1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን ስጋት እና ተስፋ

ሐሙስ፣ መጋቢት 10 2007

በምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት /ኢጋድ/ አማካኝነት ሲካሄድ የከረመው የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ሃይሎች ድርድር አለመሳካቱን ተከትሎ በአገሪቱ ሁለት ግዛቶች ተቀስቅሶ የነበረው ግጭት ወደ ሌሎች አራት ግዛቶች መስፋፋቱን የአገሪቱ ባለስልጣናት አረጋግጠዋል። ግጭቱ በተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች ነዋሪዎች ቀያቸውን ጥለው እየተሰደዱ ነው።

https://p.dw.com/p/1Eu6O
Bürgerkrieg und Hungersnot im Südsudan
ምስል Ali Ngethi/AFP/Getty Images

የደቡብ ሱዳን ፖለቲካን የሚታዘቡ ተንታኞች በአገሪቱ ለሚመሰረት የሽግግር መንግስት ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ተቀናቃኛቸውን ሪየክ ማቻርን ያካት አያካት እያከራከረ ነው።

የደቡብ ሱዳንን ፖለቲካ የሚከታተሉ ተንታኞች ሰሞኑን በተቀሰቀሰው ውጊያ ላይ ሊመክሩ ረቡዕ መጋቢት/9/2007 ዓ.ም. በኬንያዋ ዋና ከተማ ናይሮቢ ተሰይመው ነበር። በተንታኞቹ ውይይት ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ተቀናቃኛቸው የአማጺ መሪ ሪየክ ማቻር አዲስ በሚቋቋም መንግስት ውስጥ ሊካተቱ ይገባል ወይ የሚለው ጥያቄ ዋንኛ ጉዳይ ሆኖ ነበር። በአፍሪቃ ጥናት እና መረጃ ማዕከል (African Research and Resource Forum) የናይሮቢ ቢሮ ባልደረባ እና የደቡብ ሱዳን ተንታኝ የሆኑት ዳልማስ ኦቺየንግ ሁለቱን ሰዎች ማግለል መፍትሄ ነው ብለው አያምኑም።

«መራጮቻቸው መሪዎቻቸው ሲገለሉ አይቀበሉም። ምክንያቱም መሪዎቹ የተወሰነ ተቀባይነት አላቸው። ስለዚህ ለምን እንደሚገለሉ ማሳመን ካልተቻለ ግጭቱ ሊባባስ ይችላል።»

Südsudan Juba Militär 02/2015
ምስል picture-alliance/AA/S. Bol

በዩናይትድ ይቴትስ አለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲ የናይሮቢ ቅርንጫፍ የህግ ተማሪ የሆነችው አያክ አቦት ካለ ኪር እና ማቻር ከስምምነት መድረስ ይቻላል የሚል እምነት የላትም።

«የሚሆን አይመስለኝም። እነዚህ መሪዎች በቦታቸው ሆነው መቀጠል ይኖርባቸዋል። ባህላዊውን የአስተዳድር መዋቅር ብትከተል በመሪነት ላይ የሚገኙት እነዚህ ሰዎች ናቸው። እነዚህን ብታስወግድ የሚተካቸው አይኖርም። ግጭትም ይቀሰቀሳል።»

መሰረቱን ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ያደረገው የፀጥታ ስልታዊ ጥናት ተቋም (Institute of Strategic Studies) የግጭት መከላከል አጥኚው ኢማኑኤል ኪሳንጋኒ በሁለቱ ሃሳብ ፈጽሞ አይማሙም። በእሳቸው አባባል ኪርም ሆኑ ማቻር በቡብ ሱዳን ወደ ፊት በሚቋቋም መንግስት ውስጥ ቦታ ሊኖራቸው አይገባም።

«ሁለቱ ሰዎች ቦታቸውን ገለልተኛ ለሆነ መሪ ቢለቁ የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ። ይህ ለመናገር እንጂ ለማድረግ ከባድ ነው። ምክንያቱም ፕሬዝዳንቱ ቢሮዎን ይልቀቁ ቢባሉ ያላጠናቀኩት የስልጣን ዘመን አለ የሚል ክርክር ያቀርባሉ።»

የደቡብ ሱዳን የህግ ባለሙያዎች ማህበረሰብ ኃላፊ እና አጥኚ የሆኑት ዴቪድ ዴንግ በውይይቱ ላይ በግጭቱ ምክንያት የተፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ ላይ ማተኮርን መርጠዋል።

Kenia Teilnehmer eines Sicherheitsseminars in Nairobi
ምስል DW/J. Shimanyula

«ጦርነቱ የሰብዓዊ ቀውስና ሞት ብቻ ሳይሆን በደቡብ ሱዳናውያን ላይ አስከፊ ጠባሳ ጥሏል። ህይወት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከባድ እየሆነ ነው። አሁን በብዙዎች ዘንድ አሳሳቢ የሆነው ይህን ግጭት በተቻለ ፍጥነት እንዴት ማቆም ይቻላል የሚለው ይመስለኛል።»

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች በሆነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል የደቡብ ሱዳን አጥኘዋ ኤልዛቤጥ አሻሙ የኪር እና ማቻር ሃይሎች በአገሪቱ የሰብዓዊ መብት እየፈጸሙ መሆኑን ተናግረዋል።

«በግጭቱ በሁለቱም ወገኖች በሰዎች ላይ የምብት ጥሰት እና የጦርነት ወንጀል መፈጸሙን የሚያመለክቱ መረጃዎች አግኝተናል።»

በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት ጆሽ ኦኮት በአገራቸው ነባራዊ ሁኔታ የተሰማቸውን ለውይይቱ ታዳሚዎች እንዲህ አካፍለዋል።

«እንደ ደቡብ ሱዳናዊ በአገሪቱ በመካሄድ ላይ ባለው ግጭት ደስተኛ አይደለሁም። አገሪቱ ተከፋፍላለች። ሰዎችም እንደዛው ተከፋፍለዋል። ይህ ለአንድ አመት የዘለቀ ግጭት ለአዲሲቱ ሃገር አስከፊ ስም አሰጥቷታል። ቢሆንም እነዚህ መሪዎች ለሰላም እና በግጭቱ ለተጎዱ ሰዎች ሲሉ አንድ ቀን ሰላም ያወርዳሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።»

ጄምስ ሺማንዩላ/እሸቴ በቀለ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ