1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩክሬይን ውዝግብ

ረቡዕ፣ ሰኔ 25 2006

የዩክሬይን ጦር በምሥራቃዊ የሀገራቸው ከፊል በሚንቀሳቀሱት መፍቀሬ ሩስያ ሚሊሺዎች አንፃር የጥቃት ዘመቻቸውን ማጠናክራቸውን አስታወቁ። የዜና ምንጮች እንዳመለከቱት፣ የዩክሬይን ፕሬዚደንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ

https://p.dw.com/p/1CUWq
ምስል picture-alliance/AP Photo

ውጊያው በሚካሄድባቸው ዶኔስክ እና ሉሀንስክ የአሥር ቀኑ የተኩስ አቁሙ ደንብ ማብቃቱን ካስታወቁ ከትናንት እኩለ ሌሊት ወዲህ በዚሁ አካባቢ ውዝግቡ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶዋል። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር የተኩስ አቁም ደንብ የሚደረስበትን ዘዴ ለማፈላለግ የዩክሬይን፣ የሩስያ እና የፈረንሳይ አቻዎቻቸውን ዛሬ ለውይይት ወደ በርሊን ጋብዘዋል።

Ukraine Staatspräsident Petro Poroschenko
ምስል picture-alliance/dpa

የዩክሬይን ጦር በምሥራቃዊ የሀገሩ ከፊል በሚገኙት በዶኔስክ እና በሉሀንስክ አካባቢ በታንክ እና በተዋጊ አይሮፕላኖች የጀመረው ጥቃት አዲሱ የዩክሬይን መንግሥት እአአ ባለፈው ሰኔ 20 ፣ 2014 ዓም የደረሰው የተኩስ አቁም ደንብ ፈንጥቆት የነበረውን ተስፋ አደብዞታል። የተኩስ አቁሙን ደንብ ያራዘሙት ፖሮሼንኮ ሚሊሺያዎቹ ትጥቃቸውን እንዲፈቱ እና ሀገሪቱን እንዲለቁ ያቀረቡትን ጥያቄ ዓማፅያኑ ውድቅ በማድረግ በመንግሥቱ ጦር አንፃር ውጊያቸውን ቀጥለዋል። ዓማፅያኑ ሰላም ለማውረድ ቀርቦላቸው የነበረውን ዕድል እንዳልተጠቀሙበት ነው ፕሬዚደንት ፖሮሼንኮ ያስታወቁት።

« የጥቃቱን ዘመቻ በማጠናከር ሀገራችንን ነፃ እናወጣለን። ይህ ነው ለአሸባሪዎ፣ ላማፅያኑ እና ለዘራፊዎቹ፣ ባጠቃላይ ሀገራችንን ለሚያሸብሩት ሁሉ የምንሰጠው መልስ። »

ፖሮሼንኮ የተኩስ አቁሙን ደንብ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲያራዝሙ ከምዕራባውያት ሀገራት እና ዩክሬይን ዓማፅያኑን ተደግፋለች በሚል የምትወቅሳት ሩስያ ግፊት አሳርፈውባቸዋል። ይሁንና፣ ሚሊሺያዎቹ የተኩስ አቁሙን ደንብ እንደገና ለመሰባሰብ እና ራሳቸውን ለማስታጠቅ ተጠቅመውበታል በሚል ፖሮሼንኮ ሳይቀበሉት ቀርተዋል። ብዙው የዩክሬይን ሕዝብም የፕሬዚደንቱን ውሳኔ ደግፎዋል። ባለፈው የሳምንት መጨረሻ በመዲናይቱ ኪየቭ አደባባይ በመውጣት ባማፅያኑ አንፃር ውጊያው እንዲቀጥል መጠየቃቸው ይታወሳል።

ዓማፅያኑም ለጥቃቱ አፀፋ መልስ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን እየገለጹ ነው።

« ለጠላት ጥቃት ተዘጋጅተናል። ይህ የኛ ሀገር ነው። »

Ukraine Panzer und Soldaten vor Luhansk
ምስል picture-alliance/dpa

የተኩስ አቁሙ ደንብ በማብቃቱ ቅር የተሰኙት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ጥረቱ መቀጠል እንዳለበት አስታውቀዋል።

« እንደሚመስለኝ፣ በዩክሬይን እና በሩስያ መካከል አሁን የተፈጠረውን የተወሰነውን ግንኙነት በማጠናከር በምሥራቃዊው የዩክሬይን ድንበር በኩል የጦር መሳሪያ እና ተዋጊዎች እንዳይገቡ የሚከላከል አንድ የጋራ ድንበር መቆጣጠሪያ ማቋቋም ብንችል ጥሩ ሊሆን ይችላል። »

Moskau Russland Präsident Wladimir Putin
ምስል Reuters

በዚህም መሠረት፣ ሽታይንማየር ዛሬ በበርሊን ከዩክሬይን፣ ከሩስያ እና ከፈረንሳይ አቻዎቻቸው ፓቭሎ ክሊምኪን፣ ሴርጌይ ላቭሮቭ እና ከሎውሮ ፋቢዩስ ጋ የምሥራቅ ዩክሬይን ውዝግብ ሊያበቃ ስለሚችልበት ጉዳይ ይወያያሉ። በኪየቭ የሚገኘው የዩክሬይን መንግሥት የጀመረውን ወታደራዊ ርምጃ እንዲያቆም ዩኤስ አሜሪካ እንድታሳስብ ቀደም ሲል የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ላቭሮቭ ተማፅነዋል። ይሁንና፣ የተኩስ አቁሙ ደንብ ካበቃ ወዲህ በምሥራቃዊ ዩክሬይን የቀጠለው የመንግሥቱ ጥቃት እንዳሳሰባቸው የገለጹት የሩስያ ፕሬዚደንት ቭላዲሚር ፑቲን ሀገራቸው የዜጎችዋን መብት ከማስከበር ወደኋላ እንደማትል ያሰሙት ዛቻ ድርድሩን አዳጋች እንዳያደርገው አስግቶዋል።

« ሀገራችን ከድንበሯ ውጭ ያሉትን ዜጎችዋን መብት መከላከሏን ትቀጥላላች። ለዚህም ባላት የፖለቲካ እና የኤኮኖሚ አቅም፣ እንዲሁም፣ ዓለም አቀፍ ሕግ በሚፈቅደው ራስን በራስ የመከላከል መብቷም ትጠቀማለች። »

የጀርመን መራሒተ መንግሥት ሞስኮ ፕሬዚደንት ፖሮሼንኮ ያወጡትን የሰላም ዕቅድ ለመቀበል በጎ ፈቃድ አላሳየችም ያሏትን ሩስያ በመንቀፍ፣ በሩስያ አንፃር ተጨማሪ ጠንካራ ማዕቀብ ሊጣል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

አርያም ተክሌ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ