1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግጭቱ መዘዝ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 26 2010

ካለፈዉ ጥፋት ከመማር ይልቅ ጥፋቱን መልሶ መድገሙ አጓጉል ፈሊጥ ሆኖ ሶማሌ-ከኦሮሞ፤ ኦሮሞ- ከአራማራ፤ አማራ ከትግሬ፤ በርታ፤ ከአማራ፤ጉጂ ከጌድኦ ሲጋደሉ ሐዋሳ እና ብጤዎችዋ የመግባባት-መቻቻል አብነት፤ ከሁሉም በላይ የዘመኑ ስልጣኔ ምሳሌ መስለዉ ነበር።

https://p.dw.com/p/30hCT
Äthiopien Wald
ምስል Imago/imagebroker/auth

የደቡብ ኢትዮጵያ ግጭት

ለከተማ ዕድሜ በርግጥ ወጣት ናት።ግን ከዕድሜዋ በላይ ፈጥናለች።አዋሳ ወይም ሐዋሳ።አልፎ አልፎ የድፍን ኢትዮጵያ፤ ዕለት በዕለት ግን ከሠሜን-ምሥራቅ ቡኢ እስከ ደቡብ ምዕራብ ኦሞራቴ የሚያካልለዉ ሠፊ ግዛት ፖለቲካ ሲቀመር-ሲሸረብ ሲተረተርባት የዕድሜዋን አጋማሽ አስቆጠረች። 27 ዓመት።የአዲስ አበባ ፖለቲከኛ፤ ሹም፤ ቱጃር፤ቆነጃጂት፤ ቀለል፤ዘና-ፈታ ማለት ሲያምራቸዉ ይሮጡባል።ከመልካሙ ተበጀ እስከነ ማሚላ ሲያወድሱ፤ ሲያሞግሱ፤ ሲያንቆለጳጵሷት ለሰማ ዉበት-ፅዳት ደግነቷን፤አስተናጋጅ-ቻይነትዋን ለማየት አለመጓጓት በርግጥ አይቻልም።ሰሞኑን ግን ማራኪ ስም-ዉበቷ-በአስከሬን፤ደም፤ሜዳላይ በፈሰሰ ነዋሪዋ ጎድፎባታል።ቻይ አስተናጋጅነቷ።ጠፍቶ ወይም ተቀብሮ የዘር ጥላቻ ዛር ያስጓራታ።አዋሳ-እንደ ድሮዉ።ለምን? አብረን እንጠይቅ።

Karte Äthiopien englisch

                               

መቶ ሚሊዮን ሕዝብ፤ ሰማንያ ጎሳ፤ ዉስን ሐብት-እና ዘመናይ እዉቀት በተሰባጠሩባት ኢትዮጵያ ጎሳ ሰበብ ላደረገ ጠብ፤ግጭት ግድያ በርግጥ እንግዳ አይደለችም።የመሾም-መሸለም፤ የመክበር-መከበር-መጠቀሙ መሠረት ዘር እና ጎሳ የመሆኑ ፖለቲካ ሲቀነቀንባት ደግሞ ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚስማሙበት ወትሮም እንግዳ ያልሆነዉ ጠብ፤ግጭት መናሩ እርግጥ ነዉ።

ባለፉት ዓመታት በደኖ፤ አርባ ጉጉ፤ ቤኒሻንጉል፤ ጉራ ፈርዳ ሌላም ሥፍራ በዘር እና ጎሳ ሰበብ የፈሰሰዉ ደም፤የተፈናቀለዉ ሕዝብ፤ የጠፋዉ ሐብት እና ንብረት ሌላ ሥፍራ ተመሳሳይ ጥፋት እንዳይፈጠር አስተማሪ በሆነ ነበር።አልሆነም።ካለፈዉ ጥፋት ከመማር ይልቅ ጥፋቱን መልሶ መድገሙ አጓጉል ፈሊጥ ሆኖ ሶማሌ-ከኦሮሞ፤ ኦሮሞ- ከአራማራ፤ አማራ ከትግሬ፤ በርታ፤ ከአማራ፤ጉጂ ከጌድኦ ሲጋደሉ ሐዋሳ እና ብጤዎችዋ የመግባባት-መቻቻል አብነት፤ ከሁሉም በላይ የዘመኑ ስልጣኔ ምሳሌ መስለዉ ነበር።

አንድ የከተማዋ ነዋሪ  በቀደም እንዳሉት ግን ባጭር ጊዜ ዉስጥ ከኢትዮጵያ ትላልቅ ከተሞች የሰወስተኛነቱን ደረጃ የያዘችዉ ከተማ ወትሮም ቢሆን አስመሰለች እንጂ የዘር ጥላቻ፤ ግጭት፤ጥፋት ተለይቷት አያዉቅም።                         

                               

የፖለቲካ ተንታኝ አቶ መድሕን ማርጮም በዓል በተከበረ ቁጥር ዘርን ከዘር ለይቶ ማንጓጠጥ ዘንድሮ ብቻ የተከሰተ ዓይደለም ይላሉ።የዘንድሮዉ ግን በርግጥ የከፋ ነዉ።ያዩ እንደሚሉት ከሁለት ሳምንት በፊት በአብዛኛዉ በወላይታ፤ በጥቂቱም ቢሆን በጉራጌ እና በሌሎች ጎሳ አባላት ላይ የዘመተዉ የሲዳማ ተወላጅ ሰዎችን በእሳት አጋይቶ፤ በዱላ ቀጥቅጦ ገድሏል። የፊጥኝ እያሰረ መሬት ለመሬት ጎትቷል።የደረሰዉን ግፍ አቶ መድሕን  ኃይማኖትም፤ ባሕልም፤ ዘመናይነትም ያልገራዉ ይሉታል።አሳፋሪ።

2 Berta.jpg
ምስል DW

                                

የተገደለዉ ሰዉ ቁጥር በትክክል አይታወቅም።ሐዋሳ ከተማ ዉስጥ ብቻ  ሲያንስ 6፤ ሲበዛ 28 ሰዉ ተገድሏል የሚሉ አሉ።ከ27 ሺሕ በላይ የሐዋሳ ነዋሪ ተፈናቅሏል።ሐዋሳ ላይ የተቀጣጠለዉ ግጭት ወላይታ ሶዶ፤ ሻመና፤ ለኩ ከተሞች እና ወደ ሌሎች ትናንትሽ ከተሞች ተዛምቶ ተጨማሪ ሕይወት አጥፍቷል።የሻመና ነዋሪ ፓስተር ሙላቱ ጋርጆ እንደሚሉት ሻመና ዉስጥ ግጭቱ በተነሳበት ዕለት ብቻ አምስት ሰዉ መገደሉን አይተዋል።የጅብ ሲሳይ የሆነም አለ ባይ ናቸዉ-ፓስተሩ።

                                      

ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት ሻመና ከተማ ዉስጥ የሚደርስባቸዉን ጥቃት ሸሽተዉ ኦሮሚያ መስተዳድር ምዕራብ አርሲ ዞን ሲራሮ እሚባል አካባቢ የሰፈሩ የወላይታ ተወላጆች  ከ11 ሺሕ አምስት መቶ አባወራዎች ይበልጣሉ።ቤት ንብረታቸዉን ጥለዉ ለሸሹት ሰዎች እስካሁን ድረስ የተደረገላቸዉ ድጋፍ የለም።                               

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ አካባቢዉን በጎበኙበት ወቅት ግጭቱን የቀሰቀሱ ወይም ለማስቆም ያልጣሩ ባለሥልጣናት ሥልጣናቸዉን እንዲለቁ ባሳሰቡት መሠረት የተለያዩ አካባቢዎች ባለሥልጣናት ከስልጣን መልቀቃቸዉን አስታዉቀዋል።ደቡብ ክልልን የሚያስተዳድረዉ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ሊቀመንርን ጨምሮ የፓርቲዉ ባለስልጣናት በሌላ ተተክተዋል።

ግጭቱም ባለፈዉ ሳምንት ረገብ ብሏል።ዉጥረቱ ግን የሐዋሳዉ ነዋሪ እንደሚሉት አሁንም እንደናረ ነዉ።የከተማዋ ባለስልጣናት ከቤት ንብረታቸዉ በተፈናቀሉት ነዋሪዎች ላይ የሚሰነዝሩት ዛቻ እና ማስፈራሪያም አልተቋረጠም።በየዓመቱ ላጭር ጊዜ ብልጭ ብሎ በተወሰኑ ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሶ የሚዳፈነዉ ግጭት ዘንድሮ የከፋ ጉዳት ያደረሰበት ምክንያት ኢትዮጵያ ዉስጥ ባለፉት ጥቂት ወራት የሚደረጉ ለዉጦች ያሳጋቸዉ ወገኖች ሥላቀጣጠሉት እንደሆነ ታዛቢዎች ይናገራሉ።አካባቢዉን የሚያዉቁት አቶ መድሕን ማርጫ ግን  አብዛኛዉ ታዛቢ ከሚለዉ ለየት ያለ አስተያየት አላቸዉ።

                              

ፓስተር ሙላቱ እንደሚያምኑት በተለይ የሲዳማ እና የወላይታ ተወላጆች ጠብ ቁርቁስ ተለይቷቸዉ አያዉቁም።የዚያኑ ያሕል ተጋብተዉ የተዋለዱ፤ አብረዉ ኖረዉ የተዛመዱ እና የሚግባቡ ናቸዉ።እስከ ቅርብ ጊዜ ዓመታት ድረስ የተከሰቱ ግጭቶች የከፋ ጉዳት ሳያደርሱ የሚስክኑት በሕዝቡ መካከል ጥንካራ ትስስር ሥለነበረ-ነበር።

የቀድሞዉ የሲዳማ ጠቅላይ ግዛት ወይም ክፍለ-ሐገር ከሌሎች የአካባቢዉ አስተዳደሮች ጋር ተደፍልቆ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች መስተዳድር ከተመሰረተ ወዲሕ ግን ፓስተሩ እንደሚሉት ግጭቱን የሚያባብስ እንጂ የሚያበርድ ኃይል አልታየም።በተለይ ሲዳማ ፖለቲከኞች የሲዳማ ሕዝብ ከሌሎቹ ተነጥሎ አሁን በዞን ደረጃ ያለዉ መስተዳሩ ሐዋሳን ርዕሠ-ከተማ ያደረገ ክልል መመስረት አለበት የሚል መርሕ ማራመድ እና ሕዝቡን መቀስቀስ ከጀመሩ ወዲሕ ግጭቱ ተባብሷል።

Äthiopien Gambella Flüchtlingscamp
ምስል Reuters/D. Lewis

                         

አቶ መድሕን እንደሚሉት ደግሞ የሲዳማዎች የክልል ጥያቄ ለግጭቱ መክፋት አንዱ ምክንያት ነዉ።የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ኢሕአዴግ የሚከተለዉ በጎሳ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ሥርዓት የአንዱ ጎሳ ተወላጅ ከሌላዉ ጋር የተሳሰረበትን አብሮ የመኖር ይትበሐል ሰብሮታል።አቶ መድሕን ሌላም ምክንያት አላቸዉ።ደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ተፋቅረዉ የሚኖሩባት ትንሺቱ ኢትዮጵያ ብሎ አባባል ለአቶ መድሕን ዉሸት ነዉ።አካባቢዉን ለ27 ዓመታት የገዛዉ የደኢሕዴን መሪዎች የጎሳ ስብጥር፤ የክልሉ ርዕሠ መስተዳድሮች ፍርርቅ የየመስሪያ ቤቱ ሹማምንት ማንነት የጎሳ ፖለቲካዉን አጡዞ ደቡብ ኢትዮጵያ የተጨናገፈ አስተዳደር (FAILED STATE) አብነት አድርጎታል።

                              

የሐዋሳ አወቃቀር እና የየመስሪያ ቤቶችዋ ሠራተኞች ማንነት  አቶ መድሕን የጨነገፈ ያሉትን አስተዳደር ለማስረገጥ ተጨማሪ ምክንያት ያደርጉታል።ዉጤቱ ደግሞ ማቆሚያ ያጣ ደም አፋሳሽ ግጭት።ሰሞኑን በተከሰተዉ ግጭት ኃላፊነታቸዉን በአግባቡ አልተወጡም የተባሉ የወላይታ ሶዶ ዞን ባለሥልጣናት ሥልጣን ለመልቀቅ ወስነዋል።በግጭቱ የተጠረጠሩ ሰዎች መያዛቸዉንም የደቡብ ኢትዮጵያ መስተዳድር ባለሥልጣናት ተናግረዋል።የሐዋሳ ነዋሪዎች እንደሚሉት ግን ግጭቱን ያሴሩ እና ያቀነባበሩት ባለሥልጣናት ዛሬም በነበሩበት ስልጣን ላይ ናቸዉ። ሰዎች ሲገደሉ ሲደበደቡ፤ ሲፈናቀሉ፤ ቤታቸዉ ሲጋይ እና ሲዘረፍ እጁን አጣምሮ ይመለከት የነበረ ፀጥታ አስከባሪንም የነካዉ የለም። 

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ