1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዳርፉር ጉዳይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት

ረቡዕ፣ ነሐሴ 17 1998

ምዕራብ ሱዳን ከሚገኙት የስደተኞች መጠለያዎች አንዱ የምዕራባዊትዋ ሱዳን የዳርፉር ችግር ተባብሶ ቀጠለ እንጂ የተሻለ ነገር አልመጣም ።

https://p.dw.com/p/E0iG
ምስል AP

የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክርቤት በመጪው ሰኞ በዳርፉር ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለመነጋገር ቀጠሮ ይዟል ። በዚሁ ስብሰባ ላይም የአረብ ሊግ ፣ የእስልምና ጉባኤ ድርጅት ፣ የሱዳን መንግስት ና የአፍሪቃ ህብረት እንዲገኙ ተጋብዘዋል ። በሌላ በኩል ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታኒያ ቁጥሩ አስራ ሰባት ሺህ የሚደርስ ዓለም ዓቀፍ ሰላም አስከባሪ ሀይል በዳርፉር እንዲሰፍር የጠየቁበትን ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ ባለፈው ሳምንት ለፀጥታው ምክርቤት አቅርበዋል ። የሱዳን መንግስት አሁንም የተባበሩት መንግስታት ሀይሎች በሱዳን ከሰፈሩ ወታደሮቹን አጠቃለሁ በሚለው አቋሙ እንደፀና ነው ። የተባበሩት መንግስታት ወታደሮችን በዳርፉር በማስፈሩ ጉዳይ ላይ ውዝግቡ በዚህ መልኩ በቀጠለበት በአሁኑ ሰዓት የዳርፉር ፀጥታና ሰብዓዊው ሁኔታ የከፋ ደረጃ ላይ መሆኑ እየተገለፀ ነው ። የዶይቼቬለው Rainer Sütfeld ከኒውዮርክ የላከውን ዘገባ ሂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች ።
የዳርፉሩ የሰላም ስምምነት በመንግስትና በአማፅያን ከተፈረመ በኃላ የምዕራባዊትዋ ሱዳን የዳርፉር ችግር መቃለያው ጊዜ የተቃረበ መስሎ ነበር ። ይሁንና አሁን ከተባበሩት መንግስታት ሀላፊዎች እንደሚሰማው ችግሩ ተባብሶ ቀጠለ እንጂ የተሻለ ነገር አልመጣም ።
“አንድ በጣም አስከፊ የሆነ ነገር እዚያ እየተብላላ ነው ። እንደምታውቁት የዳርፉር ሰብዓዊውና የፀጥታው ሁኔታ እየከፋ መሄዱ እንዲሁም በአካባቢው የተባበሩት መንግስታት ወታደሮችን ለማስፈር ግልፅ የፖለቲካ አቅጣጫ አለመኖሩ እጅግ በጣም ያሰጋናል ። በጣምም ያሳስበናል ። ክቡራትና ክቡራን እባካችሁ ዳርፉርን አትርሱ !”
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሀፊ ማርክ ማሎክ ብራውን ስለ ዳርፉር ያሰሙት የተማፅኖ ንግግር ነበር ። ከብራውን ንግግር መረዳት እንደሚቻለው የዳርፉር ችግር ወደባሰ ደረጃ ተሸጋግሯል ። የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሀፊ ኮፊ አናን በሀምሌ መጨረሻ ላይ በምዕራብ ሱዳን ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ ለማድረግ እዚያ የተሰማራው የአፍሪቃ ህብረት ሀይል በዓለም ዓቀፍ ሀይል ይተካል ብለው ካሳወቁ ወዲህ የተንቀሳቀሰ ነገር የለም ። አሁን ያለው ተጨባጩ ሁኔታ ተቃራኒ ነው ። በስደተኞች መጠለያ ሰፈሮች የምግብ ዕጥረት አለ ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለስደተኞች የሚሰጠውን የምግብ መጠን ቀንሷል ። ምክንያቱ በቂ ገንዘብ መታጣቱ ነው ። በሌላ በኩል ዳርፉር የሚገኘው የአፍሪቃ ህብረት ሀይል ጉዳይም ያለአንዳች ውሳኔ እንደተንጠለጠለ ነው ። የዚህ ሀይል ተልዕኮ መስከረም ላይ ያበቃል ። በዳርፉር አሁንም የአማፅያኑ ጥቃት አልቆመም ። ባለፉት ወራት አስራ አንድ የዓለም ምግብ ድርጅት ሰራተኞች በአማፅያን ተገድለዋል ። ዳርፉር ውስጥ ያለው ሁኔታ ይህ ሲሆን የፀጥታው ምክርቤትም የዳርፉርን ጉዳይ አልዘነጋውም ። ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታኒያ አስራ ሰባት ሺህ የሰላም አስከባሪ ኃይል ዳርፉር እንዲዘምት ያቀዱበትን አዲስ ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ ለፀጥታው ምክርቤት አቅርበዋል ። የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር ግን ዓለም ዓቀፍ ሀይል በዳርፉር መስፈሩን አሁንም እንደተቃወሙ ነው ። የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ኀይል ሱዳን ከተላከ እናጠቃለን ብለዋል ። በቅርቡ ደግሞ አልበሽር ዳርፉርን ለማረጋጋትና ሰላማዊ ሰዎችን ከጥቃት ለመከላከል መንግስታቸው ያወጣውን ዕቅድ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ ለኮፊ አናን ልከዋል ። አናን እንዳሉት በዚህ የሱዳን መንግስት ሀሳብ ውስጥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዳርፉር ላቀደው ዘመቻ የሱዳንን ፈቃደኝነት የሚያሳይ አንዳችም ምልክት የለም ። ይልቁንም የሱዳን መንግስት ዕቅድ አስር ሺህ የሚደርሱ የሱዳን ወታደሮችን በአካባቢው በማሰማራት ዳርፉርን የማረጋጋት ሀሳብ ነው ያቀረበው ። ይህን የሱዳን ሀሳብ ስደተኞች ፣ የሰብዓዊ መብት ተምዋጋቾቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩመን ራይትስ ዋች አሸባሪ ዕቅድ ነው ያሉት ። እንደርሱ አስተያየት ዕቅዱ ደም አፋሳሽ ነው የሚሆነው ። ይህን ከመሰለው ስጋት መነሻነትም የዩናይትድ ስቴትስ አምባሰደር ጃኪ ዋልኮት ሳንደርስ የፀጥታውን ምክርቤት አባላትና ለሱዳን መንግስት ቅርበት ያላቸው መንግስታት ፕሬዝዳንት አልበሽርን ስለጉዳዩ ቢያሳምኑዋቸው የሚመረጥ መሆኑን አስታውቀዋል ።
“በፀጥታው ምክርቤት ውስጥ የሚገኙ አገራት በሙሉ እንዲሁም መንግስት ላይ ተፅዕኖ ማድረግ የሚችል ማንኛውም አገር ፕሬዝዳንቱን ለማግባባት የተቻለቸውን ግፊት እንዲያደርጉ እናበረታታለን ። ጉዳዩን ከየካቲት ወር አንስቶ ስናንቀሳቅስ ቆይተናል ። ከስድስት ወር በኃላ ግን በአካባቢው ግጭቱ እየተባባሰና ሰብዓዊው ሁኔታም እየከፋ ነው የሄደው ። እናም በዕውነቱ ይህን ጉዳይ ማንቀሳቀስ ይገባናል “ የዩናይትድ ስቴትስዋ ዲፕሎማት ይህን መፍትሄ ቢያቀርቡም የሱዳን መንግስት ዓለም ዓቀፉ ኃይል ሱዳን መስፈሩን በምንም መንገድ የሚቀበል አይመስልም ። የወቅቱ የፀጥታው ምክርቤት ፕሬዝዳንት የጋናው አምባሳደር ናና ኤፋ አፐንቴንግ እንዳሉት ደግሞ የካርቱም መንግስት እስካልተቀበለው ድረስ የተባበሩት መንግስታት ውሳኔ ተግባራዊ መሆን አይችልም ።