1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የገበሬ ሥጋት እና ተሥፋ

Eshete Bekele
ዓርብ፣ የካቲት 10 2009

ኢትዮጵያ፤ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳንን በመሳሰሉ የምስራቅ አፍሪቃ አገራት ማሽላ እና በቆሎን የመሳሰሉ ምርቶች ዋጋ ማሻቀቡን የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ገልጧል። የኢትዮጵያ ንግድ ሥራ ድርጅት የዋጋ ንረቱ የተጋነነ አይደለም የሚል ምላሽ አለው።

https://p.dw.com/p/2Xn9d
FAO, Food and Agriculture Organisation of the United Nations, Logo
ምስል AP Graphics

በሰሜን ወሎ ዞን ጉባ ላፍቶ ወረዳ ሐራ ከተማ የሚኖረው አዳነ ንጉሴ ጤፍ እና ማሽላ አምራች ገበሬ ነው። አዳነ እንደ ቀዬው ገበሬዎች ወቅቱን ጠብቆ ከዘነበ በአመት ሁለት ጊዜ ያመርታል። ታኅሳስ ላይ የጠበቁት ዘግይቶ መጣል ከጀመረ ቀናት ተቆጥረዋል። ለሚያዝያ አዝመራ በእርሻ ዝግጅት ላይ የሚገኙት እነ አዳነ ያለፈው አመት ፈታኝ ሆኖባቸው ነበር። የኤል ኒኞ የአየር ጠባይ ከተጫናቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች አንዱ ቆላማው የሐራ አካባቢ ነው።

ወቅቱ ምርት ተሰብስቦ ጎተራ የሚገባበት በመሆኑ ግብይቱ ረከስ ማለት ቢኖርበትም አልተሳካም። እነ አዳነ ምርታቸውን ለገበያ ሲያቀርቡ እንደ አሰፋፈሩ አንድ ኪሎ አሊያም ከዚያ በላይ በሚይዝ ጣሳ (መለኪያ) ይጠቀማሉ። አዳነ አንድ ኩንታል ነጭ ጤፍ 2,400 ብር ማሺላ (ደጋሌትና ጃምዮ) በኩንታል 1200 ብር፤ ነጭ ማሺላ ወይም ጅርጉቴ በኩንታል ከ900 እስከ 1,000 ብር እየተሸጠ መሆኑን ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።

የበልግ ማሳ በሚዘገጃጅበት የመርሳ አካባቢ የሚኖሩት አቶ ሙባረክ የጤፍ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ይናገራሉ። ልብአርጋቸው አያሌው የሚኖርበት ሞረት እና ጅሩ ወረዳ ስንዴ፤ማሽላ እና ዘንጋዳ ያመርታል። አካባቢው ይበልጥ የሚታወቀው ግን በምሥር አምራችነቱ ነው። በአካባቢው ገበሬዎች ተመራጩ ጥቁር ምስር በገበያ ቅናሽ አሳይቷል። 3,600 ብር የነበረው አንድ ኩንታል ጥቁር ምስር ወደ 2,800 ብር ሲቀንስ ነጭ 2,200 አካባቢ ይሸጣል። ልብአርጋቸው እንደሚለው በሞረት እና ጅሩ ገበያ ስንዴ ሲቀንስ ጤፍ ግን ተወዷል።

Sudanesische Bäuerin reinigt ausgedroschene Sorgum-Körner
ምስል picture-alliance/dpa

ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪቃ አገራት በቆሎ እና ማሽላን የመሳሰሉ የምግብ አዝርዕት ላይ የዋጋ ንረት መከሰቱን የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ባለፈው ማክሰኞ አስታውቋል። በዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ፤ኬንያ፤ሶማሊያ፤ደቡብ ሱዳን እና ታንዛኒያ የምግብ አዝርዕት ዋጋ በአንዳንድ ገበያዎች በእጥፍ ጨምሯል። የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የእህል እና ቡና ንግድ ሥራ ዘር የእቅድ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ገብረእግዚአብሄር አባይ የኤል ኒኞ የአየር ጠባይ ጫና ባሳደረባቸው አካባቢዎች የዋጋ ንረት መስተዋሉን ይስማማሉ።

ኤል ኒኞ የተሰኘው የአየር ጠባይ የፈጠረው ድርቅ እና በቅርብ ወራት ውስጥ የታየው በቂ ያልሆነ እና ያልተመጣጠነ ዝናብ ሰብል ማውደማቸው አሁን ለተፈጠረው የግብይት ዋጋ ማሻቀብ መነሾ ናቸው ተብሏል። የሐራው ገበሬ አዳነ ንጉሴ መጪው ደረቃማ ወቅት ሥጋት ፈጥሮበታል።

 

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ