1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድርቅ መባባስ ስጋት በአፍሪቃው ቀንድ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 24 2014

የዓለም ሜቴሬዎሎጂ ድርጅት ባሳለፍነው ሳምንት ይፋ ባደረገው መረጃ ከመጪው ጥቅምት እስከ ታኅሣስ በአፍሪቃው ቀንድ አካባቢ ከተለመደው ያነሰ የርጥበት ሁኔታ ይጠበቃል። ይኽን ተከትሎ የወጡ መረጃዎች የአፍሪቃው ቀንድ አካባቢ ከ40 ዓመታት በላይ ባልታየ ሁኔታ አሁን ያለው ድርቅ ሊባባስ እንደሚችል እያሳስባሉ።

https://p.dw.com/p/4GEjK
Äthiopien Tigray Konflikt Symbolbild
ምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

ጤና እና አካባቢ

 

ኢትዮጵን ጨምሮ በአፍሪቃው ቀንድ ሃገራት ባለፉት ወራት የታየው ድርቅ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል የዓለም የሜቲሪዎሎጂ ድርጅትን መረጃዎች መነሻ በማድረግ የተመድን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት እያሳሰቡ ነው። የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት በእንግሊዝኛ ምህጻሩ ኢጋድ የአየር ንብረት ትንበያ ማዕከል ዳይሬክተር ጉለይድ አርተን «በሚያሳዝን መልኩ ለአምስት ዓመት በተከታታይ በዝናብ ወራት በቂ ዝናብ እንዳልዘነበ አስተማማኝ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ነው ባሳለፍነው ሳምንት ዓርብ የተናገሩት። እሳቸው እንደሚሉትም በተለይ በድርቅ በተጎዱት የሶማሊያ፣ ኬንያ እና ኢትዮጵያ አካባቢዎች በዚህ መዘዝ ያልተጠበቀ እና አሳሳቢ ሰብዓዊ ቀውስ ሊከሰት ይችላል። ክሌር ኖሊስ የዓለም ሜቴሪዎሎጂ ድርጅት የመገናኛ ዘርፍ ባለሥልጣን ይኽንኑ ባሳለፍነው ሳምንት ይፋ አድርገዋል።

Dürre Hungersnot Afrika Flash-Galerie
የድርቁ ኹኔታ በኬንያምስል picture-alliance/dpa

«ደረቅ እና መካከለኛ ሁኔታዎች በአብዛኞቹ የአካባቢው ስፍራዎች ሊኖር እንደምችል መረጃዎች አመላክተዋል። በተለይ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ ውስጥ በድርቅ የተጎዱት አካባቢዎች እስከ ያዝነው ዓመት መጨረሻ ድረስ እጅግ አነስተኛ ዝናብ የሚያገኙ ይኾናል። ያልተጠበቀ የሰብዓዊ ቀውስ ሊደርስ በቋፍ ላይ ነን።»

ባሳለፍነው ሳምንት ሐሙስ የተመድ በበኩሉ በከፋ የረሀብ አደጋ ቋፍ ላይ ትገኛለች ባላት ሶማሊያ በድርቅ ምክንያት አንድ ሚሊየን ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን አመልክቷል። ከግማሽ ሚሊየን የሚበልጡት እነዚህ የድርቅ ተፈናቃዮችም በሀገሪቱ የድንበር አካባቢዎች እንደሚገኙም ተገልጿል። ድርቁ ባስከተለው ቀውስ ለረሃብ የተጋለጡት ቁጥርም ወደ አምስት ሚሊየን ሊጠጋ እንደሚችልም ነው የተነገረው። ካርላ ድራይስዴል የዓለም የጤና ድርጅት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ባለሙያ ናቸው።

Dürre Hungersnot Afrika Flash-Galerie
የድርቁ ተጽዕኖ በኬንያምስል picture alliance/dpa

«በርካታ ቤተሰቦች እጅግ አደገኛ የሆኑ ርምጃዎችን እንዲወስዱ ያስገደዳቸው ይኽ ሁኔታ የዓለም የጤና ድርጅትን በጣም አሳስቦታል። በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤታቸውን ትተው ምግብ፣ ውኃ እና ለከብቶቻቸው መኖ ለመፈለግ ተሰደዋል። 700 ሺህ ሰዎች ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ውስጥ በአሳሳቢ የረሀብ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት።»

በእርግጥም ድርቁ ከወትሮው ለመክፋቱ የቦሮናዎቹ አርብቶ አደሮች የቅርብ ማሳያዎች ይሆናሉ። ዳስ ከተባለው የቦረና ዞን ወረዳ ከነቤተሰባቸው ተፈናቅለው ርዳታ ለመጠየቅ የተዳረጉት ጉራ ጅርሞ የኑሯቸው ምሰሶ የነበሩት ከብቶቻቸው አልቀው አሁን በጣት የሚቆጠሩ ብቻ እንደቀሯቸው፤ የእነሱንም ዕጣ ፈንታ ለመናገር እንደሚቸግራቸው ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። እንደሳቸው ሁሉ ከኤልወዬ ወረዳ ቦረና ዞን የተፈናቀሉት ኢዳ ጉዮም እንዲሁ ዝናብ ጠብ ባለማለቱ የእሳቸውም ሆነ በጎረቤት ኬንያ ያሉት ወገኖች ሳይቀሩ ከብቶቻቸው እንዳለቁ ነው የገለጹት። የአርብቶ አደሮቹ ከብቶች በድርቁ ምክንያት ማለቃቸውን የዱብሉቂ ወረዳ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ተጠሪ የሆኑት አቶ ጃርሶ ቡሌም አረጋግጠዋል።

Ätrhiopien Dürre in der Guji-Zone
ድርቁ ያስከተለው ጉዳት በጉጂ ዞን ኢትዮጵያ ምስል DW

ቀደም ሲል በኦሮሚያ ክልል ስምንት ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ቆላማ አካባቢዎች የተከሰተውን የዝናብ እጥረት ተከትሎ ለችግር ለተዳረጉ ወገኖች ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን የክልሉ የአደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽነር ሙስጠፋ ከድሪ ለዶቼ ቬለ ገልጸው ነበር። የዝናቡ እጥረት አሁም በመቀጠሉ የችግሩን አስከፊነት እንዳባባሰው እና ለርዳታ ጥሪ መቅረቡንም ተናግረዋል።

የድርቁ ሁኔታ በሰሜን ኬንያ እና ሶማሊያም ተባብሶ መቀጠሉ ነው የሚነገረው። በኢትዮጵያ ሜቴሪዎሎጂ ተቋም መሪ ተመራማሪ እና የዋና ዳይሬክተሩ አማካሪ የሆኑት ዶክተር አሳምነው ተሾመ፤ ዝናብ የሚገኝበት ወቅት በሦስት እንደሚከፋፈል ያስረዳሉ። እሳቸው እንደሚሉትም በተለይ አሁን ድርቅ ተጠናክሮ የተከሰተባቸው የደቡብ ኢትዮጵያ አብዛኛ አካቢዎች በክረምት ዝናብ የሚያገኙ አይደሉም። ቦረናን ጨምሮ በደቡብ የሚገኙ አካባቢዎች የተሻለው የዝናብ ወቅታቸው በልግ ነው።

የዘንድሮው ክረምት በተመለከተ በአብዛኛው ጠንከር ያለ ዝናብ እና ቅዝቃዜ መኖሩ ይሰማል። የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ስዩም ጌቱ ዓለም አቀፍ የአየር ትንበያውን መሠረት አድርጎ ማብራሪያ የጠየቃቸው ዶክተር አሳምነውም ከሰኔ እስከ መስከረም በተለይ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ በአብዛኛው አካባቢዎች መደበኛ እና ከመደበኛውም በላይ የሆነ የዝናብ መጠን እንደሚኖር ትንበያው ቀድሞ መሰጡት ገልጸዋል። የበልግ ዝናብ ከጊዜ ወደጊዜ እየተዳከመ መሄዱን የተደጋገሙት ክስተቶች እያሳዩ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።

Äthiopien Konsso | Wassermangel
ኮንሶ ምስል Konso Development Association

አሁን በአፍሪቃው ቀንድ አካባቢ እንደሚታየው የዝናብ እጥረቱ በአውሮጳም ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ መባባሱን ከሳምንታት በፊት ማንሳታችን ይታወሳል። የአካባቢ ተፈጥሮ ይዞታን በቅርበት የሚከታተሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ክስተቱን ከአየር ንብረት ለውጥ እንደሚያያዝ ይናገራሉ።

የዓለም ሜቴሪዎሎጂ ድርጅት ከጥቅምት እስከ ታኅሣስ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪቃ ቀንድ ሃገራት የዝናብ እጥረቱ ቀጥሎ ድርቁን ሊያባብስ እንደሚችል አመላክቷል። አሁን ለምግብ እጥረት እና ተያያዥ ችግሮች የተዳረጉ ወገኖች ኹኔታም ወደከፋ ቀውስ እንዳይሸጋገር ተሰግቷል። እንዲህ ቅድመ ትንበያዎች መነገራቸው ከወዲሁ ሊደረጉ ለሚችሉ ዝግጅቶች እንዲበጅ ነውና የድርቁ ተጽዕኖ ብዙዎችን እንዳይጎዳ መጠንቀቁ ይመከራል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ