1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ

ዓርብ፣ ጥር 1 2012

ቄለም ወለጋ ዞን የዶምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ  መሆናቸው የተገለጸ  ተማሪዎች መታገታቸው  እየተነገረ ነው። ዩኒቨርሲቲው መረጃው እንደደረሰው እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የፀጥታ እና የትምህርት ዘርፍ አካላት ማሳወቁን ለዶቼ ቬለ ገልጿል። የሳይንስ እና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም  ጉዳዩን እየተከታተልኩ ነው ብሏል።

https://p.dw.com/p/3W0aK
Äthiopien Bildungspolitik | Banner
ምስል DW/G. Tedla

«ከታገቱት አብዛኞቹ ሴት ተማሪዎች ናቸው»

ታገቱ የተባለው የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቁጥር በውል የታወቀ አይመስልም። ገሚሱ 17 ፤ ሌላው ቁጥራቸውን አራት ያደርገዋል። ቁጥራቸውን በርከት ያደረገው ወገን  ታግተዋል ከሚላቸው ተማሪዎች አብዛኛው ደግሞ ሴት ተማሪዎች መሆናቸውን ያመለክታል። ጉዳዩን  ለማጣራት ያነጋገርናቸው የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶክተር ለታ ተስፋዬ ድርጊቱ የተፈፀመው በዩኒቨርሲቲው አካባቢ ባለመሆኑ መረጃው እንደማንኛውም ወገን እንደደረሳቸው ነው የገለፁልን። በዚህም ምክንያት ታግተዋል የሚለውን ለማረጋገጥ እንደማይችሉም ጭምር። እሳቸው እንደሚሉት በዩኒቨርሲቲው በተፈጠረ አለመረጋጋት ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ጉዟቸውን በጋምቤላ መስመር ያደረጉ ተማሪዎች አሉ። ጉዳዩ በቀጥታ ከእነሱ ጋር ይገናኝ አይገናኝ ርግጠኛ ባይሆኑም መንገድ ላይ ያሉ ተማሪዎች በመኖራቸው ለሚመለከተው የፀጥታ እና የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ አካላት ማሳወቃቸውን አስረድተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማሩን ሂደት ያደናቀፈ የተደጋገመ ረብሻ ተከስቶ እንደነበር፤ ባለፈው ሳምንትም ተመሳሳይ ችግር እንደነበርም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ገልጸዋል። ሆኖም ከተማሪዎቹ ጋር በመነጋገር ትምህርት ለመጀመር ከስምምነት መደረሱንም አመልክተዋል።

የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለእገታ ተዳርገዋል የሚለው መረጃ እንደደረሰው ያመለከተው እና ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝ የሳይንስ እና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል። ከታገቱት አብዛኞቹ ሴት ተማሪዎች ናቸው በሚል በማኅበራዊ መገናኛው መረጃውን የሚቀባበሉት ወገኖች በተለይ የሴቶችን ጉዳይ በተመለከተ የሚንቀሳቀሱ አካላት፤ እንዲሁም በካቢኔው ሴቶች የሚበዙበት የሀገር አስተዳዳሪው አካል እንዴት ዝም ይላል በሚሉ እየጠየቁ ነው። ዝርዝሩን ከድምፅ ዘገባው ያድምጡ፤

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ