1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም እግር ኳስ ዋንጫና ጀርመን

ረቡዕ፣ ሰኔ 30 2002

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ባለፈው ምሽት ኔዘርላንድ ኡሩጉዋይን 3-2 በመርታት ከ 32 ዓመታት በኋላ እንደገና ለፍጻሜ ደርሳለች።

https://p.dw.com/p/OCSR
ምስል AP

የተጋጣሚዋ ማንነት የሚለይለት በዛሬው ምሽት ነው። በዚሁ ምሽቱን ጀርመንና ስፓኝ በሚያካሂዱት ግጥሚያ ታዲያ ማን ሊያሸንፍ እንደሚችል መተንበዩ በጣሙን ያዳግታል። ከሁለት ዓመታት በፊት የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊ የነበረው የስፓኝ ብሄራዊ ቡድን በርካታ ከዋክብትን ያሰባሰበ ሲሆን የጀርመን ወጣት ቡድን ደግሞ በቀለጠፈ አጨዋወቱ በዚህ የዓለም ዋንጫ ታላላቅ ለሚባሉት ፍርሃቻን ያስተማረው። በምሽቱ ግጥሚያ አሸናፊ ሆኖ ለዋንጫው ፍጻሜ ለማለፍ የኳስ ጥበብ ብቻ ሣይሆን ወኔና የትግል መንፈስም የግድ የሚያስፈልግ ነው የሚመስለው።

ወጣቱ የጀርመን ብሄራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪቃው የዓለም ዋንጫ ውድድር እስካሁን ባሳየው የአጨዋወት ጥንካሬና ውበት ዓለምን ሲያስደንቅ ነው የሰነበተው። ቀድሞ ከጥበብ ይልቅ በትግልና በጉልበት የሚታወቀው የጀርመን እግር ኳስ አጨዋወት ቡድኑን “ታንክ” አሰኝቶት የነበረበትን ዘመን ያለፈ ታሪክ ነው ያደረገው። የጀርመን ብሄራዊ ቡድን በረቀቀ የማጥቃት አጨዋወት እንግሊዝን 4-1 ከዚያም አርጄንቲናን 4-0 ቀጥቶ ከውድድሩ ሲያስወጣ የዓለም ጋዜጦች ውዳሤ እስካሁን ማለቂያ አላገኘም። በውድድሩ ዋዜማ የጀርመን ቡድን በእንዲህ ዓይነት ግሩም አጨዋወት ከዚህ ይደርሳል ብሎ የጠበቀ ብዙ አልነበረም። የዶቸ የስፖርት ፕሮግራም ባልደረባ አርኑልፍ በትቸርም በዚሁ ከተደነቁት አንዱ ነው።

“አልጠበቅኩም። ምክንያቱም ከዓለም ዋንጫው በፊት መላውን የቡድኑን ጨዋታዎች ተከታትያለሁ። እና ሁኔታው እንዲህ አልነበረም። አሁን ግን ቡድኑ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እያደገ ነው የመጣው። በራስ መተማመንን ለማዳበር ሲችል በዚህ መንፈስም ነው ከስፓኝ የሚጋጠመው። እና የማሸነፍ ጥሩ ዕድል አለው”

የጀርመን ብሄራዊ ቡድን አጨዋወት በዓለም ዙሪያ በጋዜጦች መወደሱንም እንደቀጠለ ነው። የስዊስ የሰንበት ጋዜጣ “ዞንታግ” “ታንክ የሚለው የጀርመን ገጽታ አክትሞለታል። የጀርመን ቡድን አሁን ወጣት፣ ቀልጣፋ፣ አጥቂና የሚወደድ ነው። ለዚህ ደግሞ ሉቭን የመሰለ አሠልጣኝ ነበር ያስፈለገው”

የአውስትሪያው “ኩሪር” ደግሞ ”የጀርመን እግር ኳስ ማስደሰቱን ይቀጥላል። ምናልባት ብዙዎች ሊሰሙት ወይም ሊያነቡት አይፈልጉ እንጂ ይህ የጀርመን ቡድን የዓለም ዋንጫ ባለቤት ለመሆን የሚችል ነው” ሲል አትቷል።

የደቡብ አፍሪቃው “ሰንዴይ ኢንዲፔንደንት” በጻፈው ሃተታ እንዳስረገጠው “የጀርመን ቡድን አርጄንቲናን በሚገባ ነው ያሽነፈው። የአርጄንቲና ቡድን ሽንፈት ብቻ አይደለም የደረሰበት። ውርደትና ሃፍረት ጭምር እንጂ”

የዴንማርክ ጋዜጣ “ፍየንስ ስቲፍትስቲደንተ” ደግሞ ከሰላሣ ዓመታት ወዲህ እንዲህ ዓይነት ድንቅ የጀርመንቡድን አለመታየቱን ነው ያተተው። “የጀርመን ሕብረ-ብሄር ቅይጥ ቡድን አሁን ታላቁ የዋንጫ ባለቤት የመሆን ዕድል ያለው ቡድን ነው። ከ 1972 የኔትሰርና የቤከንባወር ዘመን በኋላ ይህን የመሰለ የተሻለ ቡድን የታየበት ጊዜ የለም”

የፈረንሣይ ጋዜጣ “ሌ ፓሪዚየን”ም “ጀርመን በሌላ ፕላኔት ላይ! ሲል የቡድኑ አጨዋወት ኳስ አፍቃሪዎችን ሁሉ የሚማርክ እንደሆነ ዘግቧል። ጋዜጣው በማያያዝ እንዳተተው “ጀርመን በዚሁ ከሁለት ዓመታት በፊት በስፓኝ የተከፈተው አዲስ የእግር ኳስ ዘመን መለያ ሆናለች”

የእሥራኤሉ “ሁሪየት” ደግሞ በተለይ አሰልጣኙን ነው ያወደሰው። “የአሂም ሉቭ በእርግጥ እንደ ማራዶና ታላቅ እግር ኳስ ተጫዋች አልነበረም። እንደ አሰልጣኝ ግን በሚገባ አስከንድቶታል” ብሏል።

በዓለም ዙሪያ የሚደረደረው ውዳሤ እንዲህ ቀጥሎ ሳላ በዚህ በጀርመንም በውድድሩ መጀመሪያ ለዘብ ያለ የነበረው የዋንጫ ሕልም አሁን እየጠነከረ በመሄድ ላይ ነው። የብዙዎች አባባል የስፓኝም ዕጣ እንደ እንግሊዝና እንደ አርጄንቲና በሽንፈት መሰናበት ነው የሚል ሆኗል። ተጫዎቾቹም ቢሆኑ የቡድኑ አጥቂ ሚሮስላቭ ክሎዘ እንደሚለው የተለየ አመለካከት የላቸውም።

“ስፓኝ እርግጥ ከእንግሊዝና ከአርጄንቲና የተሻለችዋ ናት። ግን የማትበገር አይደለችም። እነርሱንም ልናሸንፍ እንችላለን። ቡድኑን በሚገባ አጥንተን ድክመቱን በመለየት ይህንኑ በስራ ላይ ለማዋል እንሞክራለን”

እርግጥ የስፓኝ ቡድን አጨዋወት ከሰመረ ለጀርመን አደገኛ ሊሆን እንደሚችል የሚጠራጠር የለም። በቴክኒክ የሰከነ በመሆኑ!

“የስፓኝ ቡድን ለኔ በውድድዱ መጀመሪያ ታላቁ የዋንጫ ባለቤትነት ዕድል ያለው ቡድን ነበር። ተጫዋቾቹ ጥሩ ይጫወታሉ፤ ግሩም የቴክኒክ አቀነባቀርም አላቸው። ሆኖም ግን ከሁለት ዓመታት በፊት በአውሮፓ ዋንጫ ውድድር ወቅት በነበሩበት ጥንካሬ ላይ ያሉ አይመስሉም። እንደማስበው አሁን የአርጄንቲናን ዕጣ አይተዋል። መፍራታቸው አይቀርም። ይህ ደግሞ ለጀርመን ጥሩ ዕድል ነው”

ለማንኛውም የኔዘርላንድ የፍጻሜ ተጋጣሚ ማን እንደሚሆን ማምሻውን እንደርስበታለን።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ