1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት በአንካራ

ሰኞ፣ ጥር 30 2008

ለጋሽ ሃገራት ቱርክ የሚገኙ ስደተኞችን ለመርዳት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን በአስቸኳይ እንዲያቋቁሙ ጀርመን ጠየቀች ። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ዛሬ አንካራ ቱርክ ውስጥ ከቱርኩ አቻቸው አህመት ዳቩቶግሉ ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ቱርክ ለሚገኙ ስደተኞች ጊዜ ሳይጠፋ የተጨበጠ ና የሚታይ እርዳታ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

https://p.dw.com/p/1Hrh9
Türkei Ankara Treffen zur Flüchtlingskrise Merkel und Davutoglu
ምስል Reuters/U. Bektas


ሜርክል የአውሮፓ ህብረት ለቱርክ ቃል የገባውን 3 ቢሊዮን ዩሮ በአስቸኳይ እንዲሰጥም ጠይቀዋል ።ቱርክም በሃገርዋ የሚገኙ ስደተኞችን አያያዝ እንድታሻሽልም ጥሪ አቅርበዋል ።ሜርክል በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ በሶሪያዋ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ አሌፖ በሩስያ በተፈፀመው የቦምብ ጥቃት ፣በደረሰው ጥፋትና እልቂት በእጅጉ መደንገጣቸውንም ተናግረዋል ።በ10 ሺህዎች ለሚቆጠሩ ሶሪያውያን ስደት ምክንያት በሆነው በዚህ እርምጃ ሞስኮ ባለፈው ታህሳስ የፈረመችውን የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ውሳኔ ሳትጥስ እንዳልቀረም ጠቁመዋል ።
ጀርመን በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በሶርያዉ የእርስ በርስ ጦርነት ለተጎዱ ዜጎች መርጃ 2,3 ቢሊዮን ይሮ ለዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች እንደምትሰጥ ማስታወቅዋ ይታወቃል። ለርዳታ ድርጅቶቹ ከሚሰጠዉ ከዚህ ገንዘብ መካከል 1, 2 ቢሊዮን ዩሮ በዚህ ዓመት እንደሚከፈል የጀርመንዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ለንደን ብሪታንያ ላይ ባለፈዉ ሳምንት መጀመርያ በተካሄደዉ የሶርያ የእርዳታ ማሰባሰብያ ጉባዔ ላይ መናገራቸዉ ይታወቃል።
«ጀርመን የስደትን ዋና ምክንያት ለመዋጋትና የሰብዓዊ ኑሮን በሶርያና በአጎራባች ሃገሮች ሊባኖስ እና ዮርዳኖስ ለማሻሻል አስተዋጽዖ ታደርጋለች። በተጨማሪም ቱርክ ዉስጥ ለስደተኞች መርጃ ለታቀደዉ የየሦስት ቢሊዮን ዩሮ ፕሮጄክት ጀርመን የድርሻዋን ታበረክታለች። ይህ መርሃ ግብር የስደትን መነሻዎች በመዋጋት ትልቅ ሚና ይጫወታል። በችግር ለሚጉላሉት ሰዎችም ጥሩ ቀን እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ አመሰግናለሁ።»
ጀርመን ለሶርያ የምትሰጠዉን ርዳታ ይፋ ከማድረግዋ ቀደም ብሎ ብሪታንያና ኖርዌ እስከ መጭዉ የጎርጎረሳዉያኑ 2020 ዓ,ም ድረስ በጋራ ወደ 2,6 ቢሊዮን ይሮ ለዓለማቀፉ የርዳታ ድርጅቶች እንደሚከፍሉ አስታዉቀዉ ነበር። ለንደን ብሪታንያ ላይ በተካሄደዉ ለሶርያ የርዳታ ማሰባሰብያ ጉባዔ ላይ የርስ በርሱን ጦርነት ለሸሹት የሶርያ ስደተኞች መርጃና አካባቢዉ ላይ ርዳታ ለመስጠት በአጠቃላይ ወደ 10 ቢሊዮን ዩሮ እንደተሰበሰበ ተዘግቦአል። ጀርመን፤ ብሪታንያ ኩዌት ኖርዌ እና ዩኤስ አሜሪካ ባዘጋጁት በዚህ ለሶርያ ርዳታ ማሳባሰብያ ጉባዔ ላይ የ 70 ሃገራት የመንግሥታት ተጠሪዎች መገኘታቸዉ ይታውቃል።

አዜብ ታደሰ

Türkei Ankara Treffen zur Flüchtlingskrise Merkel und Davutoglu
ምስል Getty Images/AFP/A. Altan
Türkei Ankara Treffen zur Flüchtlingskrise Merkel und Davutoglu
ምስል picture-alliance/dpa


ኂሩት መለሠ