1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዘንድሮዉ ኖቤል የሰላም ሽልማት የቻይና የዲፕሎማሲ ጡንቻ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 4 2003

ኖቤል የሰላም ሽልማት በርግጥ ብዙ ጊዜ አወዛግቧል።የዘንድሮዉን ያክል የዲፕሎማሲ ዘመቻ ተከፍቶበት፥የምጣኔ ሐብት፥የፖለቲካ ጡንቻ አማዞ-ግን አያዉቅም

https://p.dw.com/p/QXCU
ሽልማቱ ሜዳሊያ


13 12 10

የኖርዌዉ የሰላም ኖቤል ሸላሚ ኮሚቴ ቶርብዮርን ያግላንድ ባለፈዉ አርብ እንዳሉት የኮሚቴያቸዉ አላማ-ምግባር የአልፍሬድ ኖብልን ምኞት ኑዛዜ መፈፀም ነዉ።ሽልማቱ የኖቤል ምኞት ኑዛዜን ማስከበሩ ብዙ ጊዜ ብዙዎች የመሰከሩለትን ያክል-ብዙዎችን እንዳወዛገበ፣ ብዙ ጊዜ በጥቂቶች ጥቂት-ጊዜ በብዙዎች በጣም ጥቂት ጊዜ በሐለኞች እንደተወገዘ ዘንድሮ ላይ ሲደርስ የሐይለኞችን ሐያል የዲፕሎማሲ ጡንቻ አማዘዘ።አርብ ኦስሎ ላይ የፈጋዉ እዉነት መነሻ፣ እንድምታዉ መድረሻ፣ የታላቁ ሽልማት ጉዞ ማጣቀሻችን ነዉ።ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

ኦስሎ-ያዉ በየአመቱ በዚሕ ሰሞን እንደምትሆነዉ ሁሉ ትቀዘቅዛለች።ለወትሮዉ የምትሆነዉን-ቅዝቃዜዋን-በሚሆንባት ታላቅ ድግስ ለማስወገድ ሽር ጉዱ በርግጥ አልተጓደለባትም።ልክ-እንደ ጥንቱ፣-እንደ ድሮዉ፣እንዳምና-ሐቻምናዉ ሁሉ የአለም ዲፕሎማት፣ ፖለቲከኛ፣ የሙዚቃ፣ የፊልም፣ የመገናኛ ዘዴዎች ታላላቅ ሰዎች ከታላቁ አዳራሻ ታጭቀዉበታል።

Oslo China Nobelpreis Rabiye Qadir
ታዳሚዉምስል DW

በየአመቱ የዚያን ዕለት-እንደሚሆንባት ሁሉ አርብም-የሆነባት ሲሆን ቅዝቃዜዉ-ገለል ቀለል ባለላት ነበር።ከመኩዋንቱ የብብት፣ የፂም ጠረን ማጥፊያ ጋር የተቀየጠዉ የወይዛዝርቱ ምርጥ-ዉድ ሽቶ፥ የፀጥታ አስከባሪዎቹ ትንፋግ፤ የብርጭቆ-ሹካ ማንካዉ ካካታ፣ ጫጫታ-ጭብጨባ ዉካታዉም ሆነ ከአዳራሹ ዉጪ ካለዉ ሠልፈኛ መፈክር-መዝሙር ጋር የሚላተመዉ የምርጥ ድምፃዉያን ምርጥ ዜማ የኦስሎን አየር አልቀየረዉም።ዉቧ ከተማ ደብቷታል።

የኦስሎ አየር በርግጥ ከዜሮ-በታች ስምንት ዲግሪ ሴልስየስ ይነበባል።የድብት-ቅዝቃዜዋ ጥናት ሰበብ ከተፈጥሮ ይልቅ የድግሷ- ምክንያትና ዉጤት መሆኑ ነዉ ዚቁ።የዘንድሮዉ ኖቤል የሠላም ሽልማትና አሸናፊዉ። ሽልማቱ ለቻይናዊዉ የመብት ተሟጋች ለ-ሊዩ ሺያኦቦ እንደሚሰጥ ባለፈዉ ጥቅምት ከኦስሎ ሲታወጅ ቀልቧል የገፈፈዉ የቢጂንጎች ዛቻ-አዚሙን እንደጣለበት ነዉ።እና ኦስሎ ትበርዳለች።በሺ የሚቆጠሩ የአለም-ምርጥ እንግዶች የታጨቁበት ምርጥ አዳራሽ በርግጥ ይሞቃል።

ከአዳራሹ መድረክ ከተደረደሩት ስድስት ወንበሮች-የመሐለኛዉ ግን ባዶ ነበር።አለምን ያሳደሙት-የአመቱ ታላቅ ሽልማት አሸናፊ ወይም የቅርብ ተወካያቸዉ መቀመጫ ነበር።ሊዩ ሺያኦቦ-ብዙ መቶ ሺሕ ኪሎ ሜትር ርቀዉ ወሕኒ-ቤት ናቸዉ።ተወካያቸዉም ከቻና ንቅንቅ እንዳይሉ ታግደዋል።እና አዳራሹ ተጨናንቋል።ሞቋል።ደምቋል።ግን ደብቶታል።የኦስሎ-የአዳራሽዋን ምናልባትም የብዙዉን አለም ቅይጥ ስሜት የሸላሚዉ ኮሚቴ ሊቀመንበር ቶርብዮርን ያግላንድን ያክል የገለጠዉ ትንሽ ነዉ።ደስታና ሐዘን።

«ተሸላሚዉ ዛሬ እዚሕ ባለመገኘታቸዉ እናዝናለን።ሰሜን-ምሥራቅ ቻይና ጎብኚ ከማይደርስበት እስር ቤት ናቸዉ።የተሸላሚዉ ባለቤት ሊዩ ሻም ሆኑ የቅርብ ዘመዳቸዉ እዚሕ ከኛ ጋ የሉም። በዚሕም ምክንያት ዛሬ ሜዳልያም ሆነ ዲፕሎማ አይሰጥም።ይሕ ራሱ ሽልማቱ አስፈላጊና ተገቢ መሆኑን አመልካች ነዉ።»

ካዳራሹ የታደሙት የአብዛኞቹ ዲፕሎማት ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ በተለይም የቻይኖችን ዛቻ-እርምጃ ለማስቀየር በቀጥታም፥- በብራስልስ፣ ዋሽንግተኖች በኩልም ሽቅብ ቁልቁል ሲሉ የከረሙት የኖርዌ ዲፕሎማት-ፖለቲከኞች የዚያን እለትም አካላቸዉ እንጂ ቀልባቸዉ ቤጂንግ ነበር።ቤጂንጎች ፍንክች አላሉም።

ሸላሚ አሸላሚዎቹ በሰብአዊ መብት ተሟጋችነታቸዉ ያከበሩ-ያደነቁ ያወደሷቸዉ ሊዩ ለቻይና መሪዎች ወንጀለኛ ናቸዉ።የአልፍሬድ ኖቤል ምኞት ኑዛዜን ለመጠበቅ የተባለዉ ሽልማትም አስራ-አንድ አመት እስራት ለተበየነባቸዉ ሰዉ መሰጡቱ የቻይና ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ማ ዣኦሹ እንዳሉት የሐያሏን ቻይናን ሐያል ሕግ መናቅ ነዉ።

«የሰላም ኖቤል ሽልማትን እስራት ተበይኖበት ወሕኒ ለሚገኝ ወንጀለኛ መሰጠቱ የኖቤል ኮሚቴዉ ለቻይና ሕግ ከበሬታ እንደሌለዉ አመልካች ነዉ።»

Flash-Galerie Oslo China Nobelpreis Liu Xiaobo Leerer Stuhl
ከግራ ሁለተኛዉ ባዶ እንደሆነ ድግሱ አበቃምስል AP

የፖላንድ፥ የመላዉ ምሥራቅ አዉሮጳ አልፎ ተርፎ የኢትዮጵያ ሶሻሊስታዊ ሥርዓት ከሁሉም በላይ ጠንካራዉ የሶቬት ሕብረት ኮሚንስታዊ ሥርዓት መናድ በጀመረበት በ1980ዎቹ ማብቂያ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ቤጂንግም ወላፈኑ ይገርፋት ነበር።የወላፈኑ ግመት የቻይና ወጣቶችን በተለይ የዩኒቨርስቲ መሪዎችን በ1989 ካደባባይ ሲያፈስ የበርሊን፥የዎርሶ፥ የቡካሬስቱ እዉነት ቤጂግም ሊደገም ነዉ-አሰኝቶ ነበር።

የሕዝባዊት ቻይና ሕዝባዊ ጦር «የሕዝብ ጥያቄ ያነገቡ» የተባሉ ተማሪዎችን ሰልፍ ታይናሚን አደባባይ ላይ ሲደፈልቀዉ ብዙ የተባለ ብዙ የተሰኘለት ለዉጥ ብዙ-እንዳስባለ እንዳሰኘ ቀረ።ከሞት-እስራት የተረፉት የብዙዎቹ ወጣቶች፥ እንደ ወጣት የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ሰልፈኛዉን የተቀየጡት የሊዩና የብዙ ብጤዎቻቸዉ ሕልም-ምኞትም ተቀጨ።ተስፋዉ ግን በተለይ ለሊዩ ጠወለገ እንጂ በርግጥ አልደረቀም ነበር።

ባለፈዉ አርብ በኦስሎዉ ሥነ-ሥርዓት ላይ የኖርዌዋ የፊልም ተዋኝ ሊፍ ኡልማን ያነበበችዉና ሊዩ ከመታሰራቸዉ በፊት የፃፉት-መልዕክት እንዳለዉ ያዘመን-በሕወታቸዉ ልዩ ሥፍራ አለዉ።

«ከግማሽ ምዕተ-አመት በሚበልጠዉ የሕይወቴ ሒደት ዉስጥ ሰኔ አራት 1989 ከፍተኛ ለዉጥ የተደረገበት ልዩ ጊዜ ነዉ።እስከ ዚያ ጊዜ ድረስ ከቻይና ባሕላዊ አብዮት በሕዋላ የኮሌጆች የመግቢያ ፈተና ሲሻሻል ዩኒቨርስቲ ለመግባት «ክፍል ሰባ-ሰባት» ከሚባለዉ ከመጀመሪያዉ መደብ መሐል ነበርኩ።ከቢኤ እስከ ኤም ኤ እስከ ፒ ኤች ዲ የነበረዉ የትምሕርቴ ሒደት ምንም እክል አልገጠመዉም ነበር።»

ያቺ ዕለት የሰዉዬዉ እንዳሉት ኑሮ-ሕይወታቸዉን ለወጠች።ፕሮፌሰፈሩ የመብት ተሟጋች ሆኑ።እና የቻይና መንግሥት ቀንደኛ ጠላት። ሊዩና ብጤዎቻቸዉ የሰብአዊ፥የመናገርና የመፃፍ መብቶች እንዲከበሩ፥ የሕግ የበላይነት እንዲኖር ያቀረቡና የሚያቀርቡት ጥያቄ-የቻይና መንግሥት ሕዝባዊ የሚለዉን ኮሚንስታዊ ሥርዓት ለማፍረስ በዉጪ ሐይላት የሚቀነባበር ሴራ ነፀብራቅ አድርጎ ነዉ-የሚያየዉ።

ሊዩና ብጤዎቹን መደገፍ-መሸለምም ለቤጂንግና ለተከታዮችዋ ኮሚንስታዊዉን ሥርዓት ለማዳከም በምዕራባዉን የሚደረግ ደባ አካል ነዉ።እርግጥ ነዉ ቻይና ከኖቤል ሸላሚ ኮሚቴዉ ጋር ስትጋጭ ወይም ሸላሚ ኮሚቴዉን ስታስፈራራ ያሁኑ የመጀመሪያዋ አይደለም።

የቻይና መንግሥት ዲሞክራሲያዉ ለዉጥ በጠየቁ ተማሪዎችን ላይ በወሰደዉ የሐይል እርምጃ ከመብት ተሟጋቾች፥ ከምዕራባዉያን መንግሥታትና መገናኛ ዘዴዎች የሚዥጎደጎድበት ትችት-ዉግዘት ባየለበት በ1989 የኖርዌዉ የኖቤል ኮሚቴ የቲቤቶቹ መንፈሳዊ መሪ ዳላይ ላማን መሸለሙ ቻይኖችን ክፉኛ ያስቆጣ፥ የምዕራባዉን ሴራ ለሚሉት ምክንያትም ማረጋገጪያ አይነት ሆኖ ነበር።

አንድ የሊዩ የቅርብ ወዳጅ በቀደም እንዳሉት የዛሬዋ ቻይና በፖለቲካ-ምጣኔ ሐብታዊ ጉልበቷ የከሐያ-አመቷ በፊቷ አልነበረችም።ዳላይ ለማ እንዳይሸለሙ ለማገድ፥ ወይም ወዳጆችዋ በሽልማቱ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንዳይገኙ ለማሳደም አልቻለችም ዛሬ ግን ጠንክራለች።ጠንካራዋ ቻይና ሊዩን ወሕኒ ቤት፥ ባላቤታቸዉን በቁም ማሰሯ-የሸላሚዉ ኮሚቴ ሊቀመንበር እንዳሉት የጥንካሬዋን ደረጃ ማጠያያቁ አልቀረም።

«ብዙዎች ሊዩ ሐገራቸዉ እንድትተዳደርበት የሚፈልጉትን በመናገራቸዉ ብቻ ቻይና አስራ-አንድ አመት እስራት መበየኗ ቻይና ባአሁኑ ያላት ጥንካሬ ሁሉ ድክመቷን የሚያጎላ ነዉ እያሉ ይጠይቃሉ።»

ለቤጂንጎች ግን የድክመት ጥንካሬ-ጉዳይ አይደለም።ሥርዓታቸዉን የመጠበቅ፥የሐያልነታቸዉን ልክ የማሳየት ጉዳይ እንጂ።በርግጥም አሳያች።ወይም ለማሳየት ሞከረች።ሽልማቱ በታወጀ ማግስት በኖርዌ ላይ የምጣኔ ሐብት ማዕቀብ ጣለች።

የቀድሞዉ የኩባ መሪ ፊደል ካስትሮ በቅርቡ በፃፉት መጣጥፍ «ይሕ የተከበረ ሽልማት እንደ ከዚሕ ቀደሙ ሁሉ የርዕዮተ-አለም ማጥቂያ ሆነ---አሉ።የካስትሮ ደቀ-መዝሙርና የዩናይትድ ስቴትስ «ጠላት» የሚባሉት የቬኑዝዌላዉ ፕሬዝዳት ሁጎ ሻቬዝ «ሊዩ ሌላዉ ኦባማ ናቸዉ።»አሉ።

Jahresrückblick 2010 International Norwegen China Friedensnobelpreis Verleihung an Liu Xiaobo in Oslo Thorbjörn Jagland Flash-Galerie
ሽልማቱ ባዶዉ ወንበር ላይምስል AP

የኩባ፥ የቬኑዙዌላ፥ የቬትናም፥ የሰሜን ኮሪያ፥ መንግሥታት በድግሱ አልተገኙም።ኮሚንስቶቹ ወይም ኮሚንዝምን ደጋፊዎቹ በድግሱ ላይ ያለመገኘታቸዉ ምክንያት ኮሚንስታዊ አድነትን ለማሳየት ነዉ-የሚል ምክንያት አለዉ።ለኢራንና ለሱዳን የኖቤል-ኮሚቴዉ የኖርዌ-ኖርዌ የምዕራብ አለም ምዕራቡ የአሜሪካ በመሆኑ ወይም ከቻይና ጋር ጠንካራ ምጣኔ ሐብታዊ ግንኙነት ሥላላቸዉ ከድግሱ ቢቀሩ ብዙ አላስደቀም።

የምዕራቦቹ ጥብቅ ወዳጆች፥ የስዑዲ አረቢያ፥ የግብፅ፥ የቱኒዝያ፥ የሞሮኮ፥ የአልጀሪያ ተወካዮችም አርብ ከኦስሎዉ አዳራሽ አልነበሩም።በሺ-የሚቆጠር የመብት ተሟጋቾች ያሰሩት የነዚሕ ሐገራት ነገስታትና አምባገነኖች ተወካዮች ከድግሱ የመቅረታቸዉ ሰበብ ቻይናን ስለሚወዱ፥ ወይም ምዕራቦችን ሥለሚጠሉ አይደለም።«ነግ በኔ» ብለዉ እንጂ።

ሩሲያም አልተገኘችም።ሐያሏ ሐገር-ለጊዜዉ ከነግብፅ ተደምራለች።ግን ያጠያይቃል።ካዛክስታን-«ኦስሎ የሚገኘዉ አምባሳደሬ በጣም ሥራ-ሥለበዛባቸዉ» ብላ ቀርታለች።ሲሪላንካም እንዲሁ።እዉነተኛዉ ምክንያት የቻይና ተፅዕኖ ተብሏል።

ዩናይትድ ስቴትስ ኦስሎ ከሚገኙ አምባሳደሯ በተጨማሪ «ለድግሱ ልዩ ድምቀት ለመስጠት» የምክር ቤት አፈ-ጉባኤዋን ጭምር ነበር የላከችዉ።የካቡልን መንግሥት ለሐሚድ ካርዛይ ያስረከቡት ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎችዋ ናቸዉ።ኢራቅን ከነመንግስቷ የዩናይትድ ስቴትስን ያክል የሚደግፍ፥ የሚያማክር-ሐገር የለም።

ዩናይትድ ስቴትስ ለምታስተባብረዉ የኖርዌዉ ተወላጅ ለሚመሩት ለኔቶ የአፍቃኒስታን ጦርነት፥ የፓኪስታንን ያክል ሥልታዊ ተባባሪ ሐገር የለም።አፍቃኒስታን፥ ኢራቅ፥ ፓኪስታን በኦስሎዉ ድግስ ላይ አልተገኙም።በጥቅሉ በድግሱ ላይ እንዲገኙ ከተጋበዙ ስልሳ-አምስት ሐገራት ቻይናን ጨምሮ አስራ-ስምንቱ ሐገራት ግብዣዉን አልተቀበሉትም።

አንድ ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ዲፕሎማት እንዳሉት ግብዣዉን እንቢኝ ካሉት አምባሳደሮች ይልቅ ዝር ዝሩን የሚያዉቁት መግሥታቱ ወይም በኦስሎ የቻይና ኤምባሲ ነዉ።

«የማይገኙ ብዙ ኤምባሲዎች አሉ።እንደሚመስለኝ ምክንያቱን ለማወቅ ቀላሉ ነገር የቻይናን ኤምባሲ መጠየቅ ነዉ።»

ብዙዎች ሳይጠይቁ መልሰዉታል።«የቻይና ዲፕሎማሲያዊ ጡንቻ፣እና አፀፋዉን ፍራቻ።» እያሉ።

ጀርመናዊዉ ጋዜጠኛና የመብት ተሟጋች ካርል ፎን ኦስየትስኪ የ1935ቱን ኖቤል የሠላም ሽልማት ማሸነፉ-የያኔዋን የናትሲ ጀርመንን ቁጣ ቀስቅሶ ነበር።እስር ቤት የነበረዉ ተሸላሚም ሽልማቱን ለመቀበል አልቻለም ነበር።ሽልማቱ ለኦስየትስኪ መሰጠቱን የተቃወሙ ሁለት የሸላሚዉ ኮሚቴ አባላትም ራሳቸዉን ከአባልነት አግልለዋል።

በ1973 ለዩናይትድ ስቴትሱ የፀጥታ ጉዳይ አማካሪ ለሔንሪ ኪስንጀርና ለቬትናሙ ዲፕሎማት ለ-ሊ ዱር ቶ የተሰጠዉ ሽልማትም ብዙ አወዛግቧል።በተለይ የቬትናሙ ዲፕሎማት ቶ «ሐገሬ ገና ሠላም ስሌላት የሰላም ሽልማቱን አልቀበልም ማለታቸዉ»የያኔዉን አለም ጉድ አሰኝቶ ነበር።

የ1994ቱ ሽልማት ለያኔዉ የእስራል ጠቅላይ ሚንስትር ለይትሳቅ ራቢን፥ ለዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሺሞን ፔሬዝና ለፍልስጤም ነፃ አዉጪ ድርጅት ሊቀመንበር ለያሲር አረፋት መሰጡ ብዙ አወዛግቦ ነበር።በተለይ አረፋትን እንደ አሸባሪ ይቆጥሩ የነበሩ ወገኖች የሳቸዉን መሸለም አዉግዘዉታል።

በሁለት ሺሕ ሰባት የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዝዳት አል-ጎር በሁለተኛዉ አመት ያሁኑ የአሜሪካ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ መሸለማቸዉ «ምን-ሠርተዉ» የሚል ጥያቄና ተቃዉሞ-ቀስቅሶ ነበር።
ኖቤል የሰላም ሽልማት በርግጥ ብዙ ጊዜ አወዛግቧል።የዘንድሮዉን ያክል የዲፕሎማሲ ዘመቻ ተከፍቶበት፥የምጣኔ ሐብት፥የፖለቲካ ጡንቻ አማዞ-ግን አያዉቅም።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ
ሒሩት መለሰ