1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን መንግስት እና የኦፐል ተቋምን ከክስረት የመጠበቅ ዕቅዱ

ሰኞ፣ ግንቦት 24 2001

26,000 ጀርመናውያን በሩስልስሀይም፡ ቦሁም፡ ካይዘርስላውተርን እና አይዘንባህ በሚገኘው የጀርመን የኦፐል ተሽከርካሪ አምራች ተቋም ውስጥ ይሰራሉ።

https://p.dw.com/p/I1Vd
ምስል AP / DW Montage

15,600 የሚሆኑት የተቋሙ ዋና ሰፈር በማይን ወንዝ ዳርቻ ካለችው የፍራንክፈርት ከተማ በስተደቡብ ምዕራብ በምትገኘው የሩስልስሀይም ከተማ ነው የሚሰሩት። ተቋሙ እአአ 2002 ዓም 750 ሚልዮን ዩሮ በማውጣት ነበር ምርቱን የጀመረው። ሆኖም፡ ተቋሙ ልክ ያሜሪካውያኑ እናት መስሪያ ቤት «በአህጽሮት ኤም በመባል የሚታወቀው ጀነራል ሞተርስ » የገጠመው የክስረት ዕጣ እንዳይገጥመው ካለፉት ጥቂት ጊዚያት ወዲህ ትልቅ ስጋት ተደቅኖበት ከቆየ በኋላ፡ የዶይቸ ቬለ ባልደረባ ዛቢነ ኪንካርትስ እንደዘገበችው፡ የጀርመን መንግስት በሳምንቱ መጨረሻ በደረሰው ገላጋይ ሀሳብ ርምጃ ዕቅድ አማካይነት ከክስረት ተርፎ ሰራተኞቹም እፎይ ሊሉ በቅተዋል።

ገላጋዩ ዜና የተሰማው ከስድስት ሰዓት ያልተቋረጠ ድርድር በኋላ ባለፈው ቅዳሜ ሌሊት ላይ ነበር የተሰማው። ክስረት አስግቶት የነበረው የኦፐል ተቋም የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለጊዜው ተረጋግጦዋል። በተደረሰው ገላጋይ ሀሳብ መሰረት፡ የኦስትርያ-ካናዳውያኑ ተሽካርካሪዎች አከፋፋይ መስሪያ ቤት « ማግና » ከሩስያውያኑ ተሽከርካሪ አምራች ተቋም « ዜድ » እና ከከፊል መንግስታዊ የሩስያውያኑ « ስፔር ባንክ » ባንድነት በመሆን በአውሮጳውያኑ እጅ የሚገኘውን ያሜሪካውያኑ የኦፐል አምራች እናት ተቋም « ኤም » አክስየን እንዲወስዱ ተወስኖዋል። የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ውሳኔውን አጥጋቢ ሆኖ አግኝተውታል።

« ኦፐል ለወደፊቱ የሚበጅ አቅጣጫ ቀርቦለታል። ይህ፡ በኔ አመለካከት፡ ለሰራተኞቹ የሚገባቸውን አዲስ ዕድል ይከፍትላቸዋል። ምክንያቱም፡ ተቋሙ ለሚገኝበት ሁኔታ ተጠያቂው እነርሱ ሳይሆኑ በዩኤስ አሜሪካ በሚገኘው « ኤም » ውስጥ የተከሰተው የተበላሸ አስተዳደር ነው፡፡ »

ሁለት መቶ አርባ የምርት ሰፈሮች ያሉት 74,000 ቀጥሮ የሚያሰራው ወደ ሀያ አራት ሚልያርድ ዩኤስ ዶላር ገቢ ያስመዘገበው « ማግና ዓለም አቀፍ » በዓለም ካሉት ትልቆቹ አከፋፋዮች መካከል አንዱ ነው። ቅዳሜ ጥዋት ተረኞች የነበሩ የኦፐል ሰራተኞች ገንዘባቸውን አሁን በተቋሙ ውስጥ ለማሰራት በወሰኑት አዲሶቹ ባለወረቶች ላይ ትልቅ ተስፋ ማሳደራቸውን ከገለጹት መካከል አንዳንዶቹ አስተያየታቸውን ሲሰጡ እንዲህ ብለዋል።

« « ማግና » ጋር የብዙ ዓመታት ጥሩ ተሞክሮ አለን። « ማግና » ከብዙ አሰርተ ዓመት

ወዲህ የሚያስፈልገንን የተሽከርካሪ ዕቃ ያቀርብልናል። ስለዚህ ውሳኔው አዎንታዊ ነው። »

« አንድ ባለወረት ማግኘታችንን እና የወደፊቱን ዕድላችንን መሞከር መቻላችንን ጥሩ ውሳኔ ሆኖ

አግኝቼዋለሁ። »

ይሁን እንጂ፡ « ማግና » ገንዘቡን በኦፐል ተቋም ውስጥ ማፍሰስ ከመጀመሩ በፊት፡ የጀርመን መንግስት በእናት « ኤም » ላይ የደረሰው ክስረት በጀርመናውያኑ የኦፐል አምራች ተቋም ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳርፍና ራሱን ችሎ እንዲቆም ለማከላከል የሚያስችል ፊናንስ ዋስትና ይሰጣል። የመንግስት እጅ ያለባቸው ባንኮች፡ በመንግስት ዋስትና፡ አንድ ነጥብ አምስት ሚልያርድ ዩሮ ያቀርባሉ። ገንዘቡ ከመቅረቡ በፊት ግን የኦፐል ተቋም የሚገኝባቸው አራት የጀርመን ፌዴራዊ ክፍላተ ሀገር በሀሳቡ ላይ መስማማት ይኖርባቸዋል።

ይህ በዚህ እንዳለ፡ የዩኤስ አሜሪካ መንግስት ዛሬ በይፋ ክስረት እንደደረሰበት ያስታወቀውን « መንበሩ ዲትሮይት የሚገኘውን « ኤም » አክስየን መካከል ስድሳ ከመቶውን እንደሚረከብ አንድ የመንግስቱ አባል አስታውቀዋል። አስራ ሁለት ከመቶውን ካናዳ፡ አስራ ሰባት ነጥብ አምስት ከመቶውን አንድ የዩኤስ አሜሪካ የተባባረው የተሽከርካሪ አምራች ተቋም የሙያተኞች ማህበር እንደሚይዘው ተገልጾዋል። ይህም « ኤም » እንደገና ለማንቀሳቀስ ይቻል ዘንድ ዩኤስ አሜሪካ ከሰላሳ ሚልያርድ ዶላር በላይ የምታቀርብ ሲሆን፡ ከተቋሙ ማምረቻ ሰፈሮች መካከል አስራ አንዱ መዘጋት ይኖርባቸዋል።

ዛቢነ ኪንካርትስ/አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሐመድ