1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ጤና ድርጅት፤ የአስቸኳይ ጊዜ በኢትዮጵያ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 2 2012

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ኃላፊ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምን የሚቃወሙ እና የሚደግፉ ፊርማዎች በኢንተርኔት እየተሰበሰቡ ነው። በኢትዮጵያ የኮሮና ተሐዋሲ መዛመትን በመስጋት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጓል። የኢትዮጵያ አየር መንገድን በኮሮና ተሐዋሲ ምክንያት ከፍተኛ ኪሳራ ደረሰብኝ ብሏል።

https://p.dw.com/p/3ak3M
Logo der Weltgesundheitsorganisation
ምስል AP

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ጥርስ ተነክሶባቸዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊው ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ከሥልጣናቸው እንዲነሱ የተጀመረው ዘመቻ ጠንከር ብሎ ታይቷል። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ሳይቀሩ ኃላፊው ላይ ቅሬታቸውን እና ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። በዚያው መጠን በተለይ አፍሪቃውያን መሪዎችን ግንባር ቀደም የኾኑበት የዶክተር ቴድሮስ ድጋፍም ታይቷል። በኹለቱም ወገን የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል። የዛሬው የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ቅኝት ዋነኛ ማጠንጠኛ ነው። በኮሮና ተሐዋሲ ምክንያት ከፍተኛ ኪሳራ ደረሰብኝ ስላለው የኢትዮጵያ አየር መንገድም የምንለው ይኖረናል። ኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮና ተሐዋሲን በተመለከተ ስለወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም አስተያየቶችን አሰባስበናል።

ድጋፍና ተቃውሞ በዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በዓለም ዙሪያ የኮሮና ተሐዋሲ ሥርጭትን በተመለከተ የወሰዷቸው ርምጃዎች በርካታ ድጋፍም ብርቱ ተቃውሞም አስነስቶባቸዋል። ተሐዋሲው በጊዜ እንዳይቀጭ የተሳሳተ መረጃ ሰጥተዋል በሚል የሚከሷቸው በርካቶች ናቸው። የለም ተሐዋሲውን ለመዋጋት ጥረት እያደረጉ ነው የሚሉ ደጋፊዎቻቸውም ብዙዎች ናቸው።

ከተቃዋሚዎቻቸው መካከል ዋነኛው እና ብርቱው የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራም ናቸው። ፕሬዚደንቱ ጠዋት የጻፉትን አንዳንድ ጊዜ ከሰአት የሚቀይሩ አይነት ቢኾኑም በዓለም ጤና ድርጅት ላይ ግን ጥርሳቸውን የነከሱ ይመስላል። ረቡዕ ዕለት የትዊተር ገጻቸው ላይ ያሰፈሩትም ይኽንኑ ያመላክታል።

የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ትዊት

አራት መቶ ስድሳ ሺህ ግድም ሰዎች የወደዱት የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ጽሑፍ፦ «ቻይና ተኮር» የኾነ ላሉት የዓለም ጤና ድርጅት ሀገራቸው ዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጓን ሊያጤኑበት እንደኾን ይጠቊማል። «እንደ ዕድል ኾኖ ድንበሮቻችንን ለቻይና ክፍት እንድናደርግ የመከሩንን ገና ከመጀመሪያውም ውድቅ አድርጌያለኹ» ይላል ጽሑፉ። ስለምንስ የተሳሳተ መረጃ ሰጡን ሲሉም ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅቱን በመውቀስ ጽሑፋቸውን ያጠናቅቃሉ። ለትዊተር ጽሑፋቸው 78 ሺህ ሰዎች አስተያየት ሰጥተውበታል።

ኤች ኬ ሊክስ የተባለ የትዊተር ተጠቃሚ ፕሬዚዳንቱ ከዚህ ቀደም የጻፉትን ያያያዘው ከሳቅ እና ተደጋጋሚ ጥያቄ ምልክቶች ጋር ነው። የተያያዘው የትዊተር መልእክት ላይ ፕሬዚደንቱ፦ «የኮሮና ተሐዋሲ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገባ ነው በቊጥጥር ስር የዋለው» ሲል ይነበባል። የዩናይትድ ስቴትስ የጤና ባለሞያዎች እና የዓለም ጤና ድርጅት «በትጋት እና በብቃት» ተግባራቸውን እየተወጡ መኾናቸውንም ይጠቊማል። ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ጽሑፉቸውን ትዊተራቸው ላይ ካሰፈሩት ከአንድ ወር ከሦስት ሳምንት አልበለጠውም።

አሜሪካዊቷ አንጋፋ ተዋናዪት ሚያ ፋሮው እዛው የፕሬዚደንቱ ትዊተር ላይ «የገዛ ቸልተኝነትን እንደተለመደው ማስቀየሺያ» ስትል ተችታለች። «ፔተር ናቫሮ ገና ጥር ወር ላይ በደንብ እንደነገረኽ ኹላችንም እናውቃለን። ምንም ያለማድረግህ፤ አለመዘጋጀትህ እና መዝረክረኩ በመቶ ሺህዎች አሜሪካኖችን እንዲታመሙ» አድርጓል ስትል ፕሬዚደንቱን ወርፋለች። የፕሬዚደንቱ የምጣኔ ሐብት አማካሪ ፔተር ናቫሮ ለዶናልድ ትራምፕ የጻፉት ነው የተባለ ማስታወሻ ኢንተርኔት ላይ ይገኛል። አማካሪው፦ የኮሮና ተሐዋሲ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አሜሪካውያንን ሕይወት ሊቀጥፍ እንደሚችል፤ 6 ትሪሊዮን ዶላር ሊያሳጣ እንደሚችል መጠቆማቸውን አክሲዮስ የተባለው ድረ-ገጽ ጽፏል። በርካቶችም ይኽን ሠነድ ተቀባብለውታል።

በዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲካ እሰጥ አገባ ዴሞክራቶቹን የሚደግፉ የመገናኛ አውታሮች ከላይ የቀረቡትን መረጃዎች እና ሌሎችን በማጣቀስ ፕሬዚደንቱ የኮሮና ተሐዋሲን እንደዋዛ ዐይተውታል በሚል በቀጣይ ምርጫ ድምፅ ለማሳጣት በትጋት እየሠሩ ነው። የፕሬዚደንቱ ደጋፊ መገናኛ አውታሮች እና ሬፐብሊካን በበኩላቸው ሀገራቸው ለገጠማት የጤና ቀውስ ተጠያቂው የዓለም ጤና ድርጅት እና ኃላፊው ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም እንደኾኑ በመናገር ላይ ናቸው።

ከዚያም ባለፈ ከሥልጣናቸው እንዲነሱ የሚጠይቅ ፊርማ ማሰባሰብ ተጀምሯል። በበርካታ ቋንቋዎች የተጻፈው የፊርማ ማሰባሰቢያ ጽሑፍ የሚጀምረው፦ ቴድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ  ከኹለት ወራት ከዐሥራ አምስት ቀናት በፊት ከቻይና የተቀሰቀሰውን ተሐዋሲ የዓለም የጤና ሥጋት ብለው አላወጁም በሚል ነው። «ኹላችንም እንደምናውቀው የኮሮና ተሐዋሲ በአኹኑ ወቅት በሕክምና የሚድን አይደለም።  በአምስት ቀናት ብቻ በተሐዋሲው የተጠቊ ሰዎች ቊጥር በዐሥር እጥፍ ነው የጨመረው። ለቊጥሩ መጨመርም ቴድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ ኮሮና ተሐዋሲን አሳንሰው ከማየታቸው ጋር ይገናኛል። ቴድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ በዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት የያዙት ኃላፊነት አይመጥናቸውም ቴድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ በአስቸኳይ ሥልጣናቸውን እንዲለቊ እንጠይቃለን» በማለት ይነበባል። የፊርማ ማሰባሰቡ ለተባበሩት መንግሥታት በሚል የተጀመረው ኦሱካ ዪፕ በሚል ስም ነው።

Schweiz PK WHO Tedros Adhanom Ghebreyesus zu Coronavirus
ምስል picture-alliance/Keystone/S. Di Nolfi

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊው ቀድሞውኑም ችግር አለባቸው ሲሉ የሚከሱ በርካቶች ናቸው። በተለያየ ጊዜም ጽሑፎች በኢንተርኔት ተለቀዋል። በተለይ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የኢትዮጵያ የጤና እና በኋላ ላይም የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ በደል መፈጸማቸውን በመጥቀስ የሚወቅሱ ጽሑፎችም እዛው ኢንተርኔት ላይ ተሰራጭተዋል።

የቴድሮስ ምላሽ

ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በበኩላቸው ዘመቻ ከተከፈተባቸው ወራቶች እንደተቆጠሩ፤ ዘረኛ ስድቦችን ከማስተናገድ ባሻገር ካለፉት ኹለት እና ሦስት ወራት አንስቶ የግድያ ዛቻ እየደረሰባቸው መኾኑን ተናግረዋል። ኮሮና ተሐዋሲን የፖለቲካ መጠቀሚያ አታድርጉት ሲሉ በጋዜጣዊ መግለጫቸው የተናገሩት ኃላፊው አንዳንድ ሰዎች ጥቊር ወይንም ኔግሮ እያሉ ስም እየሰጧቸው መኾኑን ጠቅሰዋል።  «ጥቊር ወይንም ኔግሮ በመኾኔ እኮራለሁ»ም ብለዋል። ከዚህ መግለጫቸው በኋላ በርካታ የአፍሪቃ መሪዎች ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ድጋፋቸውን በማሳየት ላይ ናቸው።

የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማኃማት ትዊተር ላይ፦ «የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት በዓለም ጤና ድርጅት እና አመራር ላይ የከፈተው ዘመቻ አስደምሞኛል» ብለዋል። «የአፍሪቃ ኅብረት የዓለም ጤና ድርጅትን እና ዶ/ር ቴድሮስን ሙሉ ለሙሉ ይደግፋል፤ በዓለም ዙሪያ በጋራ ትኩረታችን የኮሮና ተሐዋሲን መዋጋቱ ላይ ማዋል አለብን። የተጠያቂነቱ ጊዜ ይደረስበታል» ሲሉም አክለዋል።

የበርካታ የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎች በተመሳሳይ ድጋፋቸውን ለዓለም ጤና ድርጅት እና ኃላፊው አሰምተዋል። ከዚያም ባሻገር በኢንተርኔት ላይም ዋና ኃላፊውን በማሞገስ የድጋፍ ማሰባሰብ ፊርማ እየተፈረመ ነው።

የድጋፍ ፊርማው እንዲህ ይነበባል። «የተግባር ጥሪ። ከዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ጎን እቆማለሁ» በሚል ርእስ ነው የሰፈረው። የድጋፍ ፊርማው ዶ/ር ቴድሮስ የኮሮና ተሐዋሲን ለማጥፋት በትጋት እየሠሩ መኾናቸውን ይጠቅሳል። «ኾኖም አንዳንድ ሰዎች ከሥልጣናቸው እንዲነሱ መሰረተ ቢስ ክስ በመክፈት የፊርማ ማሰባሰብ ጀምረዋል» በማለት ለጠንካራ የሕዝባዊ አገልግሎታቸው ድጋፋችንን መስጠት አለብን በማለት በአራት ቋንቋዎች በአጭሩ ተጽፏል።

ያሬድ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ፦ «ዶ/ር ቴድሮስ አድህኖም ከጎኑ እንሰለፋለን ማንም በእፍሪካነቱ የሚኮራ የኢትዮጵያ ልጅ የዘረኝነት ጥቃት ሊደርስበት አይገባም አሁንም እንደጥንቱ ትከሻ ለትከሻ ገጥመን እንታገለዋለን!! ዘረኝነት ይውደም!!» ሲል ጽፏል።

«እኔ ከዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ጎን እቆማለሁ ስለ ብቃቱም እመሰክራለሁ!!» በማለት ሰው የድጋፍ ፊርማ እንዲሰጥ በትዊተር የጠየቊት ደግሞ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚንሥትር መላኩ አለበል ናቸው።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ በሚል የትዊተር ተጠቃሚ የቀረበ ጽሑፍ ደግሞ፦ «የአፍሪቃ መሪዎች ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን ከትራምፕ እየተከላከሉ ነው። እኛም ከጎኖት ነን እንበላቸው» ሲል ይነበባል።

አዳኙ ካሜራ በተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «እውነት ግን ለቴድሮስ ድጋፍ ስትሰጡ ማዕከላዊ ገብተው የተሰቃዩ ኢትዮጵያውያን ህመም ሳይሰማቹህ ቀርቶ ነው? ወይስ ቴድሮስ የሚገኝበት ድርጅት እንጂ እንደግለሰብ የሰራው ጥፋት የለም ብላቹህ ነው?» የሚል ጥያቄ ሰፍሯል።

«እንደዛ ከሆነ ጌታቸው አሰፋ፣ በረከት ስምኦንና ስብሃት ነጋም እንደድርጅት እንጂ በግለሰብ ደረጃ የሰሩት ጥፋት የለም በሉና» ይላል ጽሑፉ። «እነሱ ናቸው ያስቀመጡት እነሱ የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ» ደሳለን አንዳርጌ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ የጻፉት ነው።

ሉቃስ አንደርሰን የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ቀጣዩን ብለዋል። «ቴድሮስ አድሃኖም እንዳይመረጥ በተደረገው ካምፔን ግምባር ቀደም ተሳታፊም አስተባባሪም ነበርኩ። ሆኖም በአፍሪካ ኢትዮጵያዊነቱ ነጮች የመዘዙበትን ዘመቻ በፍፁም አልቀላቀልም ይሄ ለኔ ባንዳነት ነው ነገር ግን ቴድሮስን በግሌ ባገኘው ልበቀለው ዝግጁ ነኝ ነገር ግን በመንጋ አልቃወምም በመንጋ አልደግፍም» ሲል ይጠናቀቃል።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

Friedensnobelpreis 2019 Äthiopien | Ministerpräsident Abiy Ahmed
ምስል picture-alliance/dpa/B. Pedersen

በኢትዮጵያ የኮሮና ተሐዋሲን ለመዋጋት በሚል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉ ሌላው በማኅበራዊ መገናኛ አዴዎች አነጋጋሪ ጉዳይ ነበር። የተሰራጨዉ መግለጫ የሚንስትሮች ምክር ቤት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉን ከመግለፁ በስተቀር የተደነገበትን ዕለት፣ ዝርዝር አፈፃፀሙንም ሆነ የሚፀናበትን ጊዜ አለመጠቀሱ መግለጫው ብዙዎችን ግራ አጋብቶ ነበር።

የሚንስትሮች ምክር ቤት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉን ከመግለፁ በስተቀር የተደነገበትን ዕለት፣ ዝርዝር አፈፃፀሙንም ሆነ የሚፀናበትን ጊዜ አልጠቀሰም። ረቡዕ መጋቢት 29 ቀን ኢንተርኔት ላይ የተሰራጨው መግለጫ መጋቢት 30 ቀን 2012 በሚል ነው የሚጠናቀቀው።  

ሐብታሙ ሙኼ ፌስቡክ ላይ በሰጡት አስተያየት፦ «እውነት ለመናገር መግለጫውን ደግሜ ደጋግሜ አነበብኩት አዲሱ አዋጅ ምን እደሆነ የሚገልፅ የለም ምንም አልገባኝም አብቹ ምን ለማለት አስቦ ይሆን??» ሲሉ ግራ መጋባታቸውን ገልጠዋል። «ለእኔ ደግሞ አዋጅ ወይስ ስብከት አስብሎኛል» ያሉት ደግሞ ሶፎኒያ መላኩ ናቸው።

የአብዱ ሰኢድ የፌስቡል ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል፦ «የአስቸኳይ አዋጁ የተድበሰበሰና ግልፅነት የጎደለው ነው የአብይ አስተዳደር የህዝብን ደህንነት ችግር የጣለ ከመሆኑም በላይ የህዝባችንን ፍላጎትና ጥቅም ያላገናዘበ ነው፡፡ እጅግ አስቸጋሪ በሆነበት በአሁኑ ወቅት ትጥቅ አስፈታለሁ በሚል ስበብ ህዝብን የበለጠ ሽብርና ሁከት ውስጥ እያስገባ ነው፡፡»

ገብረስላሴ ኃይለስላሴ፦ «በለመዱት የካድሬ ቋንቋ ግራ እያጋቡን ነው» ብለዋል። በቀሩን ጥቂት ደቂቃዎች ደግሞ እስኪ በኮሮና ቀውስ ከፍተኛ ገቢ እንዳጣ ስለገለጠው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የተሰጡ አስተያየቶች እናሰማችሁ።

በኮሮና ተሐዋሲ መዛመት የተነሳ ዓለም አቀፍ በረራዎቹ እንደቀነሱበት የገለጠው የኢትዮጵያ አየር መንገድ 550 ሚሊዮን የዩኤስ ዶላር ገቢ ማጣቱን የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ለዶይቸ ቬለ (DW)ተናግረዋል።

Tewolde Gebremariam CEO Ethiopian Airlines
ምስል Reuters/T. Negeri

የዋና ሥራ አስፈጻሚው ንግግር በተመለከተ ተሾመ አብርሃም፦ «ሲጀምር በዚህ ሰዓት ስለ ትርፍና ኪሳራ የሚወራበት ግዜ አይደለም። የገረመኝ ግን በዚህች አጭር ግዜ ይህን ያክል ብር መክሰሩ ሳይን እስከአሁን የሚሰራው ብር ወደየት እደሚገባ ነዉ» ብሏል።

«ኢሀዲግ ኮፈኑን አጥልቆ ኢትዮጵያን በፊት ጥርሱ ሲግጣት ኖረ አሁን ደግሞ ብልፅግና ኮፈኑን አውልቆ በመንጋጋው ቁርጥም አደረጋት» የፍቅር ይሻላል  አስተያየት ነው።

ሙኬ ሱልጣ ፦ «የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚሕም የባሰ ቀውስ ውስጥ ብንገባም በረራውን ማቆም የለበትም በርቱ» ብለዋል።  ዳዊት ዘውዴ፦ «ኣሁን ወደ ቻይና በረራ ማቆም ለምን ኣስፈለገ ቻይና ከቫረሱ ነፃ በሆነ ሰዓት?» ሲሉ ጠይቀዋል። ኢትዮ የጁ ማን፦«አየር መንገዱ በረራውን ያቁም ብለን ጠየቅን!ይኸው ቀድሞ በረራውን አላቆምም ብሎ ብዙ መዘዝ ይዞብን መጣ የማይረባ ዶላር ለመለቃቀም ብሎ» ሲሉ ቅሬታቸውን አስፍረዋል። «ቅድሚያ ለሰው ሕይወት» የአወቀ ንጉሤ አስተያየት ነው። አበቃን።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ