1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ኤኮኖሚ በ 2012 ዓ-ም

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 10 2005

በመገባደድ ላይ ያለው የጎርጎሮሳውያኑ 2012 ቀደም እንዳለው ዓመት ሁሉ የኤውሮ የዕዳ ቀውስ ተጭኖት ነው ያለፈው።

https://p.dw.com/p/174xc
ምስል Reuters

በመገባደድ ላይ ያለው የጎርጎሮሳውያኑ 2012 ቀደም እንዳለው ዓመት ሁሉ የኤውሮ የዕዳ ቀውስ ተጭኖት ነው ያለፈው። በዚሁ የተነሣም የምንዛሪው ተቋም IMF ቀደም ሲል በዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት ላይ አቅርቦት የነበረውን ግምት ዝቅ ማድረግ ሆኖበታል። ተቋሙ የኤውሮ ቀውስ ለዓለም ኤኮኖሚ ታላቁ አደጋ እንደሆነና አዲስ የዕድገት ስብራት እንደሚያሰጋም ነበር ያስጠነቀቀው። የምንዛሪው ተቋም አዲስ ባወጣው ትንበያ የዓለም ኤኮኖሚ ከበፊቱ ባነሰ መጠን በተገባዳጁ 2012 ዓ-ም በ 3,3 ከመቶና በሚቀጥለውም በ 3,6 ከመቶ ሊያድግ እንደሚችል አመልክቷል።

ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም ሌላው ቀርቶ በኢንዱስትሪው ዓለም የዕድገት ሞተር ስትባል በቆየችው በጀርመንም የሚቀጥለውን ዓመት የዕድገት ግምቱን ከ 1,4 ከመቶ ወደ 0,9 ከመቶ ዝቅ አድርጎ ሲያርም በተፋጠነ ዕርምጃ ላይ በሚገኙት ሃገራት በቻይና፣ በሕንድና በብራዚል ላይም ግምቱን መለስ አድርጓል። እርግጥ እነዚህ በተፋጠነ ዕርምጃ ላይ የሚገኙ ሃገራትና አፍሪቃን ጨምሮ በጥቅሉ አዳጊው ዓለም ዓለምአቀፉን የፊናንስ ቀውስ ከበለጸጉት መንግሥታት በተሻለ ሁኔታ በመቋቋም መልሰው ተሥፋ ሰጭ በሆነ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የሚታወቅ ነው።

ይህን ዘግየት ብለን እንመለስበታልን፤ የምንዛሪው ተቋም IMF በዘገባው እንደጠቆመው ለዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት አቆልቋይ ሂደት ዋናው ምክንያት ምናልባትም በገበዮች ላይ የሚታየው ስጋትና አለመተማመን መጨመር ነው። በመሆኑም መዋዕለ-ነዋይን በተመለከተ ሁኔታው በሚቀጥሉት ወራት ምን መልክ እንደሚይዝ መናገሩ አዳጋች እንደሆነ ተጠቅሷል። ሁኔታው እንዲሻሻል ከተፈለገ የበለጸጉት መንግሥታት፤ በተለይም የኤውሮ ምንዛሪ አካባቢና አሜሪካ በፊናንስ ገበዮች ዘንድ ዓመኔታ በሚገባ እንዲሰፍን አጥብቀው መጣራቸውን መቀጠላቸው ግድ ነው።

Rettungsroutine - Wort des Jahres

የኤውሮ የዕዳ ቅውስና የግሪክ ችግር በዚህ ሊገባደድ በተቃረበው ዓመትም ዓቢይ የአጀንዳ ርዕስ ሆኖ እንደሚቀጥል ገና ከጥር ወር ጅምሮ ግልጽ ነበር። ምንም እንኳ የጀርመኑ የፊናንስ ሚኒስትር ጉዳዩን ቀለል አድርገው ለማቅረብ ቢሞክሩም። ሚኒስትሩ በጊዜው ስለ ችግሩ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ከባዱ ቀውስ እየተባለ መወራቱን ጠቃሚ አድርገው አላገኙትም። እናም ሁኔታውን ከማጋነን መቆጠብ እንደሚገባ ነበር ያስጠነቅቃሉ።

«በኤኮኖሚያችን እርጋታ ረገድ ተማኙ ድርጅት ስታንዳርድ-ኤንድ-ፑርስ እንዳመለከተው ሁኔታው እጅግ ጠንካራ በመሆኑ ምንም አደጋ የለብንም። ችግሩ በጋራ ምንዛሪያችን የተነሣ የቀውሱ መጋባት አደጋ ብቻ ነው። ስለዚህም ይህ እንዳይሆን የጋራ ምንዛሪያችንን በማረጋጊያ ሕብረት ማጠናከርና ችግሩ እንዳይዛመት በተሻለ መንገድ መታገል ይኖርብናል»

ግሪክን በተመለከተ በመጋቢት ወር 85 በመቶው ባንኮችንና መድሕን ድርጅቶችን የመሳሰሉ የግል ባለሃብቶች የግሪክን ዕዳ በግማሽ ይቆርጣሉ። እርግጥ ይህ ዕርምጃ ግሪክ መንግሥታዊ ክስረት ላይ ብትወድቅ ለባለሃብቶቹ ሙሉ ክስረት ሊሆን በቻለም ነበር። ግን ይህ ስጋት ለጊዜውም ቢሆን ዕውን ሣይሆን ይቀራል። ግሪክ በበኩሏ ያለዚህ የዕዳ ምሕረት በጊዜው ከለየለት መንግሥታዊ ክስረት ላይ በወደቀች ነበር። የጊዜው የግሪክ የፊናንስ ሚኒስትር ኤቫንጌሎስ ቬኒዜሎስም ታዲያ በዕዳው ምሕረት መቀነስ የተሰማቸውን ዕፎይታ ሳይጠቅሱ አላለፉም።

«ዛሬ ዕዳችንን መቀነስ መቻላችን እጅግ ጠቃሚ ነገር ነው። ከመቶ ሚሊያርድ ዶላር በላይ የሚሆን ሸክማችንን ለማቃለል ችለናል። ይህም ከአጠቃላይ የአገራችን የኤኮኖሚ አቅም አንጻር ግማሹን ያህል መሆኑ ነው። ይህን ለተከታዩ ትውልድ ስንል ማድረግ ነበረብን።»

በታሪክ ታላቁ የሆነው የዕዳ ቅነሣ ዕርምጃ በግሪክና በተቀረው አውሮፓ በሰፊው ሲወደስ ለሁለተኛው የአውሮፓ ሕብረት የ 130 ሚሊያርድ ኤውሮ የዕርዳታ ፓኬት አቅርቦትም ጥርጊያ ይከፍታል። የጀርመኑ የፊናንስ ሚኒስትር ቮልፍጋንግ ሾይብለ ሁኔታውን ተሥፋ ሰጭ አድርገው ነገር የተመለከቱት።

«ከችግሩ ገና ጨርሶ አላመለጥንም። ቢሆንም በጥሩ አቅጣጫ እያመራን ነው። ባለፉት ዓመታት ከግሪክ ጋር ደግመን ደጋግመን የተነጋገርንበትን፤ ያቀድነውን በስራ ላይ በማዋሉ ረገድ ደረጃ በደረጃ ጠቃሚ ዕርምጃ አድርገናል። ይህም ለተጨማሪ ተሥፋ ምክንያት የሚሆን ነው»

ሆኖም ግሪክ ቢቀር ቀስ በቀስ ታገግማለች በሚል በጊዜው የተጣለው ተሥፋ የታሰበውን ፍሬ አይሰጥም። እንዲያውም መንግሥት የወሰዳቸው ጠንካራ የቁጠባ ዕርምጃዎች የአገሪቱ የኤኮኖሚ አቅም በማቆልቆል እንዲቀጥል ሲያደርጉ የዕዳ ምሕረት ቢደረግም ቅሉ በነፍስ ወከፍ የዜጎች የዕዳ ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ ይዘልቃል። ግሪክ በተከታዩ ወራት በርካታ የቁጠባ ዕርምጃዎችን ትውሰድ እንጂ ቀውሱን ማሸነፉ ግን የሚቻላት ነገር አልሆነም።

Griechenland letzter Platz Korruptionsindex
ምስል AP

ግሪክ የዕዳ ቀውሱን መቋቋም ባለመቻሏ ከኤውሮው ምንዛሪ ክልል ትውጣ አትውጣ፤ የአውሮፓውያን ዓቢይ መነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ብዙ ማከራከሩም አልቀረም። ሆኖም ግን የምንዛሬው ሕብረት ተንኮታኩቶ እንዳይወድቅ የተፈጠረው ስጋት ግሪክን አቅፎ መራመዱን ግድ ነው ያደረገው። እንደ ዕውነቱ ከሆነ ግሪክ ቀውሱን የማሸነፍ አቅም ትጣ እንጂ የኤውሮ መንግሥታት የሚጠይቁትን ቁጠባና ለውጥ ገቢር ለማድረግ በሕዝቡ ላይ ያልተጫነ ሸክም የለም።

ለነገሩ ግሪካውያን ለአውሮፓ ሕብረት የቁጠባ ግፊት ተጠያቂ የሚያደርጓቸው የጀርመኗ ቻንስለር ወሮ/አንጌላ ሜርክል እንኳ ለአቴን ጥረት ዕውቅና አልነፈጉም። ሜርክል በቅርቡ በጥቅምት ወር ግሪክን ሲጎበኙ ከጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒስ ሣማራስ ከተነጋገሩ በኋላ አቴን የዕዳ ቀውሱን በመታገሉ በኩል ያደረገችውን ዕርምጃ ከፍ አድርገው ነበር ያወደሱት።

«ዛሬ እዚህ የመጣሁት የግሪክ ሕዝብ በወቅቱ የሚያሳልፈው ጊዜ ምንኛ ከባድ እንደሆነ የሚገባው ጸኑ ግንዛቤ ኖሮን ነው። በዚህ ከባድ ሁኔታ የሚሰቃዩት ብዙዎች ናቸው። ግን የተወሰነው መንገድ መታለፉን ለመናገር እወዳለሁ። ብዙ ተደርጓል፤ የሚቀርም አለ። ይህን ለማሟላት ደግሞ ጀርመንና ግሪክ በጥብቅ እንደሚተባበሩ ለማሳወቅ እፈልጋለሁ»

የሆነው ሆኖ የዕዳው ቀውስ መቼ መፍትሄ ሊያገኝ እንደሚችል እስከዛሬ በትክክል ደፍሮ ለመናገር የሚቃጣ ማንም የለም። ከግሪክ፣ ከፖርቱጋልና ከአየርላንድ ሌላ ተጨማሪ የኤውሮ ዞን ሃገራት ያለማቋረጥ ችግር ሲገጥማቸው የሚታይ ነገር ነው። ከስፓኝና ከኢጣሊያ ባሻገር ፈረንሣይም ቀውስ ላይ እንዳትወድቅ ስጋት እየጠነከረ መምጣቱም አልቀረም። የኤውሮ ዞን የዕዳ ቀውስና አሁንም መቀነስ ያቃተው ግዙፍ የአሜሪካ የበጀት ኪሣራ ተጽዕኖ በአዲሱና ምናልባትም በሚከተለው ዓመት ጭምር ለዓለም ኤኮኖሚ ፈታን እንደሆኑ የሚቀጥሉ ነው የሚመስለው።

ወደ አፍሪቃ ሻገር ስንል በአንጻሩ የዓለም ባንክና ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም የሚተነብዩት የኤኮኖሚው ዕድገት ቀጣይነት እንደሚኖረው ነው። ለዚሁም በተለይ በተፋጠነ ዕርምጃ ላይ የሚገኙት ቻይናንና ሕንድና የመሳሰሉት ሃገራት የጥሬ ዕቃ ፍላጎት መጨመር እንደ ምክንያት ይጠቀሳል። የዓለም ባንክ በበኩሉ የአካባቢው የኤኮኖሚ ዕድገት በዚህ በሚገባደደው ዓመት 2012 5,2 በመቶ፤ እንዲሁም በመጪው 2013 5,6 ከመቶ እንደሚያድግ ነው የሚተነብየው።

ለንጽጽር ያህል ከሣሃራ በስተደቡብ በሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል ያለፈው 2011 ዓ-ም የኤኮኖሚ ዕድገት በአማካይ 4,9 ከመቶ ነበር። የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም ግምትም ከዓለም ባንክ ብዙም የራቀ አይደለም። ተቋሙ የአጠቃላይ ብሄራዊ ምርቱን ዕድገት ለዚህ ዓመት በ 5,4 ከመቶና ለቀጣዩም ዓመት በ 5,3 ከመቶ መጠን አስቀምጦታል።

Symbolbild Afrika Bevölkerungswachstum
ምስል picture alliance/WILDLIFE

በመገባደድ ላይ ባለው 2012 ዓ-ም በአፍሪቃ በኤኮኖሚ ዕድገት ጥንካሬ ቀደምቱ አምሥት ሃገራት ሢየራሌዎን፣ ላይቤሪያ፣ አንጎላ፣ ኢትዮጵያና ሞዛምቢክ መሆናቸውን በዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋምና ሌሎች ጥናቶች የቀረቡ መረጃዎች ያመለክታሉ። የምንዛሪው ተቋም መረጃ እንደሚያመለክተው ሢየራሌዎን በዚህ ዓመት 36 ከመቶ የአጠቃላይ ብሄራዊ ምርት ዕድገት ስታሳይ አሃዙ የቀድሞውን የካታርን ክብረ-ወሰን ሳይቀር ጥሎ ያለፈ ነው።

ለአሠርተ-ዓመታት በእርስበርስ ጦርነት ተወጥራ የኖረችውን የምዕራብ አፍሪቃ አገር ለዚህ ያበቃው ጥሬ ብረትና ሌላም አልማዝን፣ ወርቅንና አሉሚኒየምን የመሰለ የማዕድን ሃብቷ ነው። በእርሻ ልማት ዘርፍም አገሪቱ ለባዮ ነዳጅ ተክል በሚደረግ የውጭ መዋዕለ ነዋይ ተጠቃሚ ሆናለች ነው የሚባለው። ሢየራሌዎን በአዲሱ 2013 ዓ-ም 9,1 ከመቶ ዕድገት እንደምታሳይ የምንዛሪው ተቋም ይተነብያል። ተመሳሳይ ሆኔታ ያሳለፈችው ላይቤሪያም በብረትና በጎማ ሃብት ተጠቃሚ ስትሆን አንጎላ ግዙፍ የነዳጅ ዘይት ሃብት እንዳላት የሚታወቅ ነው።

ሁለቱም ሃገራት በመጨው ዓመት ሰባት በመቶ ገደማ የሚጠጋ ዕድገት እንደሚያሳዩ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ በእርሻ ልማት ዘርፍ ዕድገት ማድረጓ ሲነገር የሞዛምቢክ የዕድገት መሠረት ደግሞ ግዙፍ የማዕድን ከሰልና የተፈጥሮ ጋዝ ሃብት ናቸው። ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም በመጨው ዓመት ለኢትዮጵያ 5,5 ከመቶ፤ እንዲሁም ለሞዛምቢክ የ 7,5 ከመቶ ዕድገት ይተነብያል። እርግጥ በተፈጥሮ ሃብታቸው የሚጠቀሙት ሃገራት በገበዮች የዋጋ ውጣ ውረድ ላይ ጥገኞች በመሆናቸው ሁሌም ስኬት መጠበቁ ያዳግታል።

አፍሪቃ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች ብትሆንም ብዙዎቹ ሃገራት እስካዛሬ ከድህነት መላቀቅ አቅቷቸው የሚገኙት አምራች ኤኮኖሚ በመገንባት ፈንታ አንድ ወጥ ጸጋ ነዳጅ፣ መዳብ፣ ቡና ወይም ኮኮ ብቻ ለገበያ በማቅረብ ላይ ጥገኛ ሆነው በመኖራቸው ነው። ከዚህ መሰሉ ሃብት የሚገኘው ገቢ የዓለም ገበያ ዋጋ በወደቀ ቁጥርና በቂ ምርት ማውጣት ባቃተ ጊዜ በቃላሉ የሚያቆለቁል ይሆናል። ሌላው ቁም ነገር የአፍሪቃ ኤኮኖሚ በዚህም ሆነ በዚያ መጠን አደገ ወሣኙ ጥያቄ የሕዝቡን ድህነት ለማለዘብ ምን ያህል አስተዋጽኦ አድረጓል ነው። በዚህ በኩል በሚገባደደው ዓመትም የተለየ ነገር ተከስቷል ለማለት አይቻልም።

እንግዲህ የዓለም ኤኮኖሚ በኢንዱስትሪ ልማት ከበለጸጉት መንግሥታት ውሱን ዕርምጃ ባሻገር ከአፍሪቃ እስከ ላቲን አሜሪካ፤ እንዲሁም ከላቲን አሜሪካ እስከ እሢያ የዕድገት ቀጣይነት የሚታይበት ሲሆን ወደተረጋጋ ሁኔታ መመለስ መቻሉ በተለይም በኦውሮ ዞን የዕዳ ቀውስ መፍትሄ ማግኘት ላይ ጥገኛ ይሆናል። ከጉዳዩ ውስብስብነት አንጻር አዲሱ ዓመት መፍትሄ የሚታይበት አይመስልም። ጉዞው ምናልባትም ረጅምና አድካሚ ሊሆን የሚችል ነው።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ