1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን መንግስት የጦር ወንጀል ፈጽሟል መባሉ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 16 2007

የደቡብ ሱዳን ጦር በዩኒቲ ግዛት አሰቃቂ ወንጀሎችን ይፈጽማል ሲል የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂዩማን ራይትስ ዎች ከሰሰ። ተቋሙ ይፋ ባደረገው አዲስ ዘገባ ከሚያዝያ ወር ጀምሮ የደቡብ ሱዳን መንግስት ጦርና ታጣቂዎች የግድያ፤ዘረፋ፤አስገድዶ መድፈር የመሳሰሉ ወንጀሎች ፈጽመዋል ሲል አትቷል።

https://p.dw.com/p/1G3tn
Südsudan Soldaten Rückeroberung Blue Nile Raffinerie
ምስል picture-alliance/AA

[No title]

የደቡብ ሱዳን መንግስት ጦርና ታጣቂ ሃይሎች ከባለፈው ሚያዝያ ወር ጀምሮ በዩኒቲ ግዛት አሰቃቂ ወንጀሎችን ፈጽመዋል ሲል የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሁማን ራይትስ ዎች ከሰሰ። ተቋሙ ባለፈው ረቡዕ ይፋ ባደረገው ዘገባ የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር መንግስት በተቀናቃኛቸው ቁጥጥር ስር በነበረችው የዩኒቲ ግዛት ላይ ጥቃት በፈጸመበት ወቅት የጦር ወንጀሎች ተፈጽሟል ሲል አስታውቋል። በሂዩማን ራይትስ ዎች የኬንያ ቢሮ ተመራማሪዋ ስካይ ዊለር ከሚያዝያ እስከሰኔ ወር በዘለቀው የመንግስት የጥቃት እርምጃ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ወንጀሎች መፈጸማቸውን ይናገራሉ።

« በተቃዋሚዎች ይዞታ ስር የሚገኙ አካባቢዎች ላይ መንግስት የወሰደው እርምጃ አስከፊ ነው። የመኖሪያ መንደሮች ተቃጥለዋል። የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተፈጽሟል። ንጹሃን ዜጎችም ተገድለዋል። እነዚህ የጦር ወንጀሎችና በንጹሃን ዜጎች ላይ በተከታታይ የተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች በግዳጅ የመኖሪያ ቀያቸውን ጥለው እንዲሰደዱ አድርጓል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግምት መሰረት ከ 100 ሺህ በላይ ሰዎች ቀያቸውን ጥለው ተሰደዋል።»

Südsudan-Verhandlungen vorerst gescheitert
ምስል Reuters/Jok Solomun

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ የደቡብ ሱዳን መንግስት ጦር ከጥቃቱ ለመሸሽ የሞከሩ ዜጎችን በታንክ እስከመጨፍለቅ እና መሞታቸውን በድጋሚ ማረጋገጥ፤በአደባባይ እንስቶችን በቡድን መድፈር እና ሰዎችን በቁማቸው የማቃጠል ወንጀሎችን ፈጽሟል ሲል በዘገባውአትቷል። ይህ ዘገባ ለአስራ ዘጠኝ ወራት በዘለቀው የደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚመዘግብ ነው ያሉት የተቋሙ አጥኚ ስካይ ዊለር የደቡብ መንግስት እና ደጋፊዎቹ በተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች ተሳትፎ ቀጥተኛ ማድረጋቸውን ይናገራሉ።

«የደቡብ ሱዳን ጦር አራተኛ ክፍለ ጦር ከቡሩን ጎሳ ታጣቂ ሚሊሺያዎች ጋር በመሆን ነው ጥቃቱ የተፈጸመው። ጥቃታቸው ያተኮረው በማዕከላዊ ዩኒቲ ግዛት ሲሆን እጅግ በርካታ ቃጠሎና አስገድዶ መድፈር የእንስቶች እገታ በበርካታ አካባቢዎች የተስፋፋ የቀንድ ሃብት ዘረፋ መኖሩን ተመልክተናል። በግዛቲቱ ደቡባዊ ክፍል ደግሞ በተለያዩ የመንግስት ጦር ክፍል በሚገኙ ወታደሮች አሰቃቂ ወንጀሎች ተፈጽመዋል። ወንጀሎቹ ግን በማዕከላዊ የዩኒቲ ግዛት እንደተፈጸሙት የከፉ አይደሉም።»

ጥቃቱ በተፈጸመባቸው የማዕከላዊ ዩኒቲ ግዛት አካባቢዎች ነዋሪዎችና ወጣቶች ራሳቸውን ለመከላከል ቢሞክሩም ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ስካይ ዊለር ተናግረዋል። ተቃዋሚዎች በአንዳንድ አካባቢዎች ከመንግስት ሃይሎች ጋር ውጊያ ገጥመውም ነበር ተብሏል።

ለ19 ወራት በዘለቀው የደቡብ ሱዳን ግጭት የመንግስትም ይሁን የተቀናቃኝ ሃይሎች ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ወንጀሎች ፈጽመዋል ያሉት ስካይ ዊለር ለደረሰው ጥፋት ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርም ይሁኑ የአማጽያኑ መሪ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል። አጥኚዋ የደቡብ ሱዳን ግጭት የጎሳ ልዩነትን ያካተተ በመሆኑ ከወታደሮችና ታጣቂዎች ተሻግሮ ወደ ከፋ የርስ በርስ ጦርነት ሊያመራ እንደሚችል ስጋታቸው ተናግረዋል።

በደቡብ ሱዳን የሚፈጸሙትን ወንጀሎች በተ.መ.ድ. አሜሪካና የአውሮጳ ህብረት ከጣሏቸው ማዕቀቦች በተጨማሪ በግጭቱ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸው ወገኖች የሚመረመሩበትና የሚዳኙበት ስርዓት እንደሚያስፈልግ ስካይ ዊለር አሳስበዋል።

አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው ፓርቲ አካል የሆነው የሱዳን ህዝቦች አርነት ጦር(SPLA) በአንድ ወቅት በነዳጅ ምርቷ በምትታወቀው የዩኒቲ ግዛት ላይ ጥቃት የከፈተው ከባለፈው ሚያዝያ ወር ጀምሮ ነበር። የሪየክ ማቻር ደጋፊዎችና ታጣቂዎችም በግዛቲቱ የአስገድዶ መድፈር፤ግድያና ህጻናትን ለውትድርና የመመልመል ወንጀል ይፈጽማሉ የሚል ክስ ይቀርብባቸዋል።

Südsudan Bentiu Soldaten der SPLA
ምስል DW

የግዛቲቱ ዋና ከተማ ቤንቱ በየጊዜው በሚካሄደው ጦርነት የወደመች ሲሆን ከ100 ሺህ በላይ ነዋሪዎቿ ውሎና አዳራቸውን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መጠለያ ጣቢያዎች አድርገዋል።

የደቡብ ሱዳን ግጭት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ ከ225,000 በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ሲፈናቀሉ 730,000 አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል። በሚቀጥለው ሰኞ በአፍሪቃ ህብረት ስብሰባ ላይ የሚገኙት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ከመሪዎች ጋር ከሚመክሩባቸው ጉዳዮች አንዱ የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ