1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩክሬይን ጊዜያዊ ሁኔታ

ረቡዕ፣ የካቲት 19 2006

የዩክሬይን ሁኔታ ገና አልሰከነም፤ በሀገሪቱ ደቡብ ምስራቃዊ ከፊል በክሩሚያ ልሣነ-ምድር ፤ በሩሲያ ተጻራሪና ደጋፊ ዩክሬናውያን ዘንድ ግጭት እንደነበረ ተነግሯል። በኪቭ፤ ከሥልጣን የተወገዱትን ፕሬዚዳንት ቪክቶር ያኑኮቪችን የተካው አዲስ አስተዳደር፤ በእርሳቸው የአስተዳደር ወቅት የነበሩ የተቋሞችን መርኆዎች በመሻር ላይ ነው።

https://p.dw.com/p/1BFqn
Ukraine Demonstration auf dem Krim Simpheropol
ምስል picture-alliance/dpa

ከሞስኮ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ፣ የሀገሪቱ የጦር ኃይሎች፣ በሰፊው ለተጠንቀቅ ዝግጁነታቸው እንዲፈተሽ ማዘዛቸውን የመካላከያ ሚንስትሩ ሰርጌይ ሾይጉ አስታውቀዋል። በመሆኑም ፣ በምዕራብና በማዕከል ወታደራዊ ማዕከላት የሚገኙ ወታደሮች ፣ ዛሬ ረፋድ ላይ በተጠንቀቅ ላይ እንደነበሩ ተገልጿል። ስለ ዩክሬይን ወቅታዊ ይዞታ ተክሌ የኋላ--

በክሬሚያ ልሣነ ምድር ርእሰ ከተማ ሲምፌሬፖል፤ በ 10 ሺ የሚቆጠሩ የአዲሱ የዩክሬይን መስተዳድር ደጋፊዎች፤ ከክፍለ ሀገሩ ም/ቤት ወጣ ብሎ ከመፍቀሬ -ሩሲያ ዩክሬናውያን ጋር ተፋጠው አንደነበረ ተመልክቷል። ተቃዋሚዎቹ፤ የዩክሬይንና የታታሮችን ሰንደቅ ዓላማዎች እያውለበለቡ ፣ «ክሪሚያ የሩሲያ አይደለችም»!« ክብር ለዩክሬይን !» የሚል መፈክሮች ማሰማታቸውን የዩክሬይን ቴሌቭዥን፣ አሳይቷል አሰምቷል ። ኮሳኮችና ሩሲያውያን በቡድን በፊናቸው የሩሲያን ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ ሲዘምሩ ታይተዋል ። በክሪሚያ ከሚገኙ ታታሮች መካከል ፣ አዲሱን የኪቭ መንግሥት የሚደግፉ ወደ ክፍለ ሀገሩ ፓርላማ በመጓዝ ፓርላማው አዲሱን የኪቭ መስተዳድር ያልተቀበለበትን ሁኔታ ተቃውመዋል ። በጥቁር ባህር የምትገኘው ሥልታዊ አቀመማጥ ያላት ልሣነ ምድር ፤ ክሪሚያ ፓርላማ አፈ ጉባዔ ቮሎዲሚር ኮንስታንቲኖቭ ክሪሚያ ከዩክሬይን እንድትገነጠል እቅድ የለም ሲሉ ተናግረዋል። የከክሪሚያ 2 ሚሊዮን ኑዋሪዎች መካከል 12 ከመቶው የቀድሞው የሶቭየት አምባገነን መሪ ጆሴፍ ስታሊን ከአንድ ቦታ ወሰ ሌላ አፈናቅሎ ያሠፈራቸው የቱርክ ዝርዮች የሆኑ ታታሮች ናቸው። አብዛኞቹ የግዛቲቱ ኑዋሪዎች ሩሲያውያን ናቸው። ትልቁ የሩሲያ የባህር ኃይል ምሽግ በሚገኝባት በክሪሚያ የወደብ ከተማ ሴቫስቶፖል፣ መፍቀሬ ሩሲያ የሆኑ ወገኖች የከተማይቱን አስተዳደር በቁጥጥራቸው ሥር አድረገዋል ። የሩሲያ ፌደሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባዔ ባለንቲን ማትቪየንኮ፣

Ukraine Demonstration auf dem Krim Simpheropol
ምስል picture-alliance/dpa

«ቪክቶር ያኑኮቪች፤ አሁንም በሥልጣን ላይ ያሉ ህጋዊው የዩክሬን መሪ ናቸው ፤ ባለፈው ቅዳሜ ፓርላማው ከሥልጣን እንዳወረዳቸው ያሳወቀው በህገ ወጥ አሠራር ነው ማለታቸው ተጠቅሷል። ያኑኮቪች የት እንደሚገኙ እስካሁን በትክክል የታወቀ ጉዳይ የለም።

Symbolbild Spezialeinheit Ukraine Berkut
ምስል picture alliance/CITYPRESS 24

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ኪቭ ውስጥ የሀገር አስተዳደር ሚንስትር አርሰን አባኮቭ፣ አስፈሪው የተቃውሞ ሰልፍ በታኙ ፌደራል ፖሊስ በመዲናይቱ ተቃዋሚዎችን በመግደሉ ኀላፊነት እንዳለበት ገልጸው ይኸው የፖሊስ ኃይል መበተኑንም አስገንዝበዋል። ጊዜያዊው ፕሬዚዳንት ኦሌክሳንድር ቱርቺኖቭ የጦር ኃይሎች አዛዥነቱንም ሥልጣን ተረክበዋል። የሽግግሩ መንግሥት ፣ ነገ በይፋ እንዲመሠረትም ሐሳብ አቅርበዋል። የተቃውሞው ፓርቲ የ ዑዳር ፓርቲ መሪ ቪታሊ ክሊችኮ ዛሬ በኪቭ የነጻነት አደባባይ የአዲሱ ካቢኔ አባላት ሹመት እንደሚገለጽ ተናግረዋል።

የዩክሬይን ጉዳይ በኀያላን መንግሥታት ዘንድ ሰፊ የአመለካከት ልዩነት እንዳያመጣ ቢያሠጋም የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ ፣ ጉዳዩ የዩክሬናውያን ነው ማለታቸው ነው የተጠቀሰው።

«ይህ ምዕራቡና ምሥራቁ የሚፋጠጥበት ጉዳይ አይደለም፤ ሊሆንም አይገባም። ይህ የሩሲያ ወይም የዩናይትድ ስቴትስ ወይም የሌሎች ምርጫ አይደለም ። ይህ የዩክሬይን ህዝብ ጉዳይ ነው። ዩክሬናውያን ናቸው ፣ የራሳቸውን መጻዔ-ዕድል ለመወሰን በመጣር ላይ ያሉት።»

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ