1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም የገንዘብ ድርጅት ዕዳ እና ኬንያ

ረቡዕ፣ መጋቢት 22 1996

ኬንያ በሙስና እና በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት ላለፉት ሶስት ዓመታት ከዓለም የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ ተጠቃሚነት ታግዳ ነበር ። ድርጅቱ እገዳውን በማንሳት ባለፈው ህዳር የብድር ርዳታ ፈቅዶላታል ። ይሁንና የሃገሪቱ የሲቪክ ማህበራት መንግስት ሌላ ዕዳ ከመጨመር ሃገሪቱ የነበረባትን ዕዳ ማሰረዝ ይገበዋል በማለት ይከራከራሉ ።

https://p.dw.com/p/E0fs

ያለፈው ዓመት ታህሳስ ስልጣን የጨበጡት የኬንያው ፕሬዝዳንት ሙያዊ ኪባኪ ለህዝባቸው ከገቡዋቸው ቃል ኪዳኖች ውስጥ የተራባውን እና በቀን ከአንድ ዶላር በታች ገቢ የሚያገኘውን ህዝብ ህይወት ለማሻሻል የሚለው አንዱ ነበር ። ሥራቸው ለመመዘን ጊዜው አጭር ቢሆንም የሃገሪቱ የፖለቲካ ሂደት አቅጣጫ አያስተማምንም የሚሉት በርካታ ኬንያውያን ናቸው ። ኪባኪ ከዚህ በተጨማሪ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ርዳታ ሰጪዎችን እና የውጭ ባለሃብቶችን ቀልብ ለመሳብ የሚያደርጉት ጥረት ኑሮው ይሻሻላል የሚባልለትን ህዝብ እየጎዳ እንደሆነ እና ወደፊትም እንደሚጎዳ ይነገራል ።

ባለፈው ሳምንት በኬንያ ምዋለ ንዋይ ፍሰት ላይ ያተኮረ ጉባኤ ተካሂዶ ነበር ። መንግስት ለጉባኤው ታዳሚዎች ኬንያ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረች እንደሆነ ገልጿል ። ከዚህ ቀደምም በሙስና ላይ ዘመቻ መጀመሩን አስታውቆ ተቃዋሚ ድርጅቶች ያላመኑበት ነገር ግን በሙስና የተጠረጠሩ ያላቸውን ሃያ ሶስት ዳኞችንም አስሯል ። ተቃዋሚዎች ከዓለም የገንዘብ ድርጅት እና ከለጋሽ ድርጅቶች ርዳታ ለማግኘት የተጠነሰሰ ነው በሚል የዳኞቹን መታሰር ይቃወማሉ ። የዓለም የገንዘብ ድርጅት ከሶስት ዓመት በኃላ በኬንያ ላይ ጥሎ የቆየው ማዕቀብ እንዲነሳ ማድረጉ ተቃዋሚዎች የሚሉትን ሃሳብ የሚያጠናክር ይመስላል ። አይ ኤም ኤፍ ባለፈው ህዳር ዕገዳውን ከማንሳቱ በተጨማሪ የ250 ሚሊዮን ዶላር ፈቅዷል ። ሌሎች የገንዘብ ለጋሾችም አይ ኤም ኤፍ የከፈተውን በር ተከትለው በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ አራት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል የገቡት በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ነበር ።

ነገር ግን ይህ ለመንግስት ባለስልጣናት አስደሳች ዜና ፤ ለሲቪክ ማህበራት ደግሞ ጭንቀትን ፈጥሯል ። የኬንያ የሲቪክ ማህበራት መንግስት ብድር ከመቀበል ይልቅ የነበረውን ዕዳ ማሰረዝ አለበት የሚል አቋም አላቸው ። የኬንያ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ብሄራዊ ምክር ቤት የቀድሞው ሊቀመንበር የሆኑት ኦውር ኦንጋዌን ሲናገሩ መንግስት የሚበደረው ገንዘብ መጠኑ ከፍ ካለ ወለድ ጋ በመሆኑ ሸክሙ የህዝብ ነው ። ስለሆነም ልክ ለአካባቢ ሃገራት እንደተደረገው ሁሉ ለኬንያም ሌላ ብድር ከመስጠት ፤ መንግስትም ከመቀበል ይልቅ ሀገሪቱ ያለባት ዕዳ ሊሰረዝ ይገባል ብለዋል ። ኬንያ ያለባት የብድር ዕዳ እንዲሰረዝላት በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው ሌላው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሃገሪቱ አብዛኛውን ዓመታዊ ገቢዋን ለዕዳ ክፍያ እንደምታውል ገልጾ ይህ አካሄድ እንዲቀየር ይጠይቃል ። የፍትህ ምክር ቤት የተባለው ይኸው ድርጅት ባለፈው ዓመት የወጣውን የሃገሪቱን የበጀት ሰነድ ተመርኩዞ እንደሚለው ለትምህርት ሰላሳ በመቶ ፤ ለጤና አገልግሎት ስምንት በመቶ የሚጠጋ የወጪ ኪሳራ እንዳለባት ያሳያል ። የዚህ ዋነኛ ተጎጂውም ደሃው ህብረተሰብ ነው ። የፍትህ ምክር ቤት ኬንያ ያለባትን ዕዳ እና ገቢ በማነጻጸር እንደሚያስቀምጠው ዕዳዋ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ይህ ደግሞ ከብሄራዊ ዓመታዊ ገቢ ሁለት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር በሶስት እጥፍ ይበልጣል ።

የሃገሪቱ መንግስት ግን ይህን አሃዛዊ መረጃ እንደ መጨረሻ ማጠቃለያ አይቀበልም ። ኬንያ በርግጥ የ605 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ እንዳለባት አምኖ ከዚህ ውስጥ ግማሹ የሃገር ውስጥ ብድር በመሆኑ የሚያሰጋ አይደለም ይላል ። ይንደ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ አሃዛዊ መረጃ ሶስት ነጥብ ሶስቱ ቢሊዮን ዶላር ከሃገር ውስጥ ባንኮች እና አበዳሪዎች የተወሰደ ገንዘብ ነው ። ዕዳው ከሃገር ውስጥ ይወሰድ ከውጭ ይምጣ ብድሩ ሃገሪቱ በዕዳ የምትንቀሳቀስ እንደሆነች ያሳያል እና አንቀበለውም ። የዓለም የገንዘብ ድርጅ እና የዓለም ባንክ የብድር አካሄዱን እንደገና ይመርምሩ የሚለው የኬንያ ሲቪክ ማህበራት እና ድርጅቶች ጥያቄም እንደጨመረ ነው ።