1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዞን ዘጠኝ የድረገጽ ጸሐፍት ክስ ዉድቅ ሆነ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 6 2008

ዞን ዘጠኝ በመባል በሚታወቁት አራት የድረገጽ ጸሐፍት እና አንድ ጋዜጠኛ ላይ በሽብርተኝነት የቀረበባቸዉን ክስ ፍርድ ቤት ዛሬ ዉድቅ አደረገ። ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ላይ የቀረበዉ ማስረጃ ሁሉ ደካማ መሆኑን ማመልከቱን የፈረንሳይ የዜና ወኪል ከአዲስ አበባ ዘግቧል።

https://p.dw.com/p/1GpYo
Äthiopien Zone9 Blogger Gruppe
ምስል Zone9

[No title]

ፍርድ ቤቱ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ የወሰነላቸው በሌለችበት የተከሰሰችው ሶሊያና ሽመልስ፣ ናትናኤል ፈለቀ ፣ አጥናፍ ብርሃነ እና አቤል ዋበላ ናቸው ። በዚሁ መሠረትም ዛሬ ማምሻዉን ከእስር ቤት እንደሚወጡ ይጠበቃል። በሌለችበት በተመሳሳይ የተከሰሰችዉ የዞን ዘጠኝ አባል ሶልያና ገብረሚካኤልም በስደት ሀገር ብትሆንም ክሱ እንደተነሳላት ተገልጿል። ሶልያና ከ18 ወራት በኋላም ቢሆን ክሱ ዉድቅ መሆኑ መልካም መሆኑን ለዶቼ ቬለ ገልጻለች።

Äthiopien Zone9 Blogger Gruppe
ምስል Zone9

በአንፃሩ ዛሬ ያስቻለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ የወንጀል ችሎት ፣ላለፉት 18 ወራት ከድረገጽ ጸሐፍቱ ጋር ታስሮ የቆየዉ አራተኛዉ ተከሳሽ ጋዜጠኛ በፈቃዱ ኃይሉ ከሽብርተኝነት ጋር የሚገናኘዉ ክስ ቢነሳለትም ለአመፅ በማነሳሳት በሚለዉ ክስ በእስር እንደሚቆይ መወሰኑን ዘገባዉ አክሎ ገልጿል። የፀረ ሽብር ክስ ተሰርዞ አመጽን በማነሳሳት ወንጀል እንዲቀየርም ወሰነ ። በፍቃዱ ሃይሉ ግን የአሸባሪነት ክሱ ቢነሳለትም ክሱ አመጽ በማነሳሳት ተቀይሯል ።ክሱም እስከ አስር ዓመት እስራት ሊያስበይን እንደሚችልም ተመልክቷል። ከ18 ወራት በፊት 6 የዞን ዘጠኝ የድረገጽ ጸሐፍት እና ሶስት ጋዜጠኞች ባጠቃላይ ዘጠኝ ነበሩ ጥቃቶችን በማሴርና ግንቦት 7 ከተባለው የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ቡድን ጋር በመተባበር ህገ መንግሥታዊ ስርዓቱን ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል በሚል ወንጀል ተከሰው ነበር የታሰሩት። ባለፈዉ ዓመት ሐምሌ ወር ከታሳሪዎቹ አራቱ ተለቀዋል። ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተዉ CPJ ኢትዮጵያን ጋዜጠኞችን በማሠር ከአፍሪቃ ሁለተኛዋ ሀገር ያደርጋል። የድርጅቱ የአፍሪቃ ተጠሪ ቶም ሮድስ ፍርድ ቤት የድረገጽ ጸሐፍትና ጋዜጠኞቹን ከተከሰሱበት የሽብር ክስ በነፃ ማሰናበቱን አወድሰዋል። ተጨባጭ ማስረጃ ሳይገኝባቸዉም ሂደቱ ረዝም ጊዜ መዉሰዱንም ጠቁመዋል። የዋሽንግተን ዲሲው ዘጋቢያችን ናትናኤል ወልዴ ሶልያና ሽመልስን በስልክ አነጋግሯታል ።
ሸዋዬ ለገሠ/ናትናኤል ወልዴ
ኂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ

Äthiopien Zone9 Blogger Gruppe
ምስል Zone9