1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድሕረ ሕወሓቶቹ ኢትዮጵያና ትግራይ

ሰኞ፣ ኅዳር 21 2013

ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ዛሬ ለምክር ቤት አባላት እንደገለፁት ስልጣን «በሰላም አስረከቡ» በተባሉት በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ መሪዎችና በነሱዉ ፍቃድና ይሁንታ ሥልጣን በያዙት ወገኖች መካከል ሽኩቻ፣ሻጥርና ጥልፍልፉ የከረረዉ ከስልጣን ርክክቡ ማግስት ጀምሮ ነዉ

https://p.dw.com/p/3m2Kt
Äthiopien Tigray | Hauptstadt Mekele | TPLF-Zentrale
ምስል EDUARDO SOTERAS/AFP/Getty Images

የድሕረ ሕወሓቶቹ ኢትዮጵያና ትግራይ

 

የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መሪዎች ዛሬም እንደ ጥንቱ እንዋጋለን እያሉ ነዉ።የፓርቲያቸዉ የ46 ዘመን የትግል፣ የገዢነት፣ የግጭት ጦርነት ታሪክ ግን በጦርነት፣ ከታሪክ ወመዘከር ሊቀመጥ ከመጨረሻዉ መጀመሪያ  ላይ የደረሰ መስሏል።የኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግሥት ጦር ትግራይ ዉስጥ የከፈተዉን ወታደራዊ ዘመቻ ማጠናቀቁን አስታዉቋል።ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት መግለጫና ማብራሪያ ደግሞ ትግራይ ዉስጥ ከሶስት ሳምንት በላይ ያዋጋዉ ጠብ  ከሁለት ዓመታት በላይ ዉስጥ ዉስጡን ሲትመከመክ የነበረ ሽኩቻ፣ፍትጊያና ሴራ ዉጤት መሆኑን አስታዉቀዋል።የወታደራዊ ዘመቻዉ ዉጤት መነሻ፣ የምክንያቱ ፍትሐዊነት ማጣቃሻ የእንግዲሁ ፖለቲካዊ ጉዞ መድረሻችን ነዉ።ሁለት እንግዶች አሉን። 

ኢትዮጵያ ብዙዎች እንደሚሉት በጦርነት የኖረች፣ በጦርነት ገዢዎችን ስትቀያይር ዘመናት ያስቆጠረች ጥንታዊት ሐገር ናት።በቅርብ ዘመን ታሪኳ እንኳን ልጅ እያሱን በንግስት ዘዉዲቱ ኋላም በአፄ ኃይለስላሴ የቀየረችዉ «የቤተ-መንግሥት» በተባለ መፈንቅለ መንግስት፣ በጥቅምት 1909 ሰገሌ ላይ በተደረገ ዉጊያ ነበር።

የአፄ ኃይለ ስላሴ ዘዉዳዊ አገዛዝ በደረግ የተቀየረዉ «ተንፏቃቂዉ ወይም የሚድኸዉ» መፈንቅለ መንግሥት በተባለዉ ሴራና በየስፍራዉ በተደረጉ ግጭቶች ነዉ።የደርግ ወይም የኢሠፓ መንግስት በኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት የተለወጠዉም በጦርነት ነዉ።

በየመንግስት ለዉጡ ሥልጣን የጨበጡት ኃይላት መበረ ሥልጣናቸዉን ያደላደሉት ደግሞ የየቀዳሚዎቻቸዉን ባለስልጣናት፣ ደጋፊ፣ አባሪ፣ ተባባሪዎቻቸዉን አንድም ገድለዉ፣ ሁለትም አስረዉ፣ ሶስትም አስኮብልለዉ  ነዉ።

መጋቢት 2010 የተደረገዉ ለዉጥ ግን ከቀዳሚዎቹ ሁሉ የተለየ ሰላማዊና የጨዋ መስሎ ነበር።የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችም ከጦርነት፣ ግጭት፣ ሽኩቻ ወደ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የመለወጣቸዉ ብስለት፣ አስተዋይነታቸዉ አብነት ተደርጎ ብዙ ተወድሶ ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ አትርፎም ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ዛሬ ለምክር ቤት አባላት እንደገለፁት ግን በይፋ የተባለና የተነገረዉ በገቢርና ከዉስጥ ከነበረዉ ዕዉነታ ጋር  የሚጣጣም አልነበረም።ስልጣን «በሰላም አስረከቡ» በተባሉት በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ መሪዎችና በነሱዉ ፍቃድና ይሁንታ ሥልጣን በያዙት ወገኖች መካከል ሽኩቻ፣ሻጥርና ጥልፍልፉ የከረረዉ ከስልጣን ርክክቡ ማግስት ጀምሮ ነዉ።ከጦር ኃይሉ ጡንጫ-እስከ ስለላዉ-ሴራ፣ ከምጣኔ ሐብቱ ሻጥር እስከ ፖለቲካ ዲፕሎማሲዉ የነበረዉ መሳሳብም ለዉጡ ከቀዳሚዎቹ አለመለየቱን መስካሪ ነዉ።

Äthiopien Mekelle | Tigray Wahlkomission Logo
ምስል DW/M. Haileselassie

ባለፈዉ ጳግሜ ማብቂያ ትግራይ ዉስጥ የተደረገዉ ክልላዊ ምርጫ ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች እንዳሉት ዶክተር ዐብይ አሕመድ የሚመሩት የፌደራል መንግስትና ዶክተር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል የሚመሩት የትግራይ ገዢ ፓርቲ ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ የገጠሙት ሽኩቻና መጠላለፍ ከማይታረቅበት ደረጃ መድረሱን ጠቋሚ ነበር።

እንደ ነባሩ ኢትዮጵያዊ ብሒል «ሁለት አዉራ አንድ ቆጥ ላይ አይሰፍርም።» ሁለቱን ወገኖች ለማግባባት የሐገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት መሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች ከአዲስ አበባ መቀሌ ተመላልሰዋል።ሁለቱ ወገኖች ልዩነታቸዉን በድርድር እንዲፈቱ የፖለቲካ አዋቂዎች፣ ሙሕራን፣ ዲፕሎማቶች ጭምር መክረዋል።የሰማ እንጂ የተቀበለ የለም።

የከፋዉ ደግሞ የመቀሌና የአዲስ አበባ መሪዎች መስከረም ማብቂያ አንዳቸዉ ለሌላቸዉ ሕጋዊ እዉቅና መፈንጋቸዉ ነበር።ባለፈዉ ጥቅምት ባሠራጨነዉ አንድ የዉይይት ዝግጅት ላይ የተከፈሉት የሕግ ባለሙያና የፌደራል ጉዳይ አጥኚ ዶክተር ለማ ይፍራ ሸዋ የኢትዮጵያን ሕገ-መንግስት ድንጋጌዎች ጠቅሰዉ «የፌደራሉ መንግሥት ሕግ የጣሱ ወገኖችን ለፍርድ ማብቀረብ አለበት» ዓይነት አስተያየት ሰጥተዉ ነበር።ዛሬስ?

                                    

የፌደራሉ መንግስት ጦርና የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ ላለፈዉ 3 ሳምንት ተኩል ያደረጉት ዉጊያ በሰዉ ሕይወት፤ አካልና ንብረት ላይ ያደረሰዉ ጉዳት እስካሁን በዝርዝር አልተነገረም።የተነገረዉ ማይ ካድራ ዉስጥ ከ600 በላይ በአብዛኛዉ የአማራ ተወላጆች በግፍ መገደላቸዉን የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ማስታወቁን ነዉ። የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅትም ከ43 ሺሕ የሚበልጡ ሰላማዊ ሰዎች ወደ ሱዳን መሰደዳቸዉን አስታዉቋልም።

በዉጊያዉ ወይም የፌደራል መንግሥት «ሕግን ማስከበር» ባለዉ ወታደራዊ ዘመቻ የደረሰዉ ጥፋት ከባድም ሆነ ቀላል ዶክተር ለማ ለዚሕ እርምጃ ምክንያት ያሉትን የሕግ ጥሰቶች ይዘረዝራሉ።

Tigray-Konflikt | Militär Äthiopien
ምስል Ethiopian News Agency/AP/picture alliance

የሕወሓት መስራች፣ የቀድሞ መሪና የሕዳሴ ግድብ የህዝብ ድጋፍ ማስተባበሪያ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር አረጋዊ በርሔ እንደሚሉት ደግሞ የፌደራዊ መንግስቱን ለወታደራዊ ርምጃ የገፋፋዉ የሕወሓት መሪዎች ሕግ ከመጣስ ባለፍ ለሽምግልና፣ ለድርድር፣ለአዋቂዎች ምክር ዝክርም እንቢኝ ማለታቸዉ ነዉ።ዶክተር አረጋዊ አክለዉ እንዳሉት ሕወሓትን የሽምቅ ተዋጊ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ የሚመሩት ኃይላት ከአንድነት ይልቅ መገንጠልን፣ከዴሞክራሲያዊነት ይልቅ አምባገነናዊነትን፣ ከድርድር ይበልጥ በኃይል መታበይን የሚያስቀድሙ ናቸዉ።

የቀድሞዉ የትግራይ ምክትል ርዕሠ መስተዳድር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል ዛሬም ከተተሸሸጉበት እንዋጋለን እያሉ ነዉ።ዶክተር ደብረ ፅዮንን በስልክ ማነጋገሩን የገለፀዉ የአሜሪካ ዜና አገልግሎት አሶስየትድ ፕረስ ዶክተር ብረፅዮን «እናሸንፋለን» ማለታቸዉን ጠቅሷልም።ከሐገር መሪነት ወደ ክልል ገዢነት፣ ከክልል ገዢነት እንደ ቅድመ 30 ዓመቱ ወደ ሽምቅ ተዋጊነት ያሽቆለቆለዉ ሕወሓት በርግጥ መሪዉ እንዳሉት ዓይነት ይሆን? ዶክተር አረጋዊ አይሆንም ባይ ናቸዉ። ዶክተር ለማ ደግሞ ሕወሓት ኖረም ሞተ «በአሸባሪነት መፈረጅ አለበት» ባይ ናቸዉ።

ሕወሓት ፈረሰ፤ ወደ ሽምቅ ተዋጊነት ተቀየረ ተባለ፣ ሞተም የከእንዲሁ የኢትጵያ ፖለቲካዊ ሒደት በጣሙን ሕወሓት እንደ ሸማቂ ቡድንም፣ እንደ መንግስትም፣ እንደ ክልላዊ ፓርቲም ለ46 ዓመታት የገዛት የትግራይ ፖለቲካዊ-ምጣኔ ሐብታዊ-ማሕበራዊ ሁኔታ በርግጥ ያነጋግራል።ከሁለቱ ተንታኞች ጋር በተናጥል ያደረግነዉን ሙሉ ቃለ መጠይቅ መስማት የምትፈልጉ አምደ መረባችንን መጎብኘት ትችላላችሁ።

ነጋሽ መሐመድ 

ሸዋዬ ለገሠ