የየመን ፕሬዝዳት ያደረጉት ሹም ሽር
ዓርብ፣ ሚያዝያ 4 2005ማስታወቂያ
የየመን ፕሬዝዳት አብድ ረቡ መንሱር ሐዲ ጠንካራ ተቀናቃኞቻቸዉ የሚባሉት የቀድሞዉን ፕሬዝዳት የዓሊ አብደላ ሳሌሕን ልጅና የቅርብ ዘመዶች ከየጦር አዛዥነት ሹመታቸዉ ሽረዉ በአምባሳደርና በወታደራዊ አማካሪነት ሾመዋቸዋል። ፕሬዝዳቱ ሐዲ ሪፐብሊካን ጋርድ የተሰኘዉን ጠንካራ ክፍለ-ጦር የሚያዙትን የሳሌሕን ልጅ ጄኔራል አሕመድ ዓሊ ሳሌሕን በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የየመን አምባሳደር፥ የቀድሞዉን ፕሬዝዳት ሁለት የቅርብ ዘመዶችን ደግሞ በኢትዮጵያና በጀርመን የየመን ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ አድርገዉ ከአጠገባቸዉ አርቀዋቸዋል። ፕሬዝዳንቱ የቀድሞዉን ፕሬዝዳት ዋነኛ ተቀናቃኝ ጄኔራል ዓሊ ሞሕሴንን ባንፃሩ ልዩ አማካሪያቸዉ አድገዉ ሾመዋቸዋል። እርምጃዉ ፕሬዝዳት ሐዲ አስጊ ተቀናቃኞቻቸዉን አርቀዉ ከአንድ ዓመት በፊት የያዙትን ሥልጣን ለማጠናከር የተጠቀሙበት ሥልት መሆኑ በግልፅ እየተነገረ ነዉ። ሰነዓ የሚኖረዉን ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ግሩም ተክለ ሐይማኖትን ሥለ ሹም ሽሩ አላማና እንድምታ በሥልክ አነጋግሬዋለሁ። ለመጀመሪያዉ ጥያቄዬ ከሰጠዉ መልስ ይጀምራል።
ግሩም ተክለ ሐይማኖት
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ