1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የበጀት ክርክር

ዓርብ፣ ግንቦት 10 2010

የጀርመን ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበጀት ጉዳይ ከሰሞኑ መክሯል። በክርክሩ ወቅት የአውሮጳ የልማት ፖሊሲ ስኬታማ እንዳልሆነ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለልማት ርዳታ የሚመደበው ገንዘብም ስደትን እንዳላስቆመ ተጠቅሷል። በዚህ ምክንያትም ለልማት የሚደረገው ርዳታ አዲስ መልክ ሊይዝ ይገባል የሚል ሃሳብ አቅርቧል።

https://p.dw.com/p/2xwel
Bundestag - Plenarsitzung  zum Bundeshaushalt - Angela Merkel und Olaf Scholz
ምስል Getty Images/AFP/T. Schwarz

የልማት ርዳታ አጠቃቀምና ስልት ትኩረት ይሻል

የስደተኞች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት መጨመርአውሮጳን በጥቅል ጀርመንን ደግሞ በግል ዛሬም ከማሳሰብ አልቦዘነም። በልማት ስም ርዳታ ከሚቀበሉ የአፍሪቃ ሃገራት የሚሰደዱት ወጣቶች ጉዳይ አሁንም መነጋገሪያ ነው። የጀርመን ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማለትም ቡንደስታኽ ስለቀጣይ በጀት ጉዳይ ሲከራከር የልማት ርዳታ እና ያላባራውን የስደተኞች ፍልሰት አንስቶ ተከራክሯል። ስለጥገኝነት ፈላጊዎች ጉዳይ በተነሳ ቁጥር ጀርመን ውስጥ በአንድ ወቅት ስደተኞች በርከት ብለው እንዲገቡ ፈቅደዋል በሚል በፖለቲከኞች የሚወቀሱት መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልም ለዚህ መፍትሄ ይሆናል ያሉትን ሃሳብ አቅርበዋል።

«የአዉሮጳ ሁለተኛው ትልቅ ተግባር ስደተኞችን እንዴት መቆጣጠር እና መያዝ ይቻላል የሚለውን ጥያቄ ነው። ይህም ነው ለቀጣይ ዓመታት ወጥሮ የሚይዘን፤ ከሶርያ ጋር ተጎራብተን ለአስርት ዓመታት ነው የምላችሁ፤ ለዚህም ነው እንደአዉሮጳ የጋራ የጥገኝነት ስርዓት እንዲኖረን መሥራታችን ትክክል የሚሆነው። ስለዚህም ፍሮንቴክስን ማቋቋማችን ትክክል ነበር፤ ግን ደግሞ 600 ፖሊሶች ብቻ ባሉት ፍሮንቴክስ ሰፊዉን የአውሮጳ የውጭ ድንበር ከዳር እስከዳር መጠበቅ አይቻልም። ስለዚህ ለወደፊት ፍሮንቴክስን ማጠናከር እና ተገቢዉንም መሣሪያ ባግባቡ ማቅረቡ ትልቁ ሥራ ይሆናል።»

ጀርመንም በዚህ በኩል የበኩሏን አስተዋፅኦ እንደምታደርም ለምክር ቤቱ አባላት አስረግጠው ተናግረዋል ሜርክል።  ሰዎች እንዲሰደዱ የሚያደርጋቸው የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ነው የሚለው እምነት ባጠላበት በዚህ ክርክር አዲስ የልማት ርዳታ ስልት መቀየስ ያስፈልጋል የሚለው ነጥብ ጎልቶ ተሰምቷል።  ዜጎች ለሚሰደዱባቸው ሃገራት አውሮጳም ሆነ ሀገራቸው የሚሰጡት የልማት ርዳታ ስደትን በመቀነሱ ረገድ ውጤት አላመጣም የሚሉት ሜርክል ከእርዳታው ይልቅ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትን ማጠናከር እንደሚበጅ ተናግረዋል። እንዲያም ሆኖ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የአውሮጳ የልማት ፖሊሲ ሁል ጊዜም ስኬታማ ስለማይሆን ለአፍሪቃ ልማት ይህ ነው የሚባል አስተዋፅኦ እንዳላደረገ ጠቁመዋል። በተለይም ለተሰዳጆች የሰብዓዊ ርዳታ ለማቅረብ በሚደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት በረድኤት ማቅረቡ ተግባር የተሰማሩ የተመድ የተለያዩ ድርጅቶች የበጀት እጥረት ገጥሟቸው መታየቱንም አንስተዋል። በዚህ ምክንያት ለምሳሌ በዮርዳኖስ ለሚገኙ ተሰዳጆች የምግብ አቅርቦት በመስተጓጎሉ ሰዎች ወደሌላ አካባቢ እንዲሰደዱ ማስገደዱንም ጠቅሰዋል። 

Niger Eröffnung der Angela-Merkel-Schule in Niamey
ምስል DW/A. Mamane Amadou

«የተመድ የእርዳታ ድርጅቶችን በጀት ስንመለከት፤ እውነቱን መረዳት እንችላለን፤ ምንም እንኳን እኛ ብዙነገሮችን ብናደርግም በዓለም አቀፍ ደረጃ ግን በሚያስገልገው መጠን የተደረገ ነገር የለም። የUNHCRም ሆነ የዓለም የምግብ መርሃግብር በጀቶችን ጨምሮ በአስደንጋጭ መልኩ በቂ አይደለም፤ ለዚህም በሄድንበት ሁሉ ድምጻችንን ከፍ አድርገን መናገር ይኖርብናል፤ ለሰብዓዊ ርዳታዎቹም የራሳችንንም አስተዋፅኦ ማድረግም አለብን።»

«እኔ አይደለም እላለሁ፤ ምክንያቱም የተለመደው የልማት ርዳታ ብቻውን በቂ አይደለም፤ ስለዚህ በኤኮኖሚው ረገድ አፍሪቃ ውስጥ ይበልጥ የብድር ስልትን አስተካክለን ተጨማሪ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ማድረግ የምንችልበትን መንገድ ማሰብ ይኖርብናል። በዚያም ላይ ቮልፍጋንግ ሾይብለ በቡድን ሃያ የፕሬዝደንትነት ዘመን እንዳደረጉት ኮምፓክት አፍሪቃ የተሰኘውን ማዕቀፍ በተሻለ መንገድ በመጠቀም እና የተሻለ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ከባቢን መፍጠር ያስፈልጋል። አለበለዚያ ጓዲት እና ጓዶች የመንግሥት የገንዘብ ድጎማም ሆነ የኤኮኖሚ ልማት ብቻውን የትም አያደርስም። » 

ይህ ሲባል ግን አሉ ሜርክል የልማት ርዳታን ከሰብዓዊ ርዳታ ጋር ማቀላቀል ወይም አንዱን በሌላው መተካት ማለት አይደለም። ይልቁንም የምንሰጠው የልማት ርዳታ እና የምንጠቀመው ስልት የሚፈለገውን ውጤት ለማስገኘት በቂ ነወይ ብለን መጠየቅ አለብን ብለዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ