1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር የአፍሪቃ ጉብኝት

ቅዳሜ፣ የካቲት 14 2007

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር፣ ምንም እንኳን እልባት ላልተገኘለት የዩክሬይን ቀውስ መፍትሔ በማፈላለጉ ጥረት ቢጠመዱም፣ በማዕከላይ እና በምሥራቅ አፍሪቃ የአራት ቀናት ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

https://p.dw.com/p/1EfG3
Kongo Steinmeier Joseph Kabila Kabange
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

ሽታይንማየር ሊሰርዙት ባልፈለጉት አራተኛው የአፍሪቃ ጉዟቸው ባለፈው ሀሙስ ከጎበኙዋት ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ጎን ርዋንዳን እና ኬንያንም ይጎበኛሉ።« በአውሮጳ በወቅቱ ለሚታዩ ችግሮች መፍትሔ የማፈላለጉ ጥረት ሙሉ ትኩረታችንን ቢጠይቅብንም፣ ጎረቤታችን ለሆነው አህጉር፣ ማለትም ለአፍሪቃ አስፈላጊውን ትኩረት ልንሰጠው ይገባል። »

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር በአራተኛው የአፍሪቃ ጉዟቸው በመጀመሪያ ከጎበኙዋት ዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላ እና ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት ወቅት ነበር ቀደም ሲል ባዳመጣችሁት አነጋገራቸው ሀገሪቱ፣ በተለይ ውዝግብ የሚታይበትን ምሥራቃዊውን ከፊል ለማረጋጋት በምታደርገው ጥረቷ ላይ የጀርመን ርዳታ ፣ ድጋፍ እንደማይለያት ያረጋገጡት። በዚሁ አካባቢ ሚሊሺያዎች እና ዓማፅያን በማዕድን የተፈጥሮ ሀብት የታደለውን አካባቢ ለመቆጠጠር ካለፉት ሁለት አሠርተ ዓመታት ወዲህ ውጊያ በማካሄድ ላይ ናቸው፣ አካባቢውን ለማረጋጋት የተመድ 20,000 ወታደሮች የተጠቃለሉበት ሰላም አስከባሪ ጓድ አሠማርቷል። ሽታይንማየር በዚሁ ጊዜ የኮንጎ ባለሥልጣናት ነፃና እና ዴሞከራሲያዊ ምርጫ እንዲያካሂዱም አክለው አሳስበዋል። የኮንጎ ፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላ በ2011 ዓም ድጋሚ የተመረጡበት ሂደት ኢዴሞክራሲያዊ እና ትክክለኛ አልነበረም በሚል ብዙ ወቀሳ እንደተፈራረቀባቸው የሚዘነጋ አይደለም።

ወጣቱ የኮንጎ ትውልድ ጀርመናዊው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ከሀገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ያደረጉትን ውይይት በቅርብ ተከታትሎታል። ምክንያቱም፣ ጀርመንን እንደ ትልቅ የኤኮኖሚ ኃይል ብቻ ሳይሆን ፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አራማጅም ጭምር አድርጎ ነው የሚመለከተው። ሽታይንማየር በኮንጎ ቆይታቸው ከሲቭሉ ማህበረሰብ፣ ከአብያተ ክርስትያን እና ከመንግሥቱ ተቃዋሚዎች ጋር ተገናኝተው ሀሰብ መለዋወጣቸው የወጣቱን ትፅቢት አሟልቷል። የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላ ፓርቲ የምርጫውን ሕግ ለመቀየር ባለፈው ጥር ወር ሙከራ ካደረገ ወዲህ በተለይ ብዙዎቹ ወጣቶች በፕሬዚደንቱ ላይ እምነት አጥተዋል። የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ መንግሥት በሀገሩ ይደረጋል ከሚባለው ምክር ቤታዊ እና ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በፊት በምትባለው ውስጥ የሕዝብ ቆጠራ እንዲደረግ አቅርቦት የነበረው ሀሳብ ደም አፋሳሽ ተቃውሞ ከቀሰቀሰ በኋላ መሰረዝ ግድ ነበር የሆነበት። በተቃዋሚ ቡድኖች አስተሳሰብ መሠረት፣ ይህ ዓይነቱ ግዙፍ ፕሮዤ ከ 70 እስከ 80 ሚልዮን ሕዝብ ይኖርባታል በምትባለው እና የተንኮታኮተ መሠረተ ልማት ያላት ሀገር ውስጥ ከአንድ ዓመት በላይ ሊወስድ ስለሚችል፣ ምርጫው ወደሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ምክንያት ይፈጥራል። ተቺዎች ይኸው ፕሮዤ በተዘዋዋሪ መንገድ የፕሬዚደንት ካቢላን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም የታቀደ አድርገው ተመልክተውታል። የመንግሥቱ ፀጥታ ኃይላት ዕቅዱን በመቃወም አደባባይ በወጡት ላይ በወሰዱት የኃይል ርምጃ 42 ሰዎች ሲገደሉ፣ በርካቶች ቆስለዋል። ፕሬዚደንት ካቢላም ኢንተርኔትን እና ማህበራዊውን የመገናኛ ብዙኃን መረቦችንም አግደዋል፣ አገልግሎቱ እስካሁንም ከሞላ ጎደል እንደተቋረጠ ነው። የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋም ላላቸው ዊሊ ማንዛምቢ እንደሚሉት፣ ይህ ሀገሪቱን የሚጎዳ ርምጃ የካቢላ ዘመን እንዳከተመለት የሚጠቁም ነው።

Kongo Unruhen in Kinshasa
ምስል Reuters/N'Kengo

« ካቢላ ትክክለኛ ምርጫ የሚካሄድበትን ሁኔታ ማመቻቸት እና ቦታቸውን መልቀቅ አለባቸው። ካሁን በኋላ ሥልጣን ላይ እንዲቆዩ አልፈልግም። ያለፉት 15 ዓመታትን ሥልጣን ላይ ናቸው፣ ስለዚህ ይበቃቸዋል ባይ ነኝ። »

ደም አፋሳሹን ግጭት ተከትሎ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ላዕላይ ምክር ቤት አከራካሪውን ረቂቅ ሕግ ከሻረ በኋላ፣ የሀገሪቱ አስመራጭ ኮሚሽንም የምርጫውን የጊዜ ሰሌዳ ይፋ አድርጓል፤ በዚሁ ሰሌዳ መሠረትም፣ ምክር ቤታዊው እና ፕሬዚደንታዊው ምርጫ እአአ ህዳር 2016 ዓም እንዲካሄድ ተወስኗል። ውሳኔውን ጀርመናዊው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሞግሰዋል።

« የምርጫውን የጊዜ ሰሌዳ በይፋ የወጣበትን ድርጊት በደስታ ተቀብለናል። ምርጫው በሰላማዊ መንገድ የሚካሄድበት በምርጫው የሚወዳደሩት ዕጩዎች እና ፓርቲዎች በእኩልነት የሚታዩበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ተስፋ እናደርጋለን። »

ይህ የጀርመናዊው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ተስፋ ግን ገሀድ መሆኑን ብዙ የዴሞክራቲክ ሬፓብሊክ ዜጎች እንደሚጠራጠሩት በማስታወቅ፣ ቀጣዮቹ ወራት ጠንካራ የፖለቲካ ውጥረት የሚታይባቸው እንደሚሆኑ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

Konfliktfreie Kalimbi-Mine Kongo
ምስል DW/J. van Loon

22 ጀርመናውያን ባለተቋማትን ይዘው የተጓዙት ሽታይንማየር በዚሁ ጉብኝታቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል የኤኮኖሚውን ግንኙነት ለማሻሻል ጥረት እንደሚያደርጉ ነው ያስታወቁት። ኮንጎ ለጀርመንበንግዱ ግንኙነት አኳያ 109ኛ ቦታ ላይ ነው የምትገኘው። ጀርመን በተፈጥሮ ሀብት ወደታደለችው ኮንጎ በ2012 ዓም 129 ሚልዮን ዩሮ የሚያወጣ ዕቃ ብቻ ነበር በንግድ የላከችው። ሽታይንማየር ከኮንጎ አቻቸው ጋር ከተገናኙ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሁለቱ ሀገራት በልማቱ እና በንግዱ ዘርፍ ይበልጥ የመቀራረብ ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ ዕድሉን ገና እንደሚገባ እንዳልተጠቀሙበት እና ብዙ ሊሰሩት የሚችሉ ነገር እንዳለ ነው ያስታወቁት።

በኮንጎ ቆይታቸው ከርዋንዳ ጋ በሚያዋስነው ድንበር አካባቢ በምትገኘው የጎማ ከተማ በጀርመን ርዳታ የተገነባውን የአየር ማረፊያን፣ በመዲናይቱ ኪንሻሳም ለ23 ዓመታት ተዘግቶ የቆየውን የገተ ባህል ማዕከል መርቀው ከፍተዋል። ዛሬ ርዋንዳን የጎበኙት ሽታይንማየር በነገው ዕለት በኬንያ በሚያደርጉት ጉብኝታቸው አራተኛውን የአፍሪቃ ጉዟቸውን ያበቃሉ።

ክላውስ ሽቴከር/አርያም ተክሌ

ልደት አበበ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ