1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጅቡቲው ፕሬዝዳንት በድጋሚ ተመረጡ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 1 2008

የጅቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማዔል ኦማር ጉሌህ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫውን በሰፊ ልዩነት አሸነፉ። ተቃዋሚዎቻቸው እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ምርጫው ፖለቲካዊ አፈና መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በተንሰራፋበት ሁኔታ የተካሄደ ነው ብለው ቢተቹም፤ ጉሌህ 87 ከመቶ የሚጠጋ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸውን የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

https://p.dw.com/p/1ISd9
Dschibuti Ismael Omar Guelleh Präsident
ምስል picture-alliance/dpa/R.Drew
Dschibuti spanisches Kriegsschiff im Hafen
ምስል Getty Images/AFP/C. De Souza

«ለአገሪቱ ከፍተኛ ሥልጣን የጅቡቲ ዜጎች በእኔ ዳግም እምነት አሳድረዋል።» ያሉት የ68 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ኦማር ጉሌህ «ነገውኑ ወደ ሥራ እገባለሁ።» በማለት ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ ለምርጫ የቀረቡት ከተዳከሙ እና ከተበታተኑ ተቃዋሚዎች ጋር የነበረ በመሆኑ ለአራተኛ የሥልጣን ዘመን እንደሚያሸንፉ ተገምቶ ነበር። በተቃዋሚዎች ኅብረት ውስጥ ከተካተቱት 7 ፓርቲዎች ሦስቱ ራሳቸውን ከምርጫው አግለዋል።

ከአጠቃላይ የጅቡቲ ዜጎች መምረጥ የሚችሉት 187,000 ያክሉ መሆናቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል። ከተፎካካሪዎች መካከል ለጉሌህ የቀረቡት ተቃዋሚ ሰባት በመቶ ብቻ ድምጽ ማግኘታቸው ተጠቅሷል። የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደዚህ ቀደም የጅቡቲ ምርጫዎች መራጮች ድምጽ እንዳይሰጡ ጥሪ ቢያቀርቡም ከተመዘገቡ ዜጎች መካከል 68 በመቶው ድምጽ መስጠታቸው ተሰምቷል። ፕሬዝዳንት ኢስማዔል ኦማር ጉሌህ ምርጫውን እንደሚያሸንፉ እርግጠኛ እንደነበሩም ተናግረዋል። በአጠቃላይ 875,000 ነዋሪ ያላት ጅቡቲ ኅልውናዋ ከተመሰረተበት ወደቧ ብዙም የማትሰፋ አነስተኛ ሀገር ናት።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ