1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩንቨርሲቲዎቹ አስተዳደራዊ ርምጃ በተማሪዎች ዕይታ

ረቡዕ፣ ጥር 6 2012

በኢትዮጵያ ዩንቨርሲቲዎች ከዕዉቀት መገበያያነት ይልቅ ጎራ ለይቶ መጋጨትና ብጥብጥ መፍጠር  እየተለመደ መጥቷል።የሚከሰቱት ግጭቶችም ተምረዉ ሀገር ህዝብና ቤተሰብን ያገለግላሉ ተብለዉ ተስፋ የተጣለባቸዉ ወጣቶች ለሞትና ለአካል ጉዳት እየተዳረጉ ይገኛል።

https://p.dw.com/p/3W06g
Äthiopien Bildungspolitik | Banner
ምስል DW/G. Tedla

«ተማሪዎች ከፖለቲካ መጠቀሚያነት መዉጣት አለባቸዉ»

ይህንን ተከትሎም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተዉ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ለችግሩ መፍትሄ ይሆናሉ ያላቸዉን እርምጃዎች ሲወስድ ቆይቷል።መስሪያ ቤቱ በተያዘዉ የትምህርት ዓመት መጀመሪያ ተማሪዎች፣ ወላጆችና የዩንቨርሲዎቹ  የአስተዳደር አካላት የሚፈርሙበት የስምምነት ቅፅ ይፋ አድርጎ ነበር። ቆይቶ ደግሞ  ዩንቨርሲቲዎች በፌደራል የፀጥታ አካላት እንዲጠበቁ ዉሳኔ አሳልፎ ነበር።ያም ሆኖ ችግሩ ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ በመምጣቱ አብዛኛዎቹ ዩንቨርሲቲዎች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ በተገቢዉ ሁኔታ ማከናወን እየተሳናቸዉ መጥቷል።አንዳንዶቹም መደበኛ የመማር ማስተማር ስራዎቻቸዉን ላልተወሰነ ጊዜ አቁመዋል።
 የሳይንስ እና ከፍተኛ የትምህር ሚኒስቴር ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመሆን ታህሳስ 26፣ 2012 ዓ/ም በሰጡት መግለጫ ደግሞ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተከስተዉ በነበሩ ግጭቶች እጃቸው አለበት ተብለው በተጠረጠሩ ከ450 በላይ በሚሆኑ ተማሪዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን አመልክተዋል።
ከነዚህም ዉስጥ ከ170 በላይ በሆኑ ተማሪዎች ከአንድ ዓመት  እስከ መባረር የሚደርስ  አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱንም አመልክቷል። ከ280 በላይ የሚሆኑት ተማሪዎች  ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱ ተገልጿል።በሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የኮሚኒክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደቻሳ ጉርሙ  ቀደምሲል ለ«DW» ገልፀዋል።
ከዚህ የዩንቨርሲቲዎቹ  አስተዳደራዊ ርምጃ በተጨማሪ በሁከቱ ተሳትፈዋል የተባሉ በህግ የሚጠየቁ መሆናቸዉንም አመልክተዋል። ከተማሪዎቹ በተጨማሪ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በተከሰቱ ግጭቶቹ  ተዋናይ ነበሩ የተባሉ  አስር መምህራንና የአስተዳደር  ሰራተኞችም  የስራ ውላቸው ተሰርዟል። ይህንን የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚንስቴር መግለጫ ተከትሎም የተለያዩ ዩንቨርሲቲዎች ግጭት ቀስቅሰዋል  ባሏቸዉ አካላት ላይ አስተዳደራዊ ርምጃ መዉሰዳቸዉን ይፋ አድርገዋል። ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ ማካሄድ ባለመቻሉ ላልተወሰነ ጊዜ ትምህርት ከተቋረጠባቸዉ ዩንቨርሲቲዎች አንዱ የሆነዉ የድሬዳዋ ይንቨርሲቲም  በ18 ተማሪዎች ላይ ርምጃ መዉሰዱን ያስታወቀ ሲሆን፤በትናንትናዉ ዕለት ደግሞ የዩንቨርሲቲዉ ፕሬዝዳንት ከሃላፊነት መልቀቃቸዉ ተሰምቷል። ይህ እርምጃ ምን ያህል ችግሩን ይፈታዋል በሚል «DW» ያነጋገረዉ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ተማሪ እንደሚለዉ እርሱ በሚማርበት ድሬደዋ ዩንቨርሲቲ  ችግሩ የቆየ ሲሆን ከቅርብ ጌዜ ወዲህ ግን በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ መጥቶ የተማሪዎች ህይወት ከፍተኛ ስጋት ላይ እየወደቀ መምጣቱን ተናግሯል። ከዚህ ጋር በተያያዘ  ዩንቨርሲቲዉ የወሰደዉ ርምጃም ትክክል መሆኑን ገልጾ አጥፊዎቹን  መለየቱ ላይ ግን ጥያቄ ያነሳል። «ዉሳኔዉ ትክክል ነዉ። ግን ትክክለኛዉ ሰዉ ይገኛል ወይ? ነዉ።ችግር ፈጣሪዉ ተደብቆ የሚያንቀሳቅሳቸዉ ከሆነ አሁንም ችግሩ አይፈታም ባይ ነኝ።» በማለት ተናግሯል።ዩንቨርሲቲዉ ቅጣት የጣለባቸዉ ተማሪዎች በበቀጣይ የባሰ ችግር ይፈጥራሉ የሚል ስጋት እንዳለዉም ተማሪዉ ገልጿል።
ሌላዉ በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ዩንቨርሲቲዎች አንዱ የሆነዉ የጅማ ዩኒቨርሲቲም  የመማር ማስተማር ስራውን አውከዋል ባላቸው 51 ተማሪዎች ላይ እርምጃ መዉሰዱን በትናንትናዉ ዕለት አስታዉቋል። በአማራ ክልልም የወሎ ዩኒቨርሲቲ  የመማር ማስተማር ስራውን  ለማደናቀፍ ፍላጎት ነበራቸዉ ያላቸዉን  332 ተማሪዎች፣ ሁለት የአስተዳደር ሰራተኞችና አንድ መምህር ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታውቋል።ጎንደር ዩንቨርሲቲ በበኩሉ ታህሳስ 22/2012 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በተለያየ ደረጃ ተሳታፊ ሆነው ተገኙ ባላቸዉ 2 ተማሪዎች ለአንድ ዓመት ፣ 39 ተማሪዎች ለሁለት ዓመት ከትምህርት ገበታቸው እንዲታገዱ እንዲሁም 11 ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ከዩንቨርሲቲዉ  እንዲሰናበቱ መወሰኑን ገልጿል። 
ከዚህም በተጨማሪ ለ7 መምህራን ቀላል የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ ለ3 መምህራን የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ 3 መምህራንን ፣ 8 የአስተዳደር ሰራተኞችን እንዲሁም አንድ  የጤና ባለሙያን  ደግሞ ሙሉ በሙሉ ከስራ አሰናብቷል።በዩንቨርሲቲዉ በአስተዳደር ዘርፍ የሁለተኛ ዲግሪዉን በመከታተል ላይ የሚገኜዉ ተማሪ ታደሰ ደሴ እንደሚለዉ ከሌሎች ዩንበርሲቲዎች  ከሚነሱ ግጭቶች ጋር ተያይዞ በጎንደር ዩንቨርሲቲም በተለያዩ ጊዚያት ረብሻ ሲነሳ መቆየቱን ገልጾ፤ የዩንቨርሲቲዉ አስተዳደርም ችግሩን በዉይይት ለመፍታት ሲሞክር መቆየቱን ጠቅሷል። ይሁን እንጅ ዉይይቱ የሚፈለገዉን ያህል ዉጤት ባለማምጣቱ ዩንቨርሲቲዉ ወደ አስተዳደራዊ ርምጃ ተሸጋግሯል። ይህ ርምጃ ጊዚያዊ አማራጭ ቢሆንም የተሻለዉ መፍትሄ ግን ተማሪዎች ከፖለቲካ መጠቀሚነት ቢወጡ ነዉ ይላል።  በመንግስት በኩል መደረግ አለበት የሚለዉንም እሳስቧል።« በዩንበርሲቲዎቹ እጃቸዉን ያስገቡ  የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ።እነዚህን ፖርቲዎች መንግስት መቆጣጠር አለበት።መንግስት ህግ ማስከበር ካልቻለ ይ ችግር ላለመፈጠሩ ዋስትና የለም» ነዉ ያለዉ።

Äthopien, Dire Dawa University
ምስል DW/M. Teklu

ከደቡብ ክልል ዩንበርሲቲዎች ደግሞ ጅንካ ዩንቨርሲቲ ታህሳስ ስድስት ቀን ባወጣዉ መግለጫ ችግር ሲፈጥሩ ነበር ባላቸዉ  ተማሪዎች ላይ ተገቢ ማጣራት ተደርጎ ቅጣት መተላለፉን  የዩንቨርሲቲዉ የኮሚንኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘርጋዉ ማንአርጎ ለ«DW» አስረድተዋል። በዚህም መሰረት በ 24 ተማሪዎች ላይ ማጣራት ተደርጎ 3ቱ ነፃ ሲሆኑ 5ቱ ለ2 ዓመት  7ቱ ተማሪዎች ለ1 ዓመት  የትምህርት ዕገዳ ጥሏል። በ9ኙ ተማሪዎች ደግሞ ከባድ የፁፍ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። በዩንቨርሲቲዉ በአስተዳደር የትምህርት ዘርፍ የ 3ተኛ ዓመት ትምህርቱን በመከታተል ላይ የሚገኜዉ ተማሪ ታደለ ይሁንም አጥፊዎቹን መቅጣቱ  ተገቢ ቢሆንም ዘላቂ መፍትሄ ግን ሊሆን አይችልም ብሏል። 
የፖለቲካ ፓርቲዎችና የመገናኛ ብዙሃን  የሚያደርጉት ማንነት ላይ ያተኮረ ቅስቀሳ ለችግሮቹ መባባስ በዋናነት አስተዋፅኦ እያደረጉ በመሆናቸዉ ጉዳዩ ጥንቃቄ ሊደረግበት እንደሚገባ ተማሪዎቹ አሳስበዋል።በመንግስት በኩልም ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ እንዲቀጥል የፀጥታ ሁኔታዉን መጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል።
የተማሪዎቹን ጥያቄ ይዘን ያነጋገርናቸዉ የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኮሚንኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደቻሳ ጉሩሙ እንደሚሉት ችግሩ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ተማሪዎቹን በተደጋጋሚ የማወያየትና የማሳመን ስራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዉ ይሄዉ ስራ አሁንም እንደሚቀጥል አመልክተዋል። ከዚህ ጎን ለጎንም አጥፊዎችን የመቅጣት ስራ ይቀጥላል ብለዋል።

 

ሙሉ ቅንብሩን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነዉ እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

ፀሐይ ጫኔ

አዜብ ታደሰ