1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የየካቲት 20/2013 ዓ/ም የዓለም ዜና

ቅዳሜ፣ የካቲት 20 2013

በጎ ፈቃደኛ የባህር ቃኚ የነብስ አድን ሰራተኞች በሜዴትራንያን ባህር በመስመጥ ላይ ከነበረች ጀልባ ከ100 በላይ ፍልሰተኞችን ታደጉ። ጀልባዋ ከተነሳችበት የሊቢያ የባሕር ዳርቻዎች ከ102 በላይ ሰዎችን አሳፍራ እንደነበር መቀመጫውን በርሊን ያደረገው « የባሕር ሰዎች 3» መርከብ የነብስ አድን ሰራተኞች ዛሬ አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/3q0yD

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ባላፈው ማክሰኞ ከሽንፋ ወደ መተማ (ገንዳ ውሀ) ሲጓዝ በነበረ ተሸከርካሪ ባልታወቁ ታጣቂዎች ታግተው የነበሩ 4 ሰዎች መለቀቃቸውን የአካባቢው ነዋሪና እና የዞኑ አስተዳደር አስታውቀዋል፡፡አንድ የሽንፋ ከተማ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ዛሬ በስልክ እንደተናገሩት ግለሰቦቹ ከመንገላታትና ከመጎሳቆል ውጪ በሰላም ወደ ቤተሰቦቻቸው ገብተዋል፣ “በህይወት መመለሳቸው ሁሉንም አስደስቷል” ብለዋል፡፡«በሰላም ነው የተወሰነ ድብደባ እና ጫና ደርሶባቸዋል።ሰውነታቸው ጉስቁልቁል ብሏል። የተደበደቡበት እንዳለ ሆኖ በሰላም መምጣታቸው ነው ደስ ያለን እኛን»ምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ታጋቾቹ በምን ዓይነት መንገድ እንደተለቀቁ ባያብራሩም አሁን ሁሉም ከእገታ ተለቅቀው ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀላቸውን አስረድተዋል፡፡«አሁን ሰዎቹ ተለቀዋል። በጥዋት ነው የተለቀቁት »የችግሩን መፈጠር ምክንያት በማድረግ በአካባቢው ያሉ አሽከርካሪዎች ወደ ገንዳ ውሀ፣ ቋራ እና ሽንፋ የሚሰጡትን የትራንስፖርት አገልግሎት አቋርጠው የሰነበቱ ሲሆን ህብረተሰቡ፣ አስተዳደሩና የፀጥታ አካላት ባደረጉት የጋራ ውይይት አገልግሎቱ ትናነት ከሰዓት በኋላ መጀመሩን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል፡፡ባለፈው ማክሰኞ አንድ ተሸከርካሪ ከሽንፋ ወደ ገንዳ ውሀ ሲጓዝ ጉባዔ ከተባለ ቦታ ላይ ያልታወቁ ታጣቂዎች 4 ሰዎችን አግተው ወስደው ነበር።  በወቅቱ በነበረው የተኩስ ልውውጥ አንድ የመንግስት የፀጥታ አባልና ከአጋቾቹ ደግሞ አንድ መገደላቸው ተዘግቧል፡፡ቀደም ባሉት ጊዜያት ተመሳሳይ መኪና አስቆሞ ማገት፣ መዝረፍና ማንገላታት በአካባቢው ይታይ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች አስታውሰው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ችግሩ ጋብ ብሎ እንደነበርም ገልፀዋል፡፡

በናይጄሪያ አብዛኞቹ ሕጻናት የሆኑ አርባ ሁለት ሰዎች ከታጣቂዎች ዕገታ ተለቀቁ። በማዕከላዊ ምዕራብ ኒጀር ግዛት ከምትገኘው ካጋራ ባልታወቁ ታጣቂዎች ከሁለት ሳምንት በፊት ታግተው  ተወስደው የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአንድ ትምህርት ቤት ማህበረሰብ አባላት አሁንም በታጣቂዎቹ እጅ  እንደሚገኙ የአካባቢው ባለስልጣናት አስታውቀዋል። ከታጋቾቹ ውስጥ ሃያ ሰባቱ ህጻናት ሲሆኑ የተቀሩት የትምህርት ቤቱ ሰራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው እንደሚገኙበት የጀርመን ዜና ወኪል ዲፒኤ ዘግቧል። በአፍሪካ በህዝብ ብዛቷ ቀዳሚ በሆነችው ናይጄሪያ በታጣቂዎች የሚደረገው እገታ እያየለ መምጣቱም ተነግሯል። ትናንት ዓርብ ጥዋት በተመሳሳይ 317 ሴት ተማሪዎች ከሚማሩበት የዛምፋራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ታግተው ሲወሰዱ ይህ ዘገባ እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ተማሪዎቹ የት እንደደረሱ አልታወቀም። ባለፈው የታህሳስ ወርም እንዲሁ 300 ወንድ ተማሪዎች ተወስደው የነበረ ሲሆን አብዛኞቹ በተለያየ መንገድ ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለሳቸው ሲታወቅ አሁንም ድረስ በታጣቂዎች እጅ ያሉ እንዳለ ባለስልጣናት አስታውቀዋል። ተማሪዎችን ከየትምህርት ቤቱ በማገት ሀላፊነቱን የወሰደ ወገን እስካሁን አልተገኘም። ነገር ግን በናይጄሪያ ሰሜናዊ ክፍል የሚንቀሳቀሰው የሽብር ቡድን ቦኮ ሃራም ተማሪዎችን በማገት እና ተደጋጋሚ ጥቃቶችን  በመፈጸም ይታወቃል።

በጎ ፈቃደኛ የባህር ቃኚ የነብስ አድን ሰራተኞች በሜዴትራንያን ባህር በመስመጥ ላይ ከነበረች ጀልባ ከ100 በላይ ፍልሰተኞችን ታደጉ። ጀልባዋ ከተነሳችበት የሊቢያ የባሕር ዳርቻዎች ከ102 በላይ ሰዎችን አሳፍራ እንደነበር መቀመጫውን በርሊን ያደረገው « የባሕር ሰዎች 3» መርከብ የነብስ አድን ሰራተኞች ዛሬ አስታውቋል። ሰራተኞቹ ስደተኞቹን የታደጉት በፕላስቲክ ጀልባ በመጓዝ ላይ እያሉ በመካከለኛው የሜድትራንያን ክፍል የጀልባው አየር መተንፈሱን ተከትሎ መስመጥ በመጀመራቸው ነው ብሏል። የነብስ አድን ሰራተኞቹ ትናንት ዓርብ በተመሳሳይ በባህር ላይ ተዳክመው የነበሩ 45 ስደተኞችን መታደጋቸውን  የጀርመን ዜና ምንጭ  ዘግቧል። በህይወት ለተረፉት ስደተኞች የህክምና እርዳታ  እየተደረገላቸው ነው ተብሏል። በባህር ላይ ተዳክመው ከተገኙት ውስጥ  አስራ ሶስቱ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ታዳጊዎች መሆናቸውም ተዘግቧል። የባህር ቃኝ መርከቧ ከስፔይኗ የወደብ ከተማ ቡርያና ከተነሳች ከሳምንት በኋላ የነብስ አድን ስራውን መስራቷ የተገለጸው። የጣልያን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር እንዳስታወቀው እስከ 2021 ድረስ ፍልሰተኞችን የጫኑ 4,500 ጀልባዎች ጣልያን ደርሰዋል። ከሊቢያ የባህር ዳርቻዎች የሚነሱ አብዛኞቹ ጀልባዎች መዳረሻቸውን ጣልያን ያደርጋሉ ።

ዩናይትድስቴትስ በሶርያ በሚገኙ እና በኢራን እንደሚደገፉ በተነገረላቸው የሚሊሻ ቡድን ላይ የፈጸመችው የአየር ጥቃት ሽብርተኝነትን ከመደገፍ ለይታ እንደማታየው ኢራን አስታወቀች። ዩናይትድ ስቴትስ ቃጢብ ሄዝቦላህ በሚባለው የሚሊሻ ቡድን ላይ ጥቃቱን የሰነዘረችው በኢራቅ የሚገኙ ይዞታዎቿን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶችን ስለሰነዘረ ነው ስትል ከሳለች። ነገር ግን በዩናይትድ ስቴትስ የተወሰደው ጥቃት በአካባቢው ሽብርተንነትን ለመዋጋት የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚያስተጓጉል ነው» ሲሉ  የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣን የሆኑት አል ሻምክሃኒ ዛሬ ተናግረዋል። ወታደራዊ ሹሙ ዛሬ ከኢራቅ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፉአድ ሁሴን ጋር ቴህራን ውስጥ ተገናኝተው  ተነጋግረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ በዚህ ጊዜ «በጸረ ሽብርተኝነት ላይ የሚደረጉ ጥቃቶች ለአዲስ የተደራጀ የሽብርተኝነት መንገድ ይከፍታል» ሲሉ ሁሴን ጥቃቱ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል። ዩናይትድ ስቴትስ በወሰደችው በዚሁ የአየር ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል ሌሎች አራት ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።

የፓኪስታን የጸረሽብር ሚስጥራዊ ግብረ ኃይል በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ባሏቸው ታጣቂዎች ላይ በወሰዱት ድንገተኛ ጥቃት ሁለት ታጣቂዎችን መግደላቸውን አስታወቁ። ግብረ ኃይሉ በደቡባዊ ፓኪስታን በምትገኘው የሱኩር ከተማ ዛሬ ማለዳ ባደረገው ድንገተኛ  ወረራ ጥቃቱን መፈጸሙን የግብረ ኃይሉ ወታደራዊ ባለስልጣን ተናግረዋል። በዘመቻው ወቅት ታጣቂዎቹ ከጥቃቱ ለማምለጥ የመከላከል ሙከራ አድርገው እንደነበር ወታደራዊ ባለስልጣኑ ሻኢድ ሶላንጊ ተናግረዋል። አሶሽየትድ ፕረስ እንደዘገበው በውጊያው የፓኪስታን ጣሊባን አባላት የሆኑ ሁለት ታጣቂዎች ተገድለዋል። ታጣቂዎቹ ካሁን ቀደም በደቡብ እና ሰሜናዊ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች የመንግስት የጸጥታ ኃይሎችን ኢላማ ያደረጉ የተለያዩ ጥቃቶችን መፈጸማቸው ተነግሯል። የታጣቂዎቹን ጥቃት ተከትሎም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በጸጥታ ስጋት ነግሶ  ቆይቷል።

በሀይቲ ታራሚዎች እስር ቤት ሰብረው ካመለጡ ከአንድ ቀንም በኋላ ከ 200 በላይ ታራሚዎች የደረሱበት አልታወቀም። ትናንት ዓርብ ታራሚዎቹ ሲያመልጡ የእስርቤቱን አዛዥ ጨምሮ 25 ሰዎች መገደላቸውን ባለስልጣናት አስታውቀዋል። ከመዲናዋ ፖርት ኦው ፕሪንስ አቅራቢያ ከሚገኘው ማረሚያ ቤት ሰብረው ያመለጡት 400 እንደሚሆኑ ባለስልጣናት አስታውቀዋል። በእስረኞቹ ጥቃት ደርሶባቸው ሳይገደሉ አልቀረም ከተባሉት 25 ሰዎች ውስጥ ሰላማዊ ሰዎች እንደሚገኙበት የፈረንሳይ ዜና ምንጭ ዘግቧል። በማምለጥ ላይ ከነበሩት ውስጥ ስድስት ታራሚዎችም ተገድለዋል። በእስር ቤቱ ውስጥ ከ 1500 በላይ እስረኞች ነበሩ። ዋንኛው የሀይቲ የወሮበላዎች ቡድን መሪ የነበረው አርኔል ጆሴፍ እስርቤቱን ሰብረው ካመለጡት ውስጥ አንዱ ሲሆን በፖሊስ በተወሰደበት እርምጃ ተገድሏል። ሌሎች ያመለጡ ታራሚዎችን ለመያዝ ፖሊስ የማደን ስራውን ማጠናከሩም ተሰምቷል።አብዛኞቹ ታራሚዎች የእጅ ካቴና የታሰረባቸው መሆኑ ምናልባት ፖሊስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊደርስባቸው ይችላል ሲሉ ባለስልጣት ተስፋቸውን ገልጸዋል።ነገር ግን በሀይቲ በተለያዩ ጊዜያት ታራሚዎች እስር ቤት ሰብረው በጅምላ ማምለጣቸውን ዘገባው አመልክቷል።TD/LA