1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ከተማና የፋተርሽቴትን ወዳጅነት

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 17 2005

ሰላምታና ምስጋናን በአማረኛ ቋንቋ ያቀርባሉ ጀርመናዊዉ የፋተር ሽቴተን ከተማ ነዋሪ። የዓለም ከተማ እና የፋተር ሽቴትን የእህትማማች ማህበት ዋና ተጠሪም ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/18NKm
Volksmusikgruppe aus Vaterstetten in Alem ketema _ Äthiopian 2004 Thema: Volksmusikgruppe aus Vaterstetten in Alem ketema _ Äthiopian 10-jährigen Jubiläum unserer Partnerschaft 2004 Autor/Copyright: DW/ Azeb Tadesse Hahn
ምስል DW/A. T. Hahn

ከአዲስ አበባ 185 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘዉ የመረሃ ቤቴ አዉራጃ እና እዚህ በደቡባዊ ጀርመን በባቫርያ ግዛት የምትገኘዉ ፋተርሽቴትን ከተማ የእህትማማችነት ማህበርን አቋቋሙዉ የትምህርት የባህል ልዉዉጥን ማድረግ ከጀመሩ ወደ ሃያ ዓመት ግድም ሊሆናቸዉ ነዉ።

Volksmusikgruppe aus Vaterstetten in Alem ketema _ Äthiopian 2004 Thema: Volksmusikgruppe aus Vaterstetten in Alem ketema _ Äthiopian 10-jährigen Jubiläum unserer Partnerschaft 2004 Autor/Copyright: DW/ Azeb Tadesse Hahn
ምስል DW/A. T. Hahn

« እስከ ዛሪ ለ 7 ግዜአት ወደ ኢትዮጵያ ሄጄ ሀገሪትዋን ጎብኝቻለሁ። በዚህም ኢትዮጵያን አንድ ቱሪስት ማወቅ ካለበት የበለጠ በደንብ አዉቃታለሁ ማለት እችላለሁ። ህዝቡንም በደንብ አዉቄዋለሁ እረዳዋለሁም ማለት እችላለሁ። ኢትዮጵያዉያን እጅግ ሰላማዊና እንግዳ ተቀባዮች መሆናቸዉን አይቻለሁ። ገጠር ሄጄ ጎጆ ቤት ዉስጥ ኖሪ አዉቃለሁ፤ በጎጆ ቤት ዉስጥ የሚኖሩ የምረዳቸዉ ቤተሰቦችም አሉኝ።»

በደቡባዊ ጀርመን በባቫርያ ግዛት ፋተርሽቴትን በምትባለዉ አነስ ያለች ከተማ ዉስጥ ነዋሪ የሆኑት እና «ዓለም ከተማ ፋተርሽቴትን» የተሰኘዉ የእህትማማች ማህበር መስራች ጀርመናዊዉ ሴፕ ክሌመንት ይባላሉ። በጎ,አ በ 1994 ዓ,ም ይህ ማህበር ሲቋቋም ማህበሩ ዋና ተጠሪ በመሆን ለአስራ ሰባት ዓመታት አገልግለዋል።

Volksmusikgruppe aus Vaterstetten in Alem ketema _ Äthiopian 2004 Thema: Volksmusikgruppe aus Vaterstetten in Alem ketema _ Äthiopian 10-jährigen Jubiläum unserer Partnerschaft 2004 Autor/Copyright: DW/ Azeb Tadesse Hahn
ምስል DW/A. T. Hahn

በጀርመኗ በፋተርሽታትን ከተማ ነዋሪ የሆኑት የማህበሩ የኮሚቴ አባል ከሆኑ ወ/ሮ ራሄል መኮንን ይህን ማህበር ከተቀላቀሉ አምስት ዓመት እንደሆናቸዉ ይናገራሉ። ማህበሩን ተቀላቅለዉ ጀርመናዉያኑ በዓለም ከተማ ለሚገኙ ህዝቦች የሚያደርጉት ስራና ጥረታቸዉን እንዲህ ያደንቃሉ።

በአሁኑ ግዜ የዓለም ከተማ እና የጀርመኗ ከተማ የፋተርሽቴትን ማህበር ዋና ተጠሪ አንቶን ሽቴፈን እንደገለጹት ማህበሩ ከተቋቋመ ሁለት የመዋለ ህጻናትን አንድ ቤተ-መጻህፍት በዓለም ከተማ ያቋቋመ ሲሆን፤ በመጭዉ ሳምንታት ሁምቦል ላይበረሪ በሚል ስያሜ ትልቅ ቤተ መጻህፍትን ገንብቶ እንደሚያስመርቅና ለምረቃዉ ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ ዝግጅት ላይ መሆናቸዉን ገልጸዉልናል። ማህበራችን ይላሉ አንቶን ሽቴፈን በመቀጠል ማህበራችን የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች መካከል የባህል ልዉዉጥ ብቻ ሳይሆን፤ በትምህርት ስልጠናዉ ዘርፍ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለህጻናቱ ማቅረብም ነዉ።

« ማህበራችን በዓለም ከተማና ፋተርሽታትን ከተሞች መካከል ያለዉን ነዋሪ ህዝብ በወንድማማችነት ማስተሳሰር ነዉ። ይህን ስል በመጀመርያ ደረጃ በአካባቢዉ ላይ ለህጻናት ትምህርት ድጋፍ መስጠት ነዉ። እስካሁን ሁለት ህጻናት መዋያ ሰርተናል አንድ አነስተኛ ቤተ መጻህፍትም አለን። በአሁኑ ወቅት 480 ህጻናት በመዋለ ህጻናቱ ለአንደኛ ትምህርት የሚያበቃቸዉን የትምህርት ዝግጅት ያደርጋሉ። በአስተማሪነት እና ህጻናቱን በመጠበቅ ባጠቃላይ 22 አዋቂዎች በዚሁ የማዋለ ህጻናት ተቀጥረዉ ያገለግላሉ። ለህጻናቱ በቂ የማንበብያ ቦታ ስለሌለን ተለቅ ያለ ህንጻ ሰርተን ከሰሞኑ ለማስመረቅ ዝግጅት ላይ ነን።»

Volksmusikgruppe aus Vaterstetten in Alem ketema _ Äthiopian 2004 Thema: Volksmusikgruppe aus Vaterstetten in Alem ketema _ Äthiopian 10-jährigen Jubiläum unserer Partnerschaft 2004 Autor/Copyright: DW/ Azeb Tadesse Hahn
ምስል DW/A. T. Hahn

በዓለም ከተማ እና በባቫርያ ግዛት በምትገኘዉ የፋተርሽቴትን ከተማ የእህትማማች ማህበር ሲመሰረት 43 አባለት እንደነበረዉ እና በአሁኑ ሰዓት 600 አባላት ማህበሩ እንዳቀፈ የሚገልጾት ሴፕ ክሊመንት፤ ማህበሩ ለመመስረት የበቃዉ በዚያን ግዜ የጀርመኗ ፋተር ሽቴትን ከተማ ከንቲባ የነበሩት ግለሰብ እና የሜንሽን ፉር ሜንሽን ማለት ሰዎች ለሰዎች» በሚል ስያሚ የሚታወቀው ግብረ ሰናይ ድርጅት ዋና አስተዳዳሪ ካርል ሃይስ በም ጓዷኛ በመሆናቸዉ እንደ ነበር አጫዉተዉናል። በዚህም የማህበሩ የመጀመርያ ተጠሪ ሴፕ ክሊመንት በጎ,አቆጣጠር 1996 ዓ,ም ኢትዮጵያን ለመጀመርያ ግዜ ለመጎብኘት ይጓዛሉ። ኢትዮጵያ እንደገባሁ የተሰማኝ ይላሉ ሴፕ ክሊመንት በመቀጠል ፤

«መጀመርያ ወደ ኢትዮጵያ ስሄድ የተሰማኝ ስሜት፤ ከዝያ በፊት የማለዉቀዉ ስሜት ነበር። ልክ ኢትዮጵያ እንደገባሁ ባዕድ ሀገር ሳይሆን እራሴ ሀገር እንደገባሁ ያህል ነበር የተሰማኝ። ይህ የሆነዉ በ1996 ዓ,ም ነዉ። ከአዲስ አበባ ወደ ገጠር ሄጄ ጎጆ ቤት ዉስጥ በእ ንግድነት ስቀመጥ፤ የተሰማኝ ይህ እኔ የተፈጠርኩበት መኖርያ ሀገሪ ነዉ የሚል ስሜት ነበር ያደረብኝ ። በጣም አስደሳችና ጥሩ ስሜት ነበረኝ። ይህ ነዉ ታድያ ለኔ አዲስ የምለዉ ተሞክሮዬ» የዚህ የሁለት ከተሞች ማህበር የኮሚቴ አባል የሆኑት ወ/ሮ ራሄል መኮንን በበኩላቸዉ ይህ ማህበር ሲመሰረት፤ የፋተር ሽቴትን ከተማ ከንቲባ በዓለም ከተማ የሚገኙ ህጻናትን አይተዉ ለህጻናቱ አንድ ነገር ለመስራት ወስነዉ ከተመለሱ በኋላ፤ በጎ አቆጣጠር 2000 ዓ,ም የመጀመርያዉ የህጻናት መዋያ ተገንብቶአል ሲሉ አጫዉተዉናል።

ጀርመናዉያኑ በግብርና የሚተዳደሩ ነዋሪዎች በብዛት በሚገኙባት እና በተለይ በጤፍና በማሽላ ምርቷ በምትታወቀዉ በመራሃቤቴዋ ዓለም ከተማ ነዋሪዎች እንግዳ ተቀባይነት ተማርከዉ፤ በከተማዉ የገበያ መሃል ያገኙትን የባህል አልባሳት፤ ባህላዊ ቁሳቁስ እና ሽሮ በርበሪን ገዝተዉ እዚህ ጀርመን ለቀሩት የማህበሩ አባላት ማሳየታቸዉ አልቀረም ኢትዮጵያዉያኑንም ፈላልገዉ እንጀራ አስጋግረዉ፤ ወጡን እራሳቸዉ ባመጡት በርበሪ እንደ ነገሩ ሰርተዉ የኢትዮጵያዉያኑን ባህል በማሰተዋወቅ ዳግም እርዳታ የሚያሰባስቡበትም ድግሶች በየግዜዉ ያዘጋጃሉ። ግን በማንኪያ በሹክያ መብላት የለመዱት ጀርመናዉያን ዓለም ከተማ ላይ እንደዉ ችግር አልገጠማቸዉ ይሆን ሴፕ ክሊመንት እንዲህ ይላሉ «በምንም አይነት የባህል ወይም የአኗኗር ቀዉስ አልገጠመኝም። ባንጻሩ የገጠመኝ የሚያባባ ሁኔታ ነበር ። የሰዉ ልጅ ህይወትን ከ1000 እና 2000 በፊት ወደኋላ መለስ ብዪ እንዳይ እንዳስብ አድርጎኛል። በጎ, አቆጣጠር 1996 ዓ,ም ኢትዮጵያ ዉስጥ የገጠመኝ የህዝቡ የአኗኗር ሁኔታ ከ2000 ዓመት በታሪክ የማዉቀዉን የሰዉ ልጅን የአኗኗር ሁኔታ ነዉ። ሰዎች ከባድ ሸክምን እየተሸከሙ በርቀት የሚጓዙበትን ነዉ ያየሁት፤ እናም እነዚህ ሰዎች ለምን ብስክሌትን አልፈጠሩም ስል እራሴን መጠየቄን አስታዉሳለሁ። ግን ሁኔታዉን ጠልቄ ስመለከተዉ እንኳን ስለ ብስክሌት ስለ ተሽከርካሪ ለማሰብ ቀርቶ፤ ለእግር መንገድ አዳጋች ነዉ። ቁልቁለት ሸለቆን አልፈዉ የሚጓዙበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ። በመጀመርያ አካባቢዉ ላይ እንደመጣሁ ሴቶች በእንስራ ዉሃ ተሸክመዉ ረጅም መንገድን ሲጓዙ ነበር ያየሁት። አሁን አሁን ደግሞ በቢጫ ደንበጃን ጭንቅላታቸዉ ላይ ተሸክመዉ ሲሄዱ ተመልክቻለሁ። እና ይህ ሁሉ የባህል የአኗኗር ቀዉስን ሳይሆን በጣም የሚያሳዝን የሚያስጨንቅ ስሜት ነዉ የፈጠረብኝ። ምክንያቱም ይህ አይነቱ አኗኗር በኛ ሀገር በጀርመን በርግጥም ከ2000 ዓመት በፊት የነበረ ሁኔታ ነዉ» የማህበሩ ኮሚቴ አባል ወሮ ራሄል መኮንን በበኩላቸዉ ጀርመናዉያኑ ከፋተርሽቴትን ወደ ዓለም ከተማ ለመሄድ ሲነሱ፤ ገንዘብ ቁሳቁስ፤ በማሰባሰብ አባት ልጁን እንደሚጠይቅ ተጨንቀዉ ተጠበዉ ነዉ።

Volksmusikgruppe aus Vaterstetten in Alem ketema _ Äthiopian 2004 Thema: Volksmusikgruppe aus Vaterstetten in Alem ketema _ Äthiopian 10-jährigen Jubiläum unserer Partnerschaft 2004 Autor/Copyright: DW/ Azeb Tadesse Hahn
ምስል DW/A. T. Hahn

በቅርቡ በወጣ ዘገባ እንደሚታወሰዉ «ሰዎች ለሰዎች» በሚል ስም የሚታወቀው ግብረ ሰናይ ድርጅት የአሰራር ግልጽነት እንደሚጎለው እንዲሁም ለድርጅቱ የሚያበረከት የእርዳታ ገንዘብ በማባከን ተወቅሷል። የአለም ከተማ እና የፋተር ሽቴትን የእህትማማች ማህበር በዚህ ረገድ ያለዉ የስራ ግልጽነት እስከም ድረስ ነዉ? የወቅቱ የባህበሩ ሊቀመንበር ጀርመናዊዉ አንቶን ሽቴፈን እንደሚሉት ከሆነ« ማህበራችን በርግጥ እጅግ ግዙፍ የሚባል አይደለም። በዚህም እንደ ትልልቅ ድርጅቶች በታዋቂ የሂሳብ አጣሪዎች ወጪ ገቢ የሚታይበት ሳይሆን፤ የማህበሩ አባላት ወጭ ገቢዉን ይቆጣጠራሉ፤ ዓመታዊ ስብሰባንም ያደርጋሉ። ኢትዮጵያ ደርሰን ስንመጣም ማህበሩ የሰራዉን፤ በቦታዉ ላይ ያለዉን ነገር ለአባላቱ ስብሰባ በመጥራት እናሳዉቃለን። ለሚደርስን ጥያቄዎች በግልጽነት መልስ እንሰጣለን፤ ማህበሩ በኪሱ ያለዉንም ገንዘብ የማህበሩ አባላት ያሳዉቃሉ፤ ገንዘቡን ይቆጣጠራሉ። ከጠቆጣጣሪዎቹ መካከል እንደዉም፤ አንዱ የቀረጥ ጉዳይ ባላሞያ ነዉ በዚህም ምክንያት፤ የምናገኘዉን ገንዘብ በትክክለኛ መንገድ ለወጭ እናዉላለን ማለት እችላለሁ» የዓለም ከተማ ፍተርሽቴትን የእህትማማች ከተሞች ማህበር አባላት ማህበሩ የተመሰረተበትን አስረኛ አመት ሲያከብሩ በሀገራቸዉ እንደሚያደርጉት ወዳጅን ለመጠየቅ ብስክሌት ይዘዉ እንደሚጓዙ ሁሉ ወደ ዓለም ከተማ ወዳሉት ዘመዶቻቸዉ ለመድረስ ከአዲስ አበባ ብስክሌት ይዘዉ የባህል ልብሳቸዉን አድርገዉ የባህል የሙዚቃ መሳርያን አንግበዉ ከአዲስ አበባ 185 ኪሎ ሚትር በብስክሌት ተጉዘዉ ዓለም ከተማ ደርሰዋል ባህላቸዉንንም ለነዋሪዉ አሳይተዉ አስረኛ አመት የምስረታ በዓላቸዉን በጋራ አክብረዋል። ይህንኑ ድግስና ጉዞ በቢዲዖ ቀርጸዉ በጀርመን በተለያዩ አጋጣሚዎችም በማሳየት ላይ ናቸዉ። በደቡባዊ ጀርመን በባቫርያ ግዛት በምትገኘዉ ፋተርሽቴትን አነስተኛ ከተማ ሲኖሩ አስር ዓመት እንደሆናቸዉ የነገሩን የማህበሩ የኮሚቴ አባል ወሮ ራሄል በበኩላቸዉ፤ ጀርመናዉያኑ ይህን ድርጅት በሁለቱ ህዝቦች መካከል ዘለቄታዊ የባህል ልዉዉጥ እንዲደረግ በትጋት እየሰሩ ነዉ በሀገሪ ልጆችና በተለይ በዓለም ከተማ ስም ጀርመናዉያኑን ማመስገን እወዳለሁ ብለዋል።

Volksmusikgruppe aus Vaterstetten in Alem ketema _ Äthiopian 2004 Thema: Volksmusikgruppe aus Vaterstetten in Alem ketema _ Äthiopian 10-jährigen Jubiläum unserer Partnerschaft 2004 Autor/Copyright: DW/ Azeb Tadesse Hahn
ምስል DW/A. T. Hahn

አዜብ ታደሰ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ