1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመንና የአፍሪቃ የጋራ ጥናትና ምርምር

ረቡዕ፣ መጋቢት 10 2006

ጀርመን ከአፍሪቃ ጋር በትብብር በምትሠራባቸው ጥናትና ምርምሮች ላይ አትኩሮ ትናንት በርሊን ውስጥ በተካሄደ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤ ላይ የተገኙት የናምቢያ የግብርን ምክትል ሚኒስትር አና ሽዌዳ በመስኩ በሚከናወኑት የትብብር ሥራዎች ሁለቱም ወገኖች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

https://p.dw.com/p/1BSYZ
Anna Shiweda, Vize-Direktorin von SASSCAL
ምስል SASSCAL

ጀርመንና አፍሪቃ በአየር ንብርት ለውጥ ላይ ባተኮሩ የጥናትና ምርምር መስኮች ይበልጥ ተቀራርበው መሥራታቸው ጠቃሚ መሆኑን የናሚብያ የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን አስታወቁ ።ጀርመን ለዘርፉ የምትሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አስገንዝበዋል ። የጀርመን ፌደራል መንግሥት ከአፍሪቃ ጋር በትምህርት እና በጥናትና ምርምር ዘርፍ በአዲስ መልክ መተባበር ይፈልጋል ። ብዙውን ጊዜ የወላጅና ና የልጅ ዓይነት የነበረው የእርዳታ አሰጣጥ ተለውጦ ከሌላኛውም ወገን በኩል አስተዋጽኦ ያለበት እንዲሆን ነው የሚፈለገው ። ትናንት የታሰበውን የአፍሪቃ ቀን ምክንያት በማድረግ በርሊን ውስጥ ጀርመንና አፍሪቃ የጋራ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይ ባተኮረ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤ ላይ የተገኙት የጀርመን የትምህርት ሚኒስትር ዮሃና ቫንካ ጀርመን በጥናትና ምርምር ጥያቄዎች ላይ ከአፍሪቃ ጋር በትብብር መሥራቱን መቀጠል የመንግሥታቸው ግብ መሆኑን አስታውቀዋል ።በአሁኑ ጊዜ በምዕራብ ና በደቡባዊ አፍሪቃ የአፍሪቃና የጀርመን ሳይንቲስቶች በጋራ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ጥናትና ምርምር የሚካሂድባቸው ሁለት ማዕከላት አሉ ።እነርሱም የምዕራብ አፍሪቃው WASCAL ና የደቡባዊ አፍሪቃው SASSCAL የተባሉት የምርምር ማዕከላት ናቸው ።

SASSCAL- Aufbau von Kompetenzenzentren für Klimawandel und Landnutzung im Südlichen Afrika
የሳስካል ተመራማሪዎች በመስክ ሥራምስል Norbert Jürgens

የጀርመን የትምህርት ሚኒስቴር ለነዚህ ተቋማት 100 ሚሊዮን ዩሮ መድቧል ። በበርሊኑ ጉባኤ ላይ የተገኙት የሳስካል ምክትል ሃላፊና የናሚብያ የግብርና የወሃና የደን ሃብት ምክትል ሚኒስትር አና ሽዌዳ የጀርመን የገንዘብ ድጋፍ በተለይ ለሃገራቸው ለናሚብያ ልዩ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን ተናግረዋል ።

«ከጀርመን ጋር የምናካሂደው ትብብር ለናሚብያ ትልቅ ትርጉም አለው ። ጀርመን ዋነኛ የገንዘብ ድጋፍ ሰጭ ሆና 5 የደቡባዊ አፍሪቃ ሃገራት ይህን ሥራ ጀምረናል ። የማዕከሉ መጠሪያ ሳስካል የደቡባዊ አፍሪቃ የአየር ንብረት ለውጥ ና የመሪት ይዞታ ሳይንስ ምርምር ማዕከል ነው ። የአየር ንብረት ለውጥ ወሳኝ ሚና አለው ምክንያቱም ድንበር አያውቅም ። ጀርመን ለአምስቱ አገራት ከአየር ንብረት ለውጥ ና የመሬት ይዞታ ስርዓት ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች የሚውል የገንዘብ እርዳታ ትሰጣለች ። በአቅም ግንባታ ታግዛለች ።»

በሳስካል ስር የታቀፉት አምስቱ የደቡባዊ አፍሪቃ ሃገራት ናሚብያ ፣ቦትስዋና አንጎላ ዛምቢያና ደቡብ አፍሪቃ ናቸው ። 5 ቱ ሃገራት ጀርመን የምትገኝበት ቦርድ መስርተዋል ። በየሃገራቱ ከጀርመን ጋር የሚሰሩ ተቋማት ተለይተዋል ። በዚህ ስራ የሚሳተፉ የጀርመን ዩኒቨርስቲዎች ተመርጠዋል ። ከጀርመን ሳይንቲስቶች ጋር የመሥራት አቅም ያላቸው ተማሪዎችም ተለይተዋል ። ትከረታቸው የምድራችን ሙቀት መጨመር ያስከተለው የአየር ንብረት ለውጥ ነው ። የማዕከሉ ምክትል ሃላፊ ሽዌዳ በዘርፉ ተባብሮ መሥራቱ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት አስረድተዋል ።

SASSCAL- Aufbau von Kompetenzenzentren für Klimawandel und Landnutzung im Südlichen Afrika
ምስል Norbert Jürgens

« የአየር ንብረት ለውጥ በሁሉም ቦታ ይከሰታል ። ሆኖም የአየር ንብረት ለውጥ ሃገራችን ላይ የሚያስከትላቸውን ችግሮች ማወቅ እንፈልጋለን ። በአካባቢያችን የአየር ንብረት ለውጥ ብንመለከት አንጎላና ናሚብያ ወይም ደግሞ ዛምቢያ ርስ በርስ ይገናኛሉ ። በአንጎላ ካልዘነበ ናሚብያ ችግር ውስጥ ትወድቃለች ዛምብያ ካልዘነበ ናምቢያ ትቸገራለች ። ስለዚህ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን ችግሮች ሰፋ አድርገን መመልከት አለብን ። »

በዓለም ዓቀፋዊው የአየር ንብረት ችግር ላይ የሚያተኩሩት WASCAL SASSCAL የጀርመንና የአፍሪቃ ሳይንቲስቶች የልምድ መለዋወጫዎችም ሆነው ያገለግላሉ ለነዚህ ማዕከላት ጀርመን እርዳታ መስጠቷን ለመቀጠል ቃል በመግባቷ ያመሰገኑት ሽዌዳ አፍሪቃውያንም ራሳቸውን የሚረዱባቸውን መንገዶች መፈለግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል ።

«እንደሚመስለኝ ዛሬ በታሰበው የአፍሪቃ ቀን ተጨማሪ ኃይል አግኝተናል ። ጀርመን አሁንም የገንዘብ ድጋፉን ለመቀጠል በገባችው ቃል ፀንታለች ። ለዝህም ምስጋናችን ከፍተኛ ነው መንግሥታችንም ይህን ፕሮጀክት በገንዘብ እንዲደገፍ መንገር አለብን የጀርመን የገንዘብ ድጋፍ ሁሌ ሊኖር አይችልም ። ስለዚህ የአፍሪቃ ሃገራት ይህን ጅምር እንዴት ወደፊትማራመድ እንደሚችሉ የራሳቸውን እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል ። »

ሂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ