1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

    የጀርመኑ ፕሬዝደንት የሩሲያ ጉብኝት

ሐሙስ፣ ጥቅምት 16 2010

በ1994 (ዘመኑ በሙሉ እጎአ ነዉ) የጀርመንን የፕሬዝደንትነት ሥልጣን ይዘዉ የነበሩት ሮማን ሔርሶግ በ1997 ለሩሲያ ምክር ቤት (ዱማ) ካደረጉት ማራኪ ንግግር ወዲሕ እስከ 2010 ድረስ የቀጠለዉ ጉብኝት፤ዉይይት ከክብር መግለጫነት አልፎ የሁለቱ ሐገራት ወዳጅነት ጥበቀት መገለጫ ተደርጎም ነበር።

https://p.dw.com/p/2mZSj
Russland Bundespräsident Steinmeier in Moskau
ምስል picture alliance/dpa/Tass/M. Metzel

Steinmeier besuch in Moskaw - MP3-Stereo

 

የጀርመን ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይማር ሐገራቸዉ ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል የሁለቱ ሐገራት መንግስታት መጣር እንደሚገባቸዉ አስታወቁ።ሩሲያን የጎበኙት ፕሬዝደንት ሽታይማር ትናንት ሞስኮ ዉስጥ ለሩሲያዊ አቻቸዉ ለቭላድሚር ፑቲን እንደነገሩት በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችን ለማስወገድ በጋራ መስራቱ  ለሁለቱ ሐገራትም፤ለዓለምም ሠላም ይጠቅማል።ይሁናና ሩሲያ የክሬሚያ ግዛትን መጠቅለልዋንና በምሥራቃዊ ዩክሬን ዉጊያ እጇን ማስገባትዋን ጀርመን እንደማትቀበለዉ ሽታይን ማየር አልሸሸጉም። በሰባት ዓመት ዉስጥ አንድ የጀርመን ፕሬዝደንት ሩሲያን ሲጎበኝ ሽታይን ማየር የመጀመሪያዉ ናቸዉ።

የተዋደችዉ ጀርመን ፕሬዝደነንቶች ለሩሲያ ያላቸዉን አክብሮት መግለጥ እና ሩሲያን መጎብኘት እንደ ግዴታ የሚያዩና የሚያደርጉት ምግባር ነዉ።በ1994 (ዘመኑ በሙሉ እጎአ ነዉ) የጀርመንን የፕሬዝደንትነት ሥልጣን ይዘዉ የነበሩት ሮማን ሔርሶግ በ1997 ለሩሲያ ምክር ቤት (ዱማ) ካደረጉት ማራኪ ንግግር ወዲሕ እስከ 2010 ድረስ የቀጠለዉ ጉብኝት፤ዉይይት ከክብር መግለጫነት አልፎ የሁለቱ ሐገራት ወዳጅነት ጥበቀት መገለጫ ተደርጎም ነበር።
ከ2012  እስከ 2017 (ዘንድሮ) ድረስ ሥልጣን ላይ የነበሩት ዮአኺም ጋዉክ ግን ይሕን ይትበሐል ሠብረዉት ነበር።እርግጥ ነዉ ፕሬዝደንት ጋዉክም ቢሆኑ በ2012 የሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በበርሊን በኩል ወደ ፓሪስ ሲጓዙ በርሊን ላይ አግኝተዉ አነጋግረዋቸዉ ነበር።
ሞስኮን ግን እንደ ፕሬዝደንት ጉብኝተዉ አያዉቁም።በሁለት ምክንያንት።ጋዉክ ሥልጣን ላይ የነበሩት የሩሲያ እና የምዕራባዉያን ጠብ የተካረረበት ወቅት መሆኑ ቀዳሚዉ ነዉ።የቀድሞዉ የምሥራቅ ጀርመን ቄስና የመብት ተሟጋቹ ጋዉክ በዚያን ወቅት እዚያዉ ምሥራቅ ጀርመን የነበረዉ የሶቬየት ሕብረት የሥለላ ድርጅት ኬጂቢ አዛዥ የነበሩት ቭላድሚር ፑቲንን መጥላታቸዉ-ሁለተኛዉ።
በዩክሬን ጦርነት እና ሩሲያ የቀድሞዋን የዩክሬን ግዛት ክሪሚያን ከግዛትዋ በመቀየጥዋ ሰበብ የሻከረው የሞስኮ እና የዋሽግተን-ብራሥልስ ግንኙነት አሁንም ብዙ መሻሻል አልታየበትም።እንደ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጠቡን ከነምክንያቱ፤ ምናልባትም መፍትሔ-ጠብ ማጋጋሚያዉንም የሚያዉቁት ሽታይንማየር አሁን እንደ ፕሬዝደንት ያደረጉት ጋዉክ አቋርጠዉን የነበረዉን የጀርመን ፕሬዝደንቶች ይትበሐል ለመቀጠል ያለመ ይመስላል።መልዕክታቸዉም «እንቀራረብ» የሚል ነዉ።«ይሕ (ግንኙነት) የምንፈልገዉን ዉይይት የሚያካትት እና  የለያየንን ግጭት ለማስወገድ የምናደርገዉን ጥረት የሚጨምርም ነዉ።»
የቀድሞዉ ዲፕሎማት የዩክሬንን ቀዉስ ለመፍታት ከሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ከሰርጌይ ላቭሮቭ ጋር በተደጋጋሚ ተወያይተዋል።ለፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንም አዲስ ሰዉ አይደሉም።የካተሪንቡርግ በሚገኘዉ ዩኒቨርስቲ በየዓመቱ ገለፃ ሥለሚያደርጉም በብዙ የሩሲያ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እና ምሑራን ዘንድ  በቅርብ ይታወቃሉ።

Russland Bundespräsident Steinmeier in Moskau
ምስል picture alliance/dpa/B. v. Jutrczenka

በዚሕም ምክንያት በሩሲያኖቹ ዘንድ ጥሩ ስምና ዝና ካላቸዉ የጀርመን ፖለቲከኞች ሽታይማየር አንዱ ናቸዉ።ትናንት ክሬምሊን ዉስጥ ከሩሲያዉ አቻቸዉ ጋር በተነጋገሩበት ወቅትም የፕሬዝደንት ፑቲንን አመኔታ በቀላሉ ያገኙ መስለዋል።«ይሕ የጀርመን ፕሬዝደንት ጉብኝት የጋራ ግንኙነታችንን ለማጠናከር ጥሩ ማበረታቻ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ።» 
ሁለቱ ፕሬዝደንቶች ሥለ ሁለቱ ሐገራት ግንኙነት እና ግንኙነቱን ለማሻሻል ሥለመፈለጋቸዉ ደጋግመዉ ቢናገሩም፤ ሩሲያ በምሥራቃዊ ዩክሬን ጦርነት እጇን ሥለማስገባትዋን እና ክሪሚያን ከግዛትዋ መጠቅለልዋን ሽታይንማየር ማዉገዛቸዉ አልቀረም።የጀርመኑ ፕሬዝደንት የሩሲያ መንግሥት ወርሶት የነበረዉን የቅዱስ ጴትሮስ-ጳዉሎስ ካቲድራልን ለፕሮቴትታንት ቤተ-ክርስቲያን በመለሰበት ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል።የመጨረሻዉን የሶቭየት ሕብረት መሪ ሚኻኤል ጎርቫቾቭን አነጋግረዋልም።

Russland Bundespräsident Frank-Walter Steinmeier mit dem ehemaligen Präsident der Sowjetunion, Michail Gorbatschow
ምስል picture-alliance/dpa/B. von Jutrczenka

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ