምጣሉ ፤ ይዘምራሉ፤ እንዲህ ዓይነት የማስታወስ ባህላዊ ድርጊትም ሲፈፀም ይታያል።»

ዘንድሮ ወደ ጀርመን የገቡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ለመጀመርያ ጊዜ የጀርመናዉያንን የገና በዓል አከባበር ዝግጅቱን የገና ገበያዉና ዛፉን አይተዋል። ባለፈዉ ጥቅምት ወር አራት ልጆችዋን ይዛ በግሪክ በኩል የባልካን አገራትን አቋርጠዉ ወደ የገቡት የወ/ሮ ሃባሺህ ሴት ልጅ ሬም ሃባሺህ የገና በዓል አከባበር እንዴት እንደሆን በሶርያ ሳለች አይታለች።
«ሶርያ ዉስጥ ሳለሁ የገና በዓል በሚከበርበት ወር የሚታየዉን የሸበረቀ ገና ዛፍና የተለያዩ የገና በዓል ማሸብረቅያዎችን ለማየት እንዲሁም በዚህ በዓል ወቅት የሚጋገረዉን የተለያዩ ጣፋቶች ለመብላት ደማስቆ ከተማ ክርስትያኖች በሚኖሩበት የከተማዉ ክፍል እንሄድ ነበር። ,,, እና ገና በዓል ማለት ከቤተሰጋር በአንድ ላይ በደስታ ማሳለፍ በመሆኑ እኛም አሁን አንድ ላይ ሆነን እያከበርን እየተደሰትን ነዉ። »

የሪም ወንድም ያማን ሃባሺህ ይህን በዓል ሲከብር የሚያየዉ እሱም የበዓሉ ተካፋይ እንደሆነ ነዉ። እዚህ ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ ላይ ቢሆንም አገሩ ሶርያን መናፈቁ አልቀረም።

«እኔ ባዕድ የምገኘዉም በባዕድ አገር ነዉ። አገሪ ዉስጥ ጦርነት አለ፤ ሁኔታዉ ሁሉ ልክ እንደ አንድ ትልቅ እስር ቤት ነዉ። እንዲያም ቢሆን አገሪን እናፍቃታለሁ፤ ልቤም ይፈልጋታል።»
በኑረንበርግ ነዋሪ የሆኑት አቶ ካሱ እንደሚሉት ልጆቻቸዉ የተወለዱት እዚህ በመሆኑ ቋንቋዉን ባህሉን አጥርተዉ በማወቃቸዉና ተዋህደዉ በመኖራቸዉ ቤተሰቡ ዉስጥ የጀርመናዉያኑ የገና በዓል በድምቀት ይከበራል፤ በመቀጠል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ታህሳስ 29 እለት የሚከበረዉ የገና በዓልንም እንደ ባህሉ እንደወጉ እንደሚያከብሩ ገልፀዉልናል።
በጀርመናዉያን ዘንድ የገና በዓል አከባበር የዳሰስንበትን ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ እንዲያደምጡ እንጋብዛለን። የዓመት ሰዉ ይበለን!

Deutschland Weihnachtsbaum wird geschmückt
ምስል picture-alliance/dpa/P. Pleul


አዜብ ታደሰ


ነጋሽ መሃመድ