1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመንና የህንድ ግንኙነት

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 19 2000

የጀርመንዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል በህንድ የመጀመሪያ ይፋ ጉብኝታቸውን ትናንት ጀምረዋል ።

https://p.dw.com/p/E0br
ሜርክልና ሲንግ በኒውዴልሂ
ሜርክልና ሲንግ በኒውዴልሂምስል AP
ከሜርክል ጋር ወደ ህንድ ከተጓዙት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት መካከል የጥናትና ምርምር ሚኒስትርዋ አኔተ ሻቫንና የጀርመን ዋነኛ የኢኮኖሚ ጉዳይ ሀላፊ ይገኙበታል ። ከዚህ በተጨማሪም ሜርክል ሰላሳ የንግድ ልኡካንንም አስከትለው ህንድ የሄዱት ። የሜርክልን የህንድ ጉብኝት አስመልክቶ የወጡ ዘገባዎች ሁለቱም ሀገራት ግንኙነታቸውን በምጣኔ ሀብት በሳይንስ እንዲሁም በፖለቲካው አቅጣጫ ማሳደግ እንደሚሹ ያስገነዝባሉ ። ሜርክል ወደ እስያ ሲያቀኑ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው ። በቅርቡ ቻይናና ጃፓን ነበሩ ህንድ ሲሄዱ የአሁኑ የመጀመሪያቸው ነው ። በህንድ የአራት ቀናት ጉብኝታቸውን ትናንት የጀመሩት ሜርክል ትናንት ህንድ ዋና ከተማ ኒውዴልሂ በሚገኘው ፕሬዝዳንታዊው ቤተ መንግስት ውስጥ የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማንሞሀን ሲንግ ባደረጉላቸው የአቀባበል ስነ ስርዓት ላይ እንደተናገሩት የአሁኑ ጉዞአቸው ዓላማም በፍጥነት በማደግ ላይ ካለችው ከእስያዊትዋ ሀገር ህንድ ጋር በልዩ ልዩ መስኮች ግንኙነታቸውን ማጠናከር ነው ። የጀርመን ሳይንቲስቶችንም አስከትለው ህንድ የገቡት ሜርክል በተለይም በሳይንስ እንዲሁም በጥናትና ምርምሩ መስክ ከህንድ ጋር በትብብር መስራት ይሻሉ ።
«ባለሞያዎቻችን ከህንድ ጋር በአጠቃላይ የጋራ ጥናትና ምርምርን ጨምሮ ልምድ እንዲለዋወጡ እንፈልጋለን ። እዚህ የመጣነውም አንዳንድ ስምምነቶችን ለመፈራረም እና ህንድም በሳይንሳዊው ልማት ዘርፍ ተባባሪያችን መሆንዋን ግልፅ ለማድረግ ነው ። »
ከዚህ ሌላ ህንድና ጀርመንን የሚቀራርቡዋቸው የጋራ ጉዳዮችም አሉ ። በተለይ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በሚከተሉዋቸው መርሆች አንፃር በፀረ ሽብሩ ትግል በቅርብ መስራታቸው በዚህ ረገድ ይነሳል ። ሆኖም ግን አስተያየት ሰጭዎች እንደሚሉት የአሁኑ ግንኙነት ከአንድ ጠንካራ አውሮፓዊት ሀገር ጋር ሊኖር የሚገባው ግንኙነት ዓይነት አይደለም ። በዚህ የተነሳም የሁለቱን አገራት ስልታዊ ግንኙነት አቅጣጫ ለማስያዝ ከዓመታት በፊት የተደረሰው ስምምነት ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ነው የህንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ናቭቴጅ ሳርና የሚናገሩት ።
« ለግንኙነቱ የተቀየሰው ስልታዊ አቅጣጫ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በሁለት ሺህ አንድ ነው የፀደቀው ። ይሁንና ይህ ካለ ፖለቲካዊ ትብብር ተግባራዊ ሊሆን አይችልም ። ሁለቱም ሀገራት ዲሞክራሲያዊ ዕሴቶቻቸውን ይዘው በሚቻላቸው ሁሉ መቀራረብ ይገባቸዋል ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ተሀድሶ መቃወማቸው በዚህ ረገድ የሚጠቀስ የጋራ አቋማቸው ነው ። ፀረ ሽብር አቋም መያዛቸውም እንዲሁ ያመሳስላቸዋል ። በበኩላችን እነዚህ ሂደቶች ተጠናክረው ማየት እንፈልጋለን ። »
ከመራሂተ መንግስት ሜርክል ጋር የጀርመን ግዙፎቹና እና ስም ያላቸው ኩባንያዎች ከፍተኛ ሀላፊዎችም አብረዋቸው ተጉዘዋል ። ከነዚህ ውስጥ የሲመንስ የባስፍ እንዲሁም የጀርመን የባቡር አገልግሎት ድርጅት የዶይቼ ባን ሀላፊዎች አሉበት ። ሜርክል ወደ ህንድ ከማቅናታቸው በፊት በሰጡት አስተያየት የጀርመን ባለኢንዱስትሪዎች ምጣኔ ሀብትዋ በመመንደግ ላይ ካለው ከህንድ ጋር የንግድ ግንኙነታቸውን እንዲያጠብቁ ጥሪ አድርገው ነበር ። ሜርክል በእስካሁኑ የጀርመንና የህንድ የንግድ ግንኙነት አይረኩም ። እንደርሳቸው ጀርመን ከህንድ ጋር ያላት የውጭ ና የውስጥ ንግድ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው ያለው ። ኢንዲያ ቱዴይ የተባለው የህንድ ሳምንታዊ መፅሄት ጋዜጠኛ ሳውራብህ ሹክላ ለዶይቼቬለ ራድዮ እንደተናገረው በአሁኑ ሰዓት ጀርመን ከህንድ ገበያ ወጥታለች ። « ግኙነታችንን እንደገና ማደስ አለብን ። ህንድና ጀርመን በጣም የዳበረ ምጣኔ ሀብታዊ ግንኙነት ነው ያላቸው ። ሆኖም አሁን ሌሎቹ የአውሮፓ ሀገራት በሙሉ ጀርመን ከገበያ ውጭ አድርገዋታል ። » የዛሬ ዓመት የጀርመንና የህንድ ንግድ አስር ቢሊዮን ዩሮ አልፎ ነበር ። ጀርመን ህንድ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን ከሚያፈሱ ሀገራት ሰባተኛው ደረጃ ላይ ናት ።