1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደ.አፍሪቃ ጠንካራ የውጭ ዜጎች ፍልሰት መቆጣጠሪያ ሕግ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 5 2007

ደቡብ አፍሪቃ በሕጋዊ እና ሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገሯ የሚገቡ የውጭ ዜጎች ቁጥር ለመቀነስ በማሰብ ባለፈው ዓመት አንድ ጠንካራ ሕግ አውጥታለች። ከብዙ ወራት ወዲህ የተጀመረው ሕጉን ተግባራዊ የማድረጉ ሂደት ግን ብዙ ቀውስ የታየበት እና በቱሪዝም እና ከውጭ በሚገባ ወረት ላይ አሉታዊ መዘዝ አስከትሏል።

https://p.dw.com/p/1Eqv9
Fremdenhass in Südafrika Flüchtling Fraser Kalikokha aus Malawi
ምስል picture-alliance/dpa


ሕጉ ኢትዮጵያዉያንን ጨምሮ ደቡብ አፍሪቃ በሚኖሩ የሌላ የአፍሪቃ ሀገራት ስደተኞችም ላይ ጥላቻው እንዲባባስ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ የመብት ተሟጋቾች ይናገራሉ። ይሁንና፣ የደቡብ አፍሪቃ ሀገር አስተዳደር ሚንስቴር ቃል አቀባይ ማይኽሎም ሽዌቴ ስራ ብለው ከዚምባብዌ እና ከሞዛምቢክ፣ እንዲሁም፣ በስደት ኢትዮጵያን ከመሳሰሉ ሀገራት ወደ ሀገሯ የሚገቡ የውጭ ዜጎችን ቁጥር የመቀነስ ዓላማ ይዞ የተነሳው የአዲሱ ሕግ አተረጓጎም ያን ያህል ችግር እንዳላስከተለ ነው የተናገሩት።

Südafrika Präsident Jacob Zuma
ምስል AFP/Getty Images/R. Bosch


« የሕጉ ተግባራዊነት ጥሩ እየተካሄደ ነው፣ እና እኛም እንደ አንድ አስፈፃሚ አካል ጉዳዩ ከሚነካቸው ጋ በመነጋገር ወደሀገራችን የሚገቡ የውጭ ዜጎችን ቁጥር ለመገደብ አምና በወጣው ሕግ አተረጓጎም ላይ የታዩ አንዳንድ ትናንሽ ችግሮችን ለማስወገድ የሚያስችል ማሻሻያ ለማድረግ እየሰራን ነው። ከውጭ ሀገር ኤምባሲዎች ፣ ከድጋፍ አፈላላጊ ቡድኖች እና በቱሪዝሙ ዘርፍ ከተሰማሩ ሰዎች ጋ ባንድነት እየሰራን ነው። »


ይሁንና፣ ካለፉት ስምንት ዓመታት ወዲህ በኬፕታውን የሚገኙት የጀርመን ትምህርት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ኸርማን ባትንበርግ የሽዌቴን አነጋገር በፍፁም አይጋሩም። ይኸው ችግር እንደሌሎቹ የውጭ ዜጎች፣ ጀርመናውያንንም እየጎዳ መሆኑን ነው ባትንበርግ የገለጹት። ባትንበርግ እስካለፈው ዓመት ድረስ ለማስተማር ስራ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለሄዱት ጀርመናውያን መምህራን ቪዛ ማውጣቱ ከሞላ ጎደል ችግር እንዳልነበረው ገልጸው፣ አዲሱ ሕግ ከወጣ ወዲህ ግን አዳጋች እየሆነ መምጣቱን ነው ያስታወቁት።

« እርግጥ፣ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለመግባት የሚያስችለውን ቪዛ ማግኘት ሁሌም አስቸጋሪ ነው። የዕድል ጉዳይ ስለነበር፣ መጨረሻ ላይ ቪዛው ይገኝ ነበር። አሁን ግን ቪዛ የማግኘቱ ነገር ላይሳካ የሚችልበት ስጋት ለመጀመሪያ ጊዜ ተደቅኖብናል»

Ausländerfeindlichkeit in Südafrika
ምስል DW


ከስራው እና ከንግዱ ዘርፍ እንደሚሰማው የውጭ ዜጎች በደቡብ አፍሪቃ የስራ ፈቃድ ለማግኘት በጣም ይቸገራሉ። ከ1,000 የሚበልጡ ሰራተኞችን ቀጥሮ የሚያሰራ የአንድ ጀርመናውያን ኩባንያ የፊናንስ ክፍል ኃላፊ ቪዛ ለማስመታት ከስድስት ወራት በላይ መጠበቅ እንደነበረባቸው፣ አንድ ሌላ ጀርመናዊ ባለተቋም በኬፕታውን ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ለመክፈት ሞክረው እንዳልተሳካላቸው በማስታወቅ ቅሬታቸውን ገልጸዋል። በደቡብ አፍሪቃ የስራ ልምምድ ማድረግ የሚፈልጉ ወጣት ጀርመናውያን እንደበፊቱ በቀላሉ ቪዛ አያገኙም፣ ምክንያቱም በአዲሱ ሕግ መሠረት ሀገሪቱ ይህን ዓይነቱን ቪዛ መስጠት አቁማለች። ከሰሀራ በስተደቡብ ላሉት የአፍሪቃ ሀገራት የተመደበው የጀርመናውያኑ የኢንዱስትሪ እና የንግድ ምክር ቤት ቡድን በርካታ ጀርመናውያን ተማሪዎች በደቡብ አፍሪቃ የስራ ልምምድ እንዲያደርጉ ቀደም ሲል ከተማሪዎቹ ጋ የደረሰውን ስምምነት፣ ምንም እንኳን ተማሪዎቹ ቲኬታቸውን ቢገዙም እና ለማረፊያቸውም ቢከፍሉ፣ መሰረዝ ግድ ሆኖበታል።


የቱሪዝሙ ኢንዱስትሪም በአዲሱ ሕግ ተፅዕኖ እንዳረፈበት እና ብዙ የማይመቹ ደንቦችን እንደያዘ በዚሁ ዘርፍ የተሰማሩት ገልጸዋል። ለምሳሌ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ይዘው ወደ ደቡብ አፍሪቃ መግባት የሚፈልጉ ሀገር ጎብኚዎች ወደ ሀገሪቱ ሲገቡ እና ሲወጡ ዓለም አቀፍ የልደት ሰነድ እንዲያሳዩ ሕጉ ይጠይቃል። ከ18 ዓመት በታች የሆነ ሕፃን ወይም ወጣት ከንዱ ወላጁ ጋ ብቻ የሚጋዝ ከሆነም፣ በጉዞው ላይ የሌለውን ወላጁን ስምምነት የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ማቅረብ ይጠበቅበታል። ይህ በሕገ ወጥ መንገድ የሚደረገውን በሕፃናት የመነገዱን ወንጀል ለመከላከል የታሰበ መሆኑን ነው የአዲሱ ሕግ አስፈፃሚዎች ያስረዱት። የአየር መንገዶች እና የጉዞ ወኪሎች ቀደም ሲል በቀረቡት ደንቦች አንፃር ተቃውሟቸውን ካሰሙ በኋላ የሀገር አስተዳደሩ ሚንስቴር ደንቦቹን እንደገና ለማጤን መወሰኑን ማይኽሎም ሽዌቴ አስታወቀዋል።


« ወደ ሀገራችን የሚመጡ የውጭ ዜጎች ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆቻቸውን የልደት ሰርቲፊኬት ያቅረብ የሚለውን ደንብ እስኪቀበሉት ድረስ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ተረድተናል። ስለዚህ የዚህኑ ደንብ ተግባራዊነት እአአ ወደ ሀምሌ አንድ አዛውረነዋል። » እንደ ሀገር አስተዳደሩ ሚንስትር ማሉዚ ጊጋባ አስተያየት፣ በሕጉ ዙርያ የሚሰማው ተቃውሞ እንዳበቃ ሕጉ ካላንዳች ለውጥ ተግባራዊ ይሆናል።
ደቡብ አፍሪቃ ወደ ሀገሯ የሚገቡ የውጭ ዜጎች ቁጥር ለመቀነስ በማሰብ ያወጣችው ሕግ ከ650,000 ለሚበልጥ ሰው የስራ ዕድል በፈጠረው የቱሪዝም ዘርፍ ላይ፣ ባጠቃላይ በሀገሪቱ ኤኮኖሚ ላይ ትልቅ ጉዳት እንደሚያስከትል ጀርመናዊው ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ኸርማን ባትንበርግ አስጠንቅቀዋል።

Südafrika Demonstration gegen Gewalt an Ausländern
ምስል AP


« ብዙ የውጭ ዜጎች አዲሱ ሕግ የሚጠይቀውን ደንብ ለማሟላት ፈቃደኞች በማይሆኑበት ወይም አንድ በደቡብ አፍሪቃ የሚገኝ የውጭ ኩባንያ ከውጭ ሰራተኛ ማስገባት በማይችሉበት ጊዜ ከሀገሪቱ የሚርቁበት ድርጊት ሀገሪቱን ብዙ ገንዘብ ያሳጣታል፣ ብዙ የስራ ቦታንም ያጠፋል »

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ