1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኽለንራይነር የአውስሽቪትዝ ትውስታ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 8 2011

ጂፕሲዎች ይታጎሩበት የነበረው የአውስሽቪትዝ ቢርክናው ካምፕ በጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 2 ቀን፤ 1944 ሌሊት ተዘግቶ በሽህዎች የሚቆጠሩ አዋቂ ወንዶች እና ሴቶች እንዲሁም ህጻናት በመርዝ ጋዝ ታፍነው እንዲገደሉ እና አስከሬናቸውም እንዲቃጠል ተደርጓል። የታሪክ ምሁራን በቅርቡ እንደደረሱበት በዚያን ሌሊት ቢያንስ 4 ሺህ ሰዎች ተገድለዋል።

https://p.dw.com/p/3Gu6X
Auschwitz-Überlebender Hermann Mano Höllenreiner
ምስል DW/A. Grunau

የጀርመናዊ ጂፕሲ የአውስሽቪትዝ ትውስታ

የዛሬ 75 ዓመት አውስሽቪትዝ በተባለው ፓላንድ በሚገኘው የናዚዎች የሰዎች ማጎሪያ ሥፍራ በ2 ቀናት ውስጥ ከተገደሉት ሰዎች መካከል 4ሺህ ሲንቲ ወይም ሮማ ተብለው የሚጠሩት ሕዝቦች ይገኙበታል። ከዚህ ግድያ በተዐምር ተርፈው ዛሬም በሕይወት የሚገኙ የአንድ ጀርመናዊ ሲንቲ ወይም ጂፕሲ አዛውንት ተሞክሮ የዛሬው ዝግጅት ትኩረት ነው።

የአውስሽቪትስ የሰዎች ማጎሪያ ሥፍራ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ናዚ ጀርመን፣ ፖላንድ ውስጥ የሠራው ከ40 በላይ የሰዎች ማጎሪያ እና መግደያ ስፍራ ነው። ከመካከላቸው «አውስሽቪትስ ቢርከናው» የተባለው ብሬዜዚንካ  ከተባለችው ከተማ ሦስት ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ካምፕ አንዱ ነው። ናዚ ጀርመን በጎርጎሮሳዊው መስከረም 1939 ፖላንድን ከወረረ በኋላ ከገነባቸው የሰዎች መጨፍጨፍያ እና ማሰቃያ ካምፖች ውስጥ «አውስሽቪትስ ቢርከናው» በተለይ ለይሁዲዎች ጉዳይ የመጨረሻ መፍትኄ የተሰጠበት ነውም ይባላል። ከመላው አውሮጳ የተሰበሰቡ አይሁዶች በባቡር እየተጋዙ ወደዚህ ካምፕ ይገቡ ነበር። ከጎርጎሮሳዊው 1942 እስከ 1944 ይሁዲዎች በዚህ ስፍራ በመርዛማ ጋዝ ታፍነው በጅምላ እንዲገደሉ ተደርጓል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ወደዚህ ስፍራ ከተጋዙት 1.3 ሚሊዮን ሰዎች መካከል ቢያንስ 1.1 ሚሊዮኑ እንደተገደሉ ይገመታል። ከነዚህም 90 በመቶው ይሁዲዎች ናቸው።  ከይሁዲዎች ሌላ ሮማ እና ሲንቲ ወይም ጂፕሲ የሚባሉት በአውሮጳ የሚገኙ አናሳ ሕዝቦችም  ተመሳሳይ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል።  
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ናዚ ጀርመን ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ሮማ እና ሲንቲዎችን ወይም ጂፕሲዎች ጨፍጭፏል። ማኖ ኽልንራይነር ሲንቲና ሮማዎች በግፍ ይገደሉበት ከነበረው «አውስሽቪትስ ቢርከናው» ከተባለው ካምፕ እንደ እድል ሆኖ በሕይወት መትረፍ ከቻሉት ሰዎች አንዱ ናቸው። በወቅቱ የ10 ዓመት እድሜ የነበረው ኽልንራይነር እና ቤተሰቡ ለጥቂት ነበር ከሞት ያመለጡት። ኽልንራይነር ዛሬ የ85 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ ናቸው። ደቡብ ጀርመን ባቫርያ ግዛት ውስጥ ከሙኒክ ከተማ በስተምሥራቅ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሜተንሃይም  የሚኖሩት እኚህ አዛውንት ለዶቼቬለዋ ዳንኤላ ግሩናው እንዳሳዩት የዛሬ 75 ዓመት እጃቸው ላይ የታተመው Z 3526 የሚለው የእስረኛ መለያ ቁጥራቸው ዛሬም አልጠፋም። ሊጎበኛቸው የሚመጣ ሰው ሁሉ ማየት የሚፈልገው እሱን መሆኑን ይናገራሉ። ከቁጥሩ በፊት የሚገኘው Z የሚለው ፊደል በጀርመንኛው ሲጎይነር የሚለው ቃል አህጽሮት ነው። ሲጎይነር አውሮጳ ውስጥ በቁጥር አናሳ የሆኑት የህዳጣኑ የሲንቲ እና የሮማ ህዝቦች መጠሪያ ነው። ኽልንራይነር ሲጎይነር ወይም ጂፕሲ ተብለው ለግፍ ቢዳረጉም እርሳቸው እና ሌሎችም ዘመዶቻቸው ጀርመናውያን መሆናቸውን ነው የሚናገሩት።
« ጀርመናዊ ነበርን አዎ ሁላችንም አያቴ ቅድመ አያቴ ሁሉም በወታደርነት አገግለዋል። እና ጀርመናዊ ሲንቲዎች ነን።»
ጂፕሲዎች ይታጎሩበት የነበረው የአውስሽቪትዝ ቢርክናው ካምፕ በጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 2 ቀን፤ 1944 ሌሊት ተዘግቶ በሽህዎች የሚቆጠሩ አዋቂ ወንዶች እና ሴቶች እንዲሁም ህጻናት በመርዝ ጋዝ ታፍነው እንዲገደሉ እና አስከሬናቸውም እንዲቃጠል ተደርጓል። የታሪክ ምሁራን በቅርቡ እንደደረሱበት በዚያን ሌሊት ቢያንስ 4 ሺህ ሰዎች ተገድለዋል። ይህ ከመፈጸሙ በፊት በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የነበረው የ10 ዓመቱ ማኖ ከወላጆቹ እና ከእህቱ ጋር ራቨርስብሩክ ወደተባለው ጀርመን ወደሚገኝ ሌላ ካምፕ ተወስዶ ነበር። ቤተሰቡ እንደ እድል ሆኖ ከነሐሴ 2ቱ ጭፍጨፋ ተርፏል። ሆኖም በስፍራው የነበሩት አያቱ፣ የአክስት የአጎቱ ልጆች ሌሎች ዘመዶቹ ግን ተገድለዋል። የኽልንራይነር ቤተሰቦች በዚህ የግፍ ግድያ 36 የቤተሰቦቻቸውን አባላት ተነጥቀዋል። የይሁዲ ዝርያ ያላቸው እናቱም ከ100 በላይ ዘመዶቻቸው ተገድለውባቸዋል። ኽልንራይነር የማጎሪያ ካምፑ ትዝታ ሲመጣ ያኔ ግድያ ይፈጸምበት ከነበረው ቦታ ይሰማ የነበረው ድምጽ አሁንም በጆሮአቸው ላይ ያቃጭላል። የግድያው ምስልም ከአዕምሮአቸው አልጠፋም። አንዳንዴ እሳቸው እና የአጎታቸው ልጅ የሰዎች አስከሬ ሲጓጓዝ ያግዙም ነበር። ከመካከላቸው የህጻናትም ይገኝበት እንደነበረ ያስታውሳሉ። 
«በጣም ትንሽ የራስ ቅል አይቻለሁ። የተገደሉትን ማንሳት አለብን። የአስከሬኑ ክምር አንዳንዴ የቤቴን ጣሪያ ያህል ሽቅብ የሚቆለል ነበር። 
የኽለንራይነር አባት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲጀመር በወታደርነት ተሰልፈው ነበር። ሆኖም ብዙ ሳይቆዩ ግማሽ ጂፕሲ በመሆናቸው ከጦሩ ተባረሩ። ወንድማቸውም ተመሳሳይ እጣ ደርሶባቸዋል። ወደ መኖሪያቸው ወደ ሙኒክ ከተመለሱ በኋላም በፖሊስ ጥበቃ ስር በመንገድ እና በሌሎችም የግዳጅ  የጉልበት ሥራ ነበር የተሰማሩት። መጋቢት 1943 ማለዳ የነኽለንራይነር በር ተንኳኳ። በሩ ሲከፈት ፖሊስ ቆሟል። ቤተሰቡ በአስቸኳይ እንዲወጣ ተነገረው። ከሌሎች ሺህዎች ጋር በከብት ማመላለሻ ፉርጎ ተጭነው ከቀናት ጉዞ በኋላ ፖላንድ ገቡ። ኽለንራይነር ያኔ 9 ዓመታቸው ነበር። ካምፓቸው «አውስሽቪትዝ ቢርከናው» እንደደረሱም ሁሉም እጃቸው ላይ መለያ ቁጥር ተነቀሶላቸው፤ ጸጉራቸውንም ተላጭተው ለጂፕሲዎች ተብሎ በተሰራ ካምፕ ውስጥ ገቡ። ዳቦ እና ሽንኩርት መሰል የበሰበሰ አትክልት ብቻ ነበር ምግባቸው። ሌሊት መነሳት ብርድም ቢሆን ግድ ነው። ህጻኑ ኽለንራይነር እድሜያቸው የገፋ ሴቶች ወድቀው እዚያው ሲሞቱ አይቷል። 
«ክረምትም ቢሆን በረዶ ቢቆለልም እጅግ ማልዶ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ነው የምንነሳው። በእድሜ የገፉ ሴቶች በብርዱ ምክንያት እዚያው እየወደቁ  ይሞታሉ ወይም ደግሞ መጸዳጃ ቦታ ይወድቃሉ። መጸዳጃ ቤት የለም። ባሊ ውስጥ ነው የምጸዳዳው እጅግ አስከፊ ነበር። እስካሁን በሕይወት መቆየት መቻላችን ተዐምር ነው።»
ከሁሉ ከሁሉ ከካምፓቸው አቅራቢያ ከሚገኘው የአስከሬን ማቃጠያ ክፍል የሚመጣው  ዘግናኝ ሽታ አይረሳቸውም። የአውስሽቪትዙ ካምፕ ከመዘጋቱ በፊት በተዛወሩበት በጀርመኑ ራቨንስብሩክ ካምፕ ጂፕሲዎች እንዲመክኑ አሰቃቂ ቀዶ ህክምናዎችን ይደረግላቸው ነበር። አባታቸው እናታቸው አጎታቸው እና ሌሎች ዘመዶቻቸው በዚህ የግዳጅ ቀዶ ህክምና እንዲመክኑ ተደርጓል። ከራቨንስብሩክ ወደ ዛክሰንሃውዘኑ ማጎሪያ የተወሰዱት ኽለንራይነር እና አክስት እና የአጎቶቻቸው ልጆች በስተመጨረሻ ከተያዙበት ካምፕ መውጣት ቻሉ። ያኔ ብዙ መራመድ ያልቻሉትን ኽለንራይነርን «ጀርመናዊ ነኝ እንዳትል» ብለው የፈረንሳይ እስረኞች በመኪና አሳፍረዋቸው ወደ ፓሪስ ሄዱ። ፓሪስ ሲገቡ 11 ዓመታቸው ነበር። በዚያ ካስጠጋቸው ቤተሰብ ጋር የቆዩት ኽለንራይነር በጎርጎሮሳዊው 1946 ቤተሰቦቻቸው ወደሚገኙበት ሙኒክ ተመለሱ። የኽራይነር ታሪክ በደራሲ አንያ ቱከርማን ተጽፎ በመጽሐፍ ታትሟል። ኽለንራይነር የደረሰባቸው ግፍ እና ሰቆቃ ትቶት ያለፈው ጠባሳ ዛሬም አልሻረም። ባለቤታቸው እንደሚናገሩት በእንቅልፍ ልባቸው ሲጮሁ ሲጨነቁ መስማት የተለመደ ነው። ማኖ ኽልንራይነር ይህ ያለፈ ታሪክ እንዳይረሳ ይታገላሉ። በትምሕርት ቤቶች እየተዘዋወሩ በማጎሪያ ካምፖቹ ስለተፈጸመው ገለጻ ያደርጋሉ። ለዚህ ተግባራቸውም የፌደራል ጀርመን የክብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ይህን የሚያደርጉትም ወጣት ጀርመናውያን በወቅቱ የሆነውን በትክክል እንዲያውቁ ለማድረግ ነው።
«ወጣት ጀርመናውያን በማጎሪያ ሥፍራዎቹ ሲፈፀም የነበረውን እና አጠቃላዩ የሂትለር ስርዓት ወንጀለኛ እንደነበር እንዲያውቁ ነው። የርሱ ተከታዮች አሁንም አሉ። ይህም ናዚዎች እንደገና ያንሰራራሉ የሚል ፍርሀት አሳድሮብኛል። ይህ ሊሆን አይገባም። 6 ሚሊዮን ይሁዲዎች 500 ሺህ ሮማ ሩስያዎች እና ሌሎችም በሙሉ መጨፍጨፋቸውን ጀርመኖች ያውቃሉ። እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ተመልሶ ሊመጣ አይገባም።»
ቤተሰቡ ጦርነቱ ካበቃ በኋላም አድልዎ መገለሉ አልቀረላቸውም። ልጃቸው የከፈተችውን የንግድ ድርጅት ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ያከናውናል የሚል ስም ወጥቶለት ነበር። ኽለንራይነር አሁንም ለልጃቸው ይሰጋሉ፤ ቤተሰቡ ደግሞ ለርሳቸው። ከስጋት ውጭ አማራጭ ለጀርመን የተባለው ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ አመራር አሌግዛንደር ጋውላንድ ጋውክ በናዚ የተፈጸመውን ግፍ በአንድ ሺህ ዓመት የጀርመን ታሪክ ውስጥ የምትታይ ጠብታ ቆሻሻ ነች ሲሉ ማናናቃቸው በእጅጉ ያሳዝናቸዋል።

Der Auschwitz-Überlebende Hermann Mano Höllenreiner mit seiner Frau Else Höllenreiner.
ምስል DW/A. Grunau
Buchcover: Mano.: Der Junge der nicht wußte, wo er war (von Anja Tuckermann)
ምስል Hanser
Mano Vater Johann Baptist Höllenreiner in Wehrmachtsuniform, 1941
ምስል Dokumentations- und Kulturzentrum Deutscher Sinti und Roma
Überlender des Holocaust - Hermann Höllenreiner zeigt Joachim Gauck
ምስል picture-alliance/dpa/W. Kumm

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ