1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ወታደሮች የሶማሊያ ዘመቻ

ዓርብ፣ መጋቢት 26 2006

የጀርመን ፌደራል ጦር እጎአ ከ2010 አንስቶ የሶማሊያ ወታደሮችን በማሠልጠን ይሳተፋል። እስካሁን ሥልጠናው የሚሰጠው ዩጋንዳ ነበር። የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው ስብሰባ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ከአሁን በኋላ የጀርመን ወታደሮች ስልጠናውን ሶማሊያ ውስጥ መስጠት ይጀምራሉ።

https://p.dw.com/p/1BbuV
Bundeswehr Ausbildungsmission in Somalia
ምስል picture-alliance/Yannick Tylle

እነዚሁ ከጀርመን የሚሄዱት ወታደራዊ ልዑካን ሶማሊያ ዋና ከተማ መቅዲሾ ውስጥ ልዩ ጦር ማሰልጠን፣ የውትድርና ትምህርት መስጠትና ለሶማሊያ ጦር ሠራዊት አደረጃጀት ጥያቄዎች ምክር በመስጠትም ያገለግላሉ። የጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው ስብሰባ ቢበዛ 20 የጀርመን አሰልጣኞች ወደ ሶማሊያ እንዲሄዱ ተስማምቷል። ጀርመንን ጨምሮ ዘጠኝ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት በተካፈሉበት የሶማሊያ ወታደሮች ስልጠና እጎአ ከ2010 አንስቶ 3,600 የሶማሊያ ወታደሮች ሰልጥነዋል። በያዝነው በጎርጎሮሳውያኑ 2014 መጀመሪያ ላይ የአውሮፓ ህብረት የሶማሊያ ተልዕኮውን ከዩጋንዳ ወደ ሶማሊያ ዋና ከተማ መቅዲሾ አዛውሯል። በዚህ ወቅትም የጀርመን ፌደራል መንግሥት የመከላከያ ሚኒስቴር በሶማሊያ የፀጥታው ሁኔታ አስተማማኝ አይደለም በሚል የጀርመን ጦር ለጊዜው ወደዚያ እንዳይሄድ አድርጎ ነበር። በመካከሉ አሁን መንግሥት በሶማሊያ ዋና ከተማ መቅዲሾ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት ፀጥታው አስተማማኝ ተብሎ በሚታሰብ ስፍራ 20 የጀርመን ወታደሮችን ለማስፈር ተዘጋጅቷል። የጀርመን ክርስቲያን ዲሞክራት ህብረት ፓርቲ በምህፃሩ CDU የውጭ ጉዳዮች ፖለቲከኛ ፊሊፕ ሚስፌልደር ምክር ቤቱ የደረሰበት ውሳኔ ትክክለኛ ነው ይላሉ።

EUTM Somalia Archiv 2012
ምስል Bundeswehr

«ሰፋ ያለ ድርሻ ያለውና የወታደሮችን መጠን የሚመለከት ቢሆንም እዚህ ከባድ ውሳኔ ላይ ደርሰናል። እንደኛ አመለካከት የተወሰደው እርምጃ ትክክል ነው። የሚመጣውን ሁሉ ለመቀበልም ዝግጁ ነን።»

በሶማሊያ በደፈጣ ተዋጊው አሸባብ የሚካሄዱ የሰዎች ህይወት የሚያልፍባቸው ከባድ ጥቃቶች በተደጋጋሚ ይደርሳሉ። የነዚህ ጥቃቶች ዒላማዎችም በተለይ የአፍሪቃ ህብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ኃይል በምህፃሩ AMISOM ወታደሮች ናቸው። የሶሻል ዲሞክራቶቹ እንደራሴ ዳግማር ፍራይታግ ለጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት እንዳስረዱት ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ አሁን የሚሰጠው ድጋፍ ለሶማሊያ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ሃገራት መረጋጋትም ወሳኝና መቋረጥም የሌለበት ነው።

«ይህ የአሁኑ ሂደት ይሳካል አለበለዚያም ሶማሊያ መጨረሻ የተንኮታኮተች የምትባል ሃገር መሆን ነው። ይህ ከዛም አልፎ አጠቃላዩን የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ስጋት ላይ ይጥለዋል። ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለሰላምና መረጋጋት የሚሰጠው ድጋፍ አስፈላጊ እንደመሆኑ መጠን መቀጠል ያለበት ነው።»

Afrika Bundeswehr bildet somalische Soldaten in Uganda aus
ምስል MARC HOFER/AFP/Getty Images

በተያዘው እቅድ መሠረት የአውሮፓ ህብረት እጎአ በ2016 ሊካሄድ እስከ ታቀደው ምርጫ ድረስ የመንግሥት መዋቅሮችን በመዘርጋትና ሶማሊያንም በማረጋጋት እገዛ ያደርጋል። የጀርመን ጦር የሶማሊያ ተልዕኮ የሚቆየው እስከሚቀጥለው ዓመት መጋቢት አጋማሽ ድረስ ነው። በጀርመን ምክር ቤት ተቃዋሚዎቹ ፓርቲዎች ግራዎቹና አረንጓዴዎቹ የጀርመን ጦር ሶማሊያ መሰማራቱን ተቃውመዋል። በተቃዋሚዎቹ የምክር ቤት ተወካዮች አስተያየት በሶማሊያ የአውሮፓ ህብረት ተልዕኮ አልተሳካም። ህብረቱ ካሰለጠናቸው የሶማሊያ ወታደሮች አብዛኛዎቹ መንግሥትን ከድተው ከሸማቂ ታጣቂዎች ጋር ተቀላቅለዋል። ከግራዎቹ ፓርቲ የምክር ቤት አባል ሴቪም ዳግዴሌን የሶማሊያ መንግሥት ይፈፅማል ያሏቸውን የመብት ጥሰቶች ዘርዝረዋል።

«በሥልጠና እኛ የምናግዘው በሶማሊያ የሚገኘው መንግስት ተብዬው ሰብዓዊ መብት ክፉኛ በመርገጥ የሚወቀስ ነው። ፍርድ ቤት ተብዬዎቹም ሙት በቃ ይበይናሉ፤ ፖለቲካው ለጭቆና ለኃይል እርምጃና ለሙስና የቆመ ነው።»

ተቃዋሚዎች ከዚህ በተጨማሪ የዩናይትድ ስቴትስ አብራሪ የለሽ አውሮፕላኖች ጀርመን ከሚገኙ የአሜሪካን ጦር ሰፈሮች በሚሰጥ ትዕዛዝ ሶማሊያ ውስጥ የሚያካሂዱትን ድብደባ አውግዘዋል። የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ተወካይ አግኒየስካ ብሩገር የጀርመን መንግሥት ይህን የመብት ጥሰት አይቶ እንዳላየ ማለፍ የለበትም ሲሉም አሳስበዋል። ከጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት 118 ቱ የጀርመን ጦር ሶማሊያ መዝመቱን ተቃውመዋል።

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ