1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የጥገኝነት ሕግ የገጠመዉ ጫና

ረቡዕ፣ መስከረም 26 2008

የጀርመን የጥገኝነት መብት አሠራር ከሌላዉ ዓለም በጣም የተለየ ነዉ። እናም አንዳንዶች ለዚህ ነዉ አሁን ከፍተኛ ጫና ሀገሪቱ የገጠማት የሚል መከራከሪያ ያነሳሉ። የጥገኝነት መብት አሰጣጡ እንዴት ነበር የተቀረጸዉ? እንዳለስ ይቀጥላል ወይ? ይህን በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ።

https://p.dw.com/p/1Gk8S
Deutschland Flüchtlinge in Berlin
ምስል picture alliance/dpa/B. von Jutrczenka

[No title]

በጀርመን ሕገመንግሥት አንቀፅ 16 መሠረት በፖለቲካ ክስ የሚሳደድ ግለሰብ ጥገኝነት የማግኘት መብት አለዉ። ይህን የሚያስለዉጥ ምንም ምክንያታዊነት አይኖርም። የሃምበርግ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ምሁር ራይንሃርድ ሜርክል እንደሚሉት ደግሞ ለእዉነተኛ ተሰዳጆች ትክክለኛዉን የጥገኝነት መብት ከሚያጎናፅፉ እጅግ ጥቂት ከሆኑት ሃገራት መካከል ጀርመን አንዷ ነች።

«እኔ እስከማዉቀዉ ድረስ ምናልባት ጀርመን ብቻ ናት ማለት ባይቻልም፤ ለጥገኝነት ጠያቂዎች መሠረታዊ መብትን ሙሉ በሙሉ ከሚያከብሩ ከጥቂቶቹ ሃገራት አንዷ ናት። በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 16 የተጠቀሰዉ ለጀርመናዊ ሳይሆን የዉጭ ዜጋን የሚመለከት ነዉ። »

ይህም በሁለተኛዉ ጦርነት ወቅትና እሱም ካለፈ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በተከሰተዉ የጅምላ ስደትና መፈናቀል ሲከሰት የተደነገገ ነዉ። የፌደራል ሪፑብሊክ ጀርመን የጥገኝነት አሰጣጥ ሕግ ከመላዉ ዓለም ጋር ሲነፃፀር እጅግ ቸር ነዉ። በጎርጎሪዮሳዊዉ 1993ዓ,ም በመጠኑ እስኪሻሻል ድረስም የጥገኝነት መብት ገደብ አልባ ሆኖ ቆይቷል።

Deutschland Registrierung von Flüchtlingen
ለምዝገባ ከተሰለፉ ጥገኝነት ጠያቂዎች በከፊልምስል DW/R. Fuchs

በንፅፅር እጅግ ጥቂት ሰዎች የፖለቲካ ጥገኝነት ይጠይቁ ስለነበርም ፖለቲካዉም ሆነ ማኅበረሰቡ ችግር አልነበረበትም። ሆኖም ግን በዩጎዝላቪያ ጦርነት ጊዜ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ዓመታት በድንገት በመቶዎችና ሺዎች የሚገመቱት ወደ ጀርመን ተሰደዱ። በጥገኝነት ፈላጊዎች መኖሪያ ላይም ጥቃት ተሰንዝሮ ነበር። በወቅቱም በተካሄደ መጠይቅ አማካኝነት ሶስት አራተኛ የሚሆነዉ ጀርመናዊ የጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር መቀነስ እንደሚኖርበት ጠየቀ። ጠንካራ ፖለቲካዊ ክርክር ከተካሄደ በኋላም ክርስቲያን ዴሞክራት፣ ክርስቲያን ሶሻል ኅብረት እና ነፃ ዴሞክራት ፓርቲ ጥምረት በጋራ ከተቃዋሚዉ ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ ጋር ከአንድ ስምምነት ደረሱ። ይህም የፖለቲካ ጥገኝነት መስጠት የሚል ነዉ። ይህ በሕጉ ላይ ወሳኝ ማሻሻያ ነበር። ለፖለቲካ ስደተኛ ሶስተኛ አማራጭ ሀገር መሆን። ይህ ደግሞ የጀርመን ጎረቤት ሃገራትንም ይመለከታል። በዚህ መሠረታዊ ለዉጥ ምክንያትም ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1993ዓ,ም ወዲህ ጀርመን ዉስጥ የጥገኝነት ጠያቂዉ ቁጥር እጅግ ቀንሷል። የዛሬ ስምንት ዓመት ጀርመን ዉስጥ ጥገኝነት የጠየቀዉ ብዛት ከ20,000 ቀንሶ ታይቷል።

በአሁኑ ጊዜ በሁለትና ሶስት ቀናት እጅግ በርካታ ስደተኞች ያለ ቁጥጥር ወደ ጀርመን ይገባሉ። የየፌደራል መንግሥቱ ባለስልጣናትም የሚገቡት ሰዎች ቁጥር እና ከየትስ ሀገር መጡ የሚለዉን አያዉቁትም። የቀድሞዉ ሕግ ያልሠራበት ምክንያቱ ግልፅ ነዉ፤ አንዳንድ የአዉሮጳ ኅብረት ጎረቤት አባል ሃገራት ስደተኞቹን መዝግበዉ የጥገኝነት ማመልከቻቸዉን በማየት አስፈላጊዉን ርምጃ ከመዉሰድ ይልቅ የቀድሞዉን የኅብረቱን መመሪያ በመተዉ ወደፈለጉበት እንዲሄዱ በመልቀቃቸዉ ነዉ። ጀርመን ሰዎቹን ወደመጡበት የመመለስ መብቱ አላት፤ ነገር ግን ከፖለቲካ እና ሞራል አኳያ አላደረገችዉም። በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ የፌደራል ጀርመን መንግሥት እየበረከተ የመጣዉ የስደተኛ ጎርፍ በፈጠረበት ጫና ምክንያት ከኦስትሪያ ጋር በመተባበር ለጊዜዉ ድንበር ላይ ቁጥጥር እንዲካሄድ ወስኗል። ያም ሆኖ ስደተኞች ድንበር አልፈዉ መግባት ይችላሉ። አንድ የጀርመን ክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፖለቲከኛ ግን የሀገሪቱ የጥገኝነት ሕጉ ይበልጥ እንዲጠብ ካልሆነም ቤተሰብ የማዋሃጃዉ ደንብ ገደብ እንዲደረግበት ጠይቀዋል። ይህ ከሕግ አኳያ አስቸጋሪ ነዉ። ያም ቢሆን ግን ግልፅ የፖለቲካ ጥገኝነት ፈላጊ ወይም ከእርስ በርስ ጦርነት የሸሸ ስደተኛን ለመቀበል የማቆያ ስፍራም ይሁን የገንዘብ አቅም የጥገኝነት ጠያቂዉ መጠን ገደብ እንዲረግበት ያስገድዳል። አንዳንዶችም በስደተኛዉ መብዛት ባህል እሴታችን ይበረዛል ፤ብሎም ይጠፋል የሚል ስጋት ማሰማት ጀምረዋል። ጀርመን የስደተኛ አቀባበልና የጥገኝነት አሰጣጧ ላይ ለዉጥ ታድርግ ለሚለዉ ሕዝበ ዉሳኔ መሰጠት ያስፈልግ ይሆን? የሕግ ምሁሩ ራይንሃርድ ሜርክል ይህ አስቸጋሪ ሥራ እንደሚሆን ይገምታሉ።

Deutschland Bundestag Asylrechtsänderung Gregor Gysi
የጀርመን ምክር ቤት በሕጉ ላይm ሲመክርምስል Reuters/A. Schmidt

«ይህ በጣም ከባድ ከሆኑ ጥያቄዎች አንዱ ነዉ። የፖለቲካ ፍልስፍናዉ እና ሕገ መንግሥቱ የተደባለቀበት ነዉ። ማለት የሚቻለዉ በአሁኑ ጊዜ የሚታየዉ ሕጉ በሚፈቅደዉ መሠረት ነዉ። የጀርመን መንግስትም ሆነ የጀርመን ምክር ቤት በተሰጠዉ የሕግ ማዕቀፍ እንደ ሕግ አዉጭ አካል ሕዝበ ዉሳኔም ሳይካሄድ ሊያደርገዉ ይችላል። መሠረታዊ እና ዴሞክራሲያዊ መመሪያዉንም እጅግ ግልፅ አድርጎ ማሳየት ይኖርበታል።»

Deutschland Dresden Pegida Demonstration
የስደተኞችን መበርከት የተቃወመዉ የፔጊዳ ሰልፍምስል picture-alliance/dpa/B. Settnik

ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የዩሮ ሸርፍን የሚቃወመዉ የጀርመን አማራጭ ፓርቲ/AfD/ ነፃ ነዉ ያለዉ የሀገሪቱን የጥገኝነት ሕግ ለመቃወም በዛሬዉ ዕለት ማምሻዉን ኤርፉርት ከተማ ላይ ሰልፍ ለማካሄድ ተዘጋጅቷል። የሰልፉ ተሳታፊዎች ቁጥር ባይገለፅም የተለያዩ የኒዮ ናዚ ቡድኖች እንደሚገኙ ማመላከታቸዉ ተሰምቷል። ከሁለት ዓመታት በፊት የተመሠረተዉ AfD ከተለያዩ ሃገራት የተሰደዱ ጥገኝነት ጠያቂዎች ጀርመንን ያጥለቀለቋት በዚህ ሕግ ምክንያት ነዉ የሚል አቋም አለዉ። የስደተኞቹን መበርከት ተከትሎም በየመጠለያ ጣቢያዉ በተለያዩ ምክንያቶች በመካከላቸዉ የሚነሳዉ ግጭት እና የሚደርሰዉ ጉዳት የሃገሪቱን መገናኛ ብዙሃንና ዜጎችን ቀልብ እንደያዘ ነዉ።

ክሪስቶፍ ሃሰልባህ/ ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ