1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዘገየው የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ

ረቡዕ፣ መጋቢት 14 2008

የኢትዮጵያ መንግስት ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ለውጭ ኩባንያዎችም ይሁን ለአገር ውስጥ ባለሐብቶች መስጠቱን በጊዜያዊነት ማቆሙን አስታውቋል። መንግስት ከውሳኔ የደረሰው ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን እና ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር የወሰዱት ኩባንያዎች ስኬታማ ባለመሆናቸው መሆኑን ቢያስታውቅም ውሳኔው እጅጉን የዘገየ ተብሎ ተተችቷል።

https://p.dw.com/p/1IIN0
Äthiopien Ackerland
ምስል DW/Eshete Bekele

የዘገየው የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ

የህንዱ ካራቱሪ ኩባንያ በምዕራብ ኢትዮጵያ የጋምቤላ ክልል የወሰደውን 300,000 ሔክታር መሬት ተረክቦ የእርሻ ዝግጅት ሲጀምር አዲስ አበባ ላይ ባለስልጣናት እና የኩባንያው ባለቤት የምስራች እየነገሩ ነበር። ስለ መሬት እደላው በውጭ አገራት ጋዜጠኞች የተጠየቁት የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ «የኢትዮጵያ መንግስት የግብርና ፖሊሲ ዋንኛ ትኩረት ባለ አነስተኛ የእርሻ መሬት ባለ ይዞታዎች» መሆናቸውን ጠቁመው «የግሉ ዘርፍ ደጋፊ ግን ደግሞ ቁልፍ ሚና የሚጫወትበት እድል» መኖሩን ተናግረው ነበር። የኢትዮጵያ መንግስት ፖሊሲ ቀልባቸውን ከሳባቸው አንዱ የሆነው ካራቱሪ ኩባንያ ባለቤት ራም ካራቱሪ በስራው ሲሰማሩ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ በማድረግ ሌላ ማንም ያልሰራውን መስራታቸውን ተናግረው ነበር። የሚመረተው ምርትም ለኢትዮጵያ ገበያ የሚውል መሆኑን መናገራቸው አልቀረም።


ካራቱሪ ለሩዝ እርሻ ልማት በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ወረዳ የተረከበውን መሬት እርሻ ዝግጅት ሲጀምር በቦታው የነበረውን ደን በአግባቡ ማንሳት ሳያስፈልገው እሳት ለቀቀበት። በእንጨት ንግድ ተሰማርቷል የሚል ወቀሳም ቀርቦበት ነበር። መቀመጫውን በህንድ ባንግሎር ያደረገው ካራቱሪ ግሎባል ሊሚትድ ኩባንያ በኢትዮጵያ የጋምቤላ ክልል 300ሺ ሄክታር መሬት ለማልማት ሲሰጠው በአመት አንድ ሚሊዮን ቶን በቆሎ፤ ሩዝ፤የፓልም ተክልና ሌሎች የግብርና ውጤቶችን ሊያመርት ነበር። የኩባንያው የግብርና ስራ ለአካባቢው ነዋሪዎች መፈናቀል ምክንያት ነው በማለት ሁማን ራይትስ ዎች እና የኦክላንድ ማዕከልን የመሳሰሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የኢትዮጵያን መንግስት በተደጋጋሚ ወቅሰዋል።። ኩባንያውም ለአካባቢው ነዋሪዎች ቃል የገባውን የስራ አድል መፍጠር፤የጤናና የትምህርት መሰረተ ልማት ማቅረብ ተስኖት ቆይቷል።
ይህም ሁሉ ሆኖ ግን ኩባንያው ከሰረ። ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያገኘውን ስልሳ ሚሊዮን ብር ጨምሮ ወደ 170 ሚሊዮን ብር ብድር ያገኘው እና ለአገር ውስጥ ባለ ሐብቶች ብቻ ተወስኖ የቆየው ማሽኖችን የማከራየት ስራ የተፈቀደለት ካራቱሪ እቅዱን ማሳካት ተሳነው። ከኢትዮጵያ መንግስት ጋርም እሰጥ አገባ ውስጥ ገባ።

Flash-Galerie Äthiopien Land Grab
ምስል DW/Schadomsky

በኢትዮጵያ የሰፋፊ የእርሻ ልማት ተሰማርቶ የከሰረው ግን ካራቱሪ ግሎባል ብቻ አይደለም። ለተመሳሳይ የእርሻ ስራ በጋምቤላ ክልል ከባሮ ወንዝ አቅራቢያ 27 ሺህ ሔክታር መሬት እና 89 ሚሊዮን ብር ብድር የወሰደው ቢ.ኤች.ኦ. ባዮ ፕሮዳክትስ የተሰኘ የህንድ ኩባንያ ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ገጥሞታል።

የኢትዮጵያ መንግስት በግብርናው ዘርፍ የእውቀትና ክህሎት ሽግግር ለማድረግ፤የሥራ እድል ለመፍጠርም ሆነ አመታዊ ምርትን ለማሳደግ የሰነቀው እቅድ ባለመሳካቱ የእርሻ መሬቶችን መስጠት ማቆሙን አስታውቋል። ከውሳኔው ለመድረስ ጥናት መካሄዱን የተናገሩት የኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንት እና የመሬት አስተዳደር ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዘነበ ለባለሐብቶቹ ብድር መስጠት ጭምር መቆሙን ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በሰፋፊ የእርሻ ስራ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው ባለሐብቶች 3.6 ሚሊዮን ሔክታር መሬት አዘጋጅቶ የነበረ ሲሆን 2.4 ሚሊዮን ሔክታር የሚሆነው ለኩባንያዎች መተላለፉን አቶ ዳንኤል ዘነበ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
ድምጽ 2የኢኮኖሚ ባለሙያ እና ፖለቲከኛ የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ የሰፋፊ የእርሻ ልማትን ለማስፋፋት የቀረበው እቅድ ላይ ተቃውሞ የላቸውም። የሰፋፊ እርሻ ልማት በኢትዮጵያ መንግስት የእድገትና ለውጥ እቅድ ውስጥ የግሉን ዘርፍ ለማሳተፍ የሞከረ ብቸኛው ውጥን ነው የሚሉት አቶ ግርማ ችግሮች እንደነበሩበት ግን ይናገራሉ። የመሬትም ይሁን የብድር አቅርቦቱ አቅም እና ፍላጎቱ ያላቸውን ኢትዮጵያውያንን ገሸሽ በማድረግ የውጭ ኩባንያዎች ላይ ማተኮሩ ቀዳሚው መሆኑን ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንት እና የመሬት አስተዳደር ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዘነበ በእርሻ ስራ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች መረጣ ላይ ችግር እንዳልነበረ ይከራከራሉ። በእርሳቸው አባባል ዋናው ችግር ኩባንያዎቹ የእርሻ መሬቱንም ይሁን የብድር አቅርቦት ካገኙ በኋላ በቃላቸው ስራውን መከወን አለመቻላቸው ነው።
የህንዶቹ ካራቱሪ ግሎባልም ይሁን ቢ.ኤች.ኦ. ባዮ ፕሮዳክትስ ኩባንያዎች የወሰዱትን የእርሻ መሬት እና ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር በአግባቡ በስራ ላይ ማዋል ሲሳናቸው የኢትዮጵያ መንግስት እርምጃ ለመውሰድ እስከ ስምንት አመታት ፈጅቶበታል። አቶ ዳንኤል ዘነበ ተቋማቸው እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ድጋፍ ለማድረግ መሞከር መምረጡን ይናገሩ እንጂ አቶ ግርማ ሰይፉ ተግባራዊነቱን ለመከታተል እና ለማረቅ ምንም ስራ አልተሰራም በማለት ተችተዋል።

Äthiopien Ackerland
ምስል DW/Eshete Bekele

ካራቱሪ ግሎባልን የመሰሉ የውጭ ኩባንያች ከወሰዱት መሬት ስፋት እና ካገኙት የብድር መጠን አኳያ ዋና መነጋገሪያ ይሁኑ እንጂ ኢትዮጵያውያን ኩባንያዎች እና ባለ ሐብቶችም በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ናቸው። ጋምቤላን በመሰሉ አካባቢዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ወስደው ስኬታማ መሆን ተስኗቸዋል። አቶ ዳንኤል ዘነበ አሁን የተላለፈው ውሳኔ እነሱንም እንደሚመለከት ተናግረዋል።

አቶ ግርማ ሰይፉ በሰፋፊ እርሻ ሥራ ላይ የተሰማሩት ኢትዮጵያውን በቂ ልምድ እና እውቀት ያላቸው ስለመሆናቸው ጥያቄ አላቸው። የኢትዮጵያ መንግስት የሚያቀርባቸው ማበረታቻዎችም አገሪቱ ያለባትን የምግብ እህል ምርት ችግር ለሚቀርፉት አለመሆኑን ተችተዋል።

Äthiopien Ackerland
ምስል DW/Eshete Bekele

የኢትዮጵያ መንግስት በጋምቤላ ክልል ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ለባለ ሐብቶች ለማቅረብ ሲዘጋጅ አስፈላጊውን የካሳ ክፍያ በተገቢው መንገድ አልከፈለም፤የሰብዓዊ መብት ጥሰትም ፈጽሟል ተብሎ ተተችቷል። የኢትዮጵያ መንግስት ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ለማዘጋጀት በጋምቤላ ክልል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ2010 እስከ 2013 ዓ.ም. ድረስ የሰፈራ መርሐ-ግብር አካሂዷል። ባለፈው ዓመት ጥር ወር በዓለም አቀፍ የምርመራ ጋዜጠኞች ጥምረት ይፋ የተደረገው እና ከባንኩ ሾልኮ ወጥቷል የተባለዉ የአጣሪ ቡድን ዘገባ የሰፈራ መርሐ ግብሩ በግዳጅ የተካሄደ ነበር ሲል የኢትዮጵያ መንግስትን ወቅሷል።‘ከመኖሪያ ቀያችን በግዳጅ ተፈናቅለናል’ በማለት የኢትዮጵያ መንግስትን በከሰሱ 26 የአኙዋክ ተወላጆች ጥያቄ የተቋቋመው አጣሪ ቡድን ያዘጋጀው ሰነድ የሰፈራ መርሐ-ግብሩ በግዳጅ መከናወኑን፤ ከዓለም ባንክ ለመሰረታዊ አገልግሎት ተብሎ የተመደበው ገንዘብም ነዋሪዎችን አስገድዶ ለማስፈር መዋሉን ይጠቁማል። ሰዎችን በማፈናቀልና ሌላ ሥፍራ በማስፈሩ ሒደት በአኝዋክ ተወላጆች ላይ ድብደባ፤አስገድዶ መድፈር እና ግድያ መፈጸሙን ዘግቧል።


እሸቴ በቀለ
ሒሩት መለሰ