1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩኤስ አሜሪካ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር የግብፅ ጉብኝት

እሑድ፣ ሰኔ 15 2006

የኢራቅ እና የሌቫንት እሥልማዊ መንግሥት የተሠኘዉ አክራሪ ቡድን፤ በኢራቅ እና በሶርያ ሥልታዊ ቦታዎችን መቆጣጠሩ፤ የዩኤስ አሜሪካዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ በመካከለኛዉ ምሥራቅ እና አዉሮጳ ዉይይት እንዲያደርጉ አስገድዶአቸዋል። ሚንስትሩ በቅድምያ ጉዞአቸዉን ወደ ግብፅ ያደረጉ ሲሆን፤ በግብፅ የዉስጥ የፖለቲካ ጉዳይም ይነጋገራሉ።

https://p.dw.com/p/1CNx2
John Kerry Außenminister USA bei Präsident Al-Sisi Ägypten 22.06.2014
ምስል Reuters

ባልተጠበቀ ጊዜ ወደ አፍሪቃ የተጓዙት የዮናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርጆን ኬሪ ዛሬ የግብፅ ጉብኝታቸዉን ጀምረዋል። የሀገራቸው የመንግሥት ተወካዮች እንደገለፁት ኬሪ በመዲና ካይሮ ከሁለት ሳምንት በፊት ቃለ ማህላ የፈፀሙትን የግብፅ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲን አግኝተው ይነጋገራሉ። ግብፅ ውስጥ በመንግሥት ተቃዋሚዎች ላይ የሚደረገው ጫና እና ህዝቡን እየከፋፈለ ያለው አዲስ አመራር መወያያ ርዕሳቸውም እንደሚሆን ተገልጿል።

የአሜሪካኑ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢራቅ የሚንቀሳቀሰዉን የሱኒ አሸባሪ ቡድን ለማባረር አጋር ለማፈላለግ እንደሆነ ነዉ የተመለከተዉ። በሌላ በኩል ኬሪ ከካይሮ ቆይታቸው በኋላ ወደ ዮርዳኖስ ያመራሉ። የዮናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ከዮርዳኖሱ አቻቸው ከናሰር ሹዳህ ጋር ተገናኝተው በጎረቤት ኢራቅ ስላለው ወቅታዊ ቀውስ እንደሚነጋገሩም ይጠበቃል። ከአልቃይዳ ጋ ግንኙነት አለው የሚባለው የሱኒ ቡድን ባለፉት ቀናት በተደጋጋሚ በኢራቅ ከተሞች ላይ ጥቃት ማድረሱ ይታወሳል።

ISIS Kämpfer Checkpoint bei Mosul 11.06.2014 Karussel
ምስል Reuters

ኢራቅን ለሰወስት ይገምሳታል ተብሎ የሚፈራዉ ጦርነት የምዕራባዉያን ሐያላን የረጅም ጊዜ አቋማቸዉን እንዲለዉጡ እያስገደዳቸዉ ነዉ። የኢራን እስላማዊ አብዮተኞች ሥልጣን ከያዙበት እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ከ1979 ጀምሮ ኢራንን በጠላትነት ሥታድናት የኖረችዉ ዩናይትድ ስቴትስ አሁን የኢራቅ አማፂንን ለማጥቃት ከቴሕራን መንግሥት ጋር ዉይይት ጀምራለች። የዩናትድ ስቴትስና የኢራን ዲፕሎማቶች በያዝነዉ ሳምንት ዉስጥ ቪየና-ኦስትሪያ ዉስጥ ሥለ ኢራቅ ቀዉስ አንስተዉ መወያየታቸዉ ይታወቃል።

አዜብ ታደሰ

ልደት አበበ