1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ፕሬዝዳንት ሥልጣን መልቀቅና አፍሪቃ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 24 2002

አምባሳደር ሲራጅ ረሺድ ዛሬ ለዶቸ ቬለ እንደገለጡት ፕሬዝዳት ሆርስት ከለር የአፍሪቃና የጀርመንን በተለይም የኢትዮጵያና የጀርመንን ግንኙነት ለማጠናከር አበክረዉ የጣሩ መሪ ነበሩ።

https://p.dw.com/p/Neyl
ከለርምስል AP

01 06 10 የጀርመኑ ፕሬዝዳት ሆርስት ከለር ብዙም ሳይጠበቅ ትናንት ሥልጣን መልቀቃቸዉ ለብዙዎቹ የአፍሪቃ መንግሥታት አስደንጋጭ ነዉ የሆነዉ።የተለያዩ የአፍሪቃ ሐገራት ባለሥልጣናት እንዳሉት ፕሬዝዳት ከሕለር ሥልጣን መልቀቃቸዉ አፍሪቃን አንድ ወዳጅ አሳጥቷታል።ፕሬዝዳት ሆርስት ከለር የአለም ገንዘብ ድርጅት (IMF) ዋና ሥራ-አስኪያጅ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ አፍሪቃን ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸዉ ይነገርላቸዋል።ነጋሽ መሐመድ የፍሪቃዉያኑን አስተያየት አሰባስቧል። የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF-በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) የበላይ ሐላፊ በነበሩበት ዘመን ምዕራብ አፍሪቃን ከጎበኙበት ጊዜ ጀምሮ-የሚያዉቁ እንደሚሉት የአፍሪቃና የአፍሪቃዉያን ጉዳይን ዘንግተዉት አያዉቁም።ለአፍሪቃ የመቆርቆር-ማዘናቸዉ ምክንያት ሁለት ነዉ።እንደ ሰዉ-ሰአብዊነት-እንደ ምጣኔ ሐብት-ፖለቲካ አዋቂ ደግሞ-የበለፀገዉ አለም አፍሪቃን ጥሎ-እንደበለፀገ አይቀጥልም የሚል እምነት-ሁለት። ከለር ከአለም የሰወስተኛዋ ባለኢንዱስትሪ ሐብታም ሐገር ፕሬዝዳት ሲሆኑ አፍሪቃን የመርዳት ፍላጎት ምኞታቸዉን የሚያስፈፅሙበት ድርጅት ወይም ማሕበርን መሠረቱ። ወዳጅነት ከአፍሪቃ ጋር አሉት ስሙን።አፍሪቃዉያን ችግረቻቸዉን ለማቃለል-በጋራና በተናጥል የሚያደርጉት ጥረት ለጀርመኑ ፕሬዝዳት ከእንግዲሕ የቀድሞ ነዉ የሚባሉት አላማ-ምኞት ስኬት ጥሩ ጀምር አይነት ነበር። «በአፍሪቃ ሐገራት የሲቢል ማሕበረሰብ በመመስረት ላይ ናቸዉ።ብዙ ሰዎች አሁንም መፃኤ እድላቸዉን ለመወሰን ገና ዝግጁ አይደሉም።ገበሬዎች በጋራ ዘር የሚሸምቱበት፥ምንጭ የሚያጎለብቱበት፥ ዜጎች ሙስናን የሚዋጉበት፥መግንስታቸዉን የሚከታተሉበት፥ ሴቶች ትምሕር ቤቶች እንዲሠሩ፥ የኤድስ ሕሙማን የሚታከሙበት ማሕበራት ማሕበራት መመስረት አለባቸዉ። አፍሪቃዉያን የራሳቸዉን ችግር ራሳቸዉ ለማቃለል የሚያደርጉትን ጥረት የአፍሪቃ ሙሕራን፥ ፖለቲከኞችና ታዋቂ ሰዎች እንያግዙ ከለር ብዙ ጥረዋል።የአፍሪቃ መሪዎችንና ታዋቂ ግለሰቦች ጀርመን ድረስ ጋብዘዉ አነጋግረዋል።የተለያዩ የአፍሪቃ ሐገራትን ጎብኝተዋል።አንዷ ቤኒን ነበረች።የቤኒን መንግሥት ቃል አቀባይ ቪክቶር ቶፓኖዉ ከለር ወዳጃችን ነበሩ አሉ-ትናንት። «ፕሬዝዳት ከለር የአፍሪቃ በተለይ ደግሞ ከዚሕ ቀደም የጎበኟት የቤኒን ታላቅ ወዳጅ ናቸዉ።ከሳቸዉ ጋር ጥሩ የትብብር ወዳጅነት አዳብረናል።ባሁኑ ወቅት ስልጣናቸዉን በመልቀቃቸዉ በጣም አናዝናለን።» ከሳቸዉ በፊት የነበሩ የጀርመን ፕሬዝዳቶች አድርገዉት በያዉቁት መንገድ በጦርነት፥ በሙስና በረሐብና በሽታ የሚማቅቀዉ አፍሪቃዊ ለመርዳት ብዙ ጥረዋል።በዚሕም ሰበብ የጀርመን መገናኛ ዘዴዎች «የአፍሪቃ ፕሬዝዳት» በሚል ቅፅል እስከ መጥራት ደርሰዉም ነበር።ፕሬዝዳንትቱ ብዙ ሳይጠበቅ ትናንት ሥልጣን መልቀቃቸዉን የታንዛኒያ ምክር ቤት የዉጪ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀመንበር ዊልሰን ማስሊንጊ አስደንጋጭ ብለዉታል። «አስደንጋጭ ነዉ።ለኔ በጣም አስደንጋጭ ነዉ።የተከበሩ ፕሬዝዳት ከለር ያታንዛኒያ ወዳጅ ነበሩ።የመላዉ አዳጊ ሐገራት ወዳጅ ነበሩ።---ሥልጣናቸዉን መልቀቃቸዉን ስሰማ በጣም ነዉ የደነገጥኩት።» ሆርስት ከለር ሕዳር 1998 እዚሕ ቦን ባስተናገዱት የአፍሪቃ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከተካፈሉት አንዱ የቀድሞዉ የናጀሪያ ፕሬዝዳት ኦሌ ሼጎን ኦባሳንጆ ከለርን «የአፍሪቃና የምዕራቡ አለም አገናኝ ድልድይ» አይነት ብለዋቸዉ ነበር።የናጄሪያዉ ምክትል ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አልዩ ኢዲ ሆንግ ደግሞ ትናንት አንድ ወዳጅ አጣን አሉ። «ይሕ ይሆናል ብለን ላልጠበቅነዉ ለሁላችንም አስደንጋጭ ነዉ።ያለፈዉን የሥራ ልምዳቸዉን እና ከአፍሪቃ ጋር ያላቸዉን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ለምናዉቀዉና የአፍሪቃን ጉዳይ ከልብ የሚያስተናግዱበትን መንገድና ብልሐት ለምንረዳዉ በርግጥ እኛ ሁላችንም አንድ ወዳጅ ያጣን ይመስለኛል።» ---------------------------- ኢትዮጵያም በጀርመኑ ፕሬዝዳት ሆርስት ከለር ሥልጣን መልቀቅ አንድ ታላቅ ወዳጅ ያጣች ያክል እንደሚሰማት በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር አስታዉቀዋል።አምባሳደር ሲራጅ ረሺድ ዛሬ ለዶቸ ቬለ እንደገለጡት ፕሬዝዳት ሆርስት ከለር የአፍሪቃና የጀርመንን በተለይም የኢትዮጵያና የጀርመንን ግንኙነት ለማጠናከር አበክረዉ የጣሩ መሪ ነበሩ።

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ