1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ኤኮኖሚ በመገባደድ ላይ ባለው 2006 ዓ.ም.

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 18 1999

ዓመት አልፎ ዓመት ሊተካ በተቃረበ ቁጥር ተሸኚውን መለስ ብሎ ማስተዋሉና ለመጪው ዘመን አዲስ ተሥፋ ማቀንቀኑ ያለ፤ ተገቢም ነገር ነው። ከዚህ የሚገኘው አጠቃላይ ግንዛቤ ለወደፊቱ ዕድገት ጠቃሚነት አለው። ተሰናባቹ 2006 በዓለም ኤኮኖሚ ሂደት ረገድ እርግጥ ቀደም ካለው እምብዛም የተለየ አልነበረም። ቢሆንም በተወሰነ ደረጃ ዕርምጃ መታየቱ አልቀረም፤ መሥፍን መኮንን!

https://p.dw.com/p/E0dH
ዓለም በ 2006 ዓ.ም.
ዓለም በ 2006 ዓ.ም.

በአጠቃላይ ግን ዓለምአቀፉን የኤኮኖሚ ስርዓት ፍትሃዊ በማድረጉ ረገድ መሠረታዊ ለውጥ ቀርቶ፤ ለዚሁ አስፈላጊው ጥርጊያ እንኳ የተከፈተበት፤ ያን ያህል የተሥፋ ጭላንጭል የታየበት ነበር ለማለት ያዳግታል። ምዕራቡ ዓለም ዕድገቱን አንቆ ከቆየው የልማት ዕጦት በከፊልም ቢሆን ሲያገግም መታየቱና በታዳጊ አገሮች የሚሌኒየሙን የልማት ግብ ዕውን ለማድረግ በተያዘው ጥረት ዕርምጃው አዝጋሚ ሆኖ መቀጠሉ፤ እንዲሁም አፍሪቃ በምጣኔ-ሐብት ዕድገትና በውዝግቦች መካከል፤ የቻይና አድጎ-ማሳደግ የመስፋፋት ፖሊሲና የምዕራቡ ዓለም ስጋት፤ እነዚህ በዓመቱ በዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ መድረክ ላይ ጎልተው ከታዩት ጉዳዮች የተወሰኑት ነበሩ።

በአፍሪቃ፤ በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ፤ ዓመቱ የሚገባደደው አሁንም ማብቂያው የማይታወቅ፤ ምስቅልቅልና ስጋት የጋረደው ሆነ ነው። የአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም የልማት ጠንቅ ጦርነት፤ መፈናቀል፤ ስደት፤ አሁንም ስደት፤ ማለቂያ ያጣ መዘዝ ሆኖ ቀጥሏል። ዓመቱ የእሢያ ኤኮኖሚ በተለመደው ፈጣንና ጠንካራ ሁኔታ ዕድገቱን የቀጠለበት፤ ምዕራቡ ዓለምም፤ ቢቀር አውሮፓ እንደገና እመርታ ማሣየት የያዘችበት ሆኖ ነው ያለፈው። በአሜሪካ በምጣኔው ሐብት ይዞታ ረገድ የታየው የማገገም ሁኔታ በዓመቱ ማብቂያ መቃረቢያ ላይ እንደገና ደብዘዝ ሲል በአውሮፓ በዚሁ ጊዜ ለቀጣይ ዕድገት ተሥፋ የሚሰጥ አዝማሚያ ነው የተከሰተው።
ጀርመንን በመሳሰሉት የአውሮፓ ሕብረት አገሮች ከምጣኔው ሐብት ዕርምጃ አንጻር የጥም ጊዜያት የነበሩት ዓመታት በወቅቱ እያለፉ ነው። የጀርመን ኤኮኖሚ በአውሮፓ ዓመቱ ሲጀምር ከነበረበት ከመጨረሻ ደረጃው ተነስቶ በዚህ መልክ ቀደምት ይሆናል ብለው የጠበቁት ብዙዎች አልነበሩም። እርግጥ በአሕጽሮት OECD በመባል የሚጠራው የአውሮፓ የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት ባልደረባ ሃይኖ ፎን ማየር እንደሚጠቁሙት የወቅቱ ስኬት አመዝኖ የሚገኘው በውጩ ንግድ ላይ ነው።

“አንዱ እግር፤ ማለት የውጩ ንግድ ጠንካራና የኤኮኖሚውን ግፊት ሊቋቋም የሚችል ነው። ሌላው እግር፤ የውስጡ የገበያ ፍላጎት ወይም ፍጆት ግን ገና ከድካሙ አልተላቀቀም። ሆኖም የዕድገቱ ጤናማ ዝንባሌ ለውጡ ፍሬ መስጠት መጀመሩን የሚያሣይ ነው። እንዲህም ሆኖ ግን ጀርመን በምርኩዝ መሄዷን ትቀጥላለች” ባይ ናቸው። ቢሆንም አሁን በዓመቱ መገባደጃ ወቅት የጀርመን ሕዝብ በምርት ፍጆቱ ረገድ ምርኩዙን አሽቀንጥሮ የጣለ ነው የሚመስለው። ለሕዝቡ የገበያ ፍጆት መጨመር እርግጥ የመግዛት አቅሙ ማደጉ ሣይሆን ሌላ ምክንያት አለው።

ፌደራሉ ም/ቤት በአዲሱ ዓመት የሚጸና የምርት ቀረጥ ጭማሪ ለማድረግ መወሰኑ ፍጆተኛው ዋጋ ከመወደዱ በፊት አሮጌው ዘመን ሳይገባደድ የተቻለውን ሁሉ ቀድሞ ለመገብየት መነሣቱ ነው ምክንያቱ። እርግጥ በጀርመን ከአምሥት ሚሊዮን በላይ ዘልቆ የነበረው የሥራ አጦች ቁጥር ለመጀመሪያ ጊዜ ከአራት ሚሊዮን በታች ሊወርድ በቅቷል። የአገሪቱ ኩባንያዎች በተለይ በውጩ ንግድ እየካበቱ፤ ገንዘባቸውን ከመቼውም በላይ በሥራ ላይ እያዋሉ ነው።

በሌላ በኩልም መንግሥት በማሕበራዊው ዋስትና ዘርፍ ባሰፈነናቸው ለውጦችና ጠንካራ የቁጠባ መርሁ ተሟጦ የነበረ የበጀት ካዝናውን መልሶ መሙላት ይዟል። በግብር ስብሰባው ካዝናቸው በመሙላቱ ደስታ ወይም እፎይታ የተሰማቸው የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ፔር ሽታይንብሩክ እንደቅርብ የሥልጣን ቀደምቶቻቸው እንቅልፍ የሚያጡበት ጊዜ ማለፍ የያዘ ነው የሚመስለው። ሚኒስትሩ እርካታቸውን ሲገልጹ፤ “የገንዘብ መኖር የሚያሳድረው ስሜት ገንዘብ የማጣትን ክፉ ስሜት ያህል ጠንካራ አይደለም የሚል አነጋገር አለ። በመሆኑም በወቅቱ ሁኔታው ከጠበቅኩት በላይ እጅግ ጥሩ በሆነ መልክ እየተራመደ ሲሄድ በማየቴ ደሥታዬ ወደር የለውም” ብለዋል።

እርግጥ በወቅቱ በጀርመንም ሆነ በጠቅላላው በአውሮፓ የሚታየው የማገገም አዝማሚያ የሥራ አጡን ችግር ለዘለቄታው ሊፈታ መብቃቱ ገና ብዙ ያጠያይቃል። ጉልህ ነገር ቢኖር የኢንዱስትሪውን ዘርፍ መካበት ያህል የሕዝቡ የኑሮ ይዞታ በተጣጣመ ሁኔታ ሲያድግ አለመታየቱ ነው። የኢንዱስትሪውን መካበት ካነሣን በኤነርጂ ዋጋ መናር ሳቢያ ታላላቅ ኩባንያዎች በዓመቱ ያግበሰበሱት ትርፍ መጠን እንደገና ሞራላዊ ገደብን ያለፈ ነበር።
የነዳጅ ዘይት ዋጋ አሁን በዓመቱ መገባደጃ ላይ ጥቂት ለዘብ ቢልም በበርሚል እስከ 78 ዶላር መተኮሱ ለተጠቃሚው ከባድ ፈተና ነበር የሆነው፤ ሆኖም እንደቀጠለ ነው። በዓመቱ መጀመሪያ በወርሃ ጥር የሩሢያ መንግሥታዊ የነዳጅ ዘይትና የጋዝ ኩባንያ ጋዝፕሮም በዋጋ ውዝግብ ሳቢያ በኡክራኒያ ላይ ቧምቧውን መዝጋቱ አውሮፓን ብርቱ የኤነርጂ ጥገኝነት ፈተና ላይ የጣለ ነበር። የኤነርጂው ውድነት ተጽዕኖ በዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት ላይ በአዲሱም ዘመን ጸንቶ ይቀጥላል።

አፍሪቃ በ 2006 ዓ.ም. ባለፉት አሠርተ-ዓመታት የዕድገት አዝማሚያ በመቀጠል ቀና እያለች ነው፤ በርከት ያሉ የክፍለ-ዓለሚቱ አገሮች በአማካይ አምሥት በመቶ ዕድገት አሣይተዋል ሲል የዓለም ባንክ በቅርቡ አመልክቶ ነበር። በጎ አስተዳደር በተወሰኑ አገሮች መቆናጠጥ መያዙ፤ የእርስበርስ ጦርነቶች እየተወገዱ መሄዳቸውም ለዕድገቱ ዓበይት ምክንያቶች መሆናቸው መጠቀሱ አልቀረም። እርግጥ ይህን የጠቃቀሰው የዓለም ባንክ በዓመቱ የአፍሪቃ የልማት ዘገባው አሁንም ከግማሽ በላይ የሚሆነው የአፍሪቃ ሕዝብ ከድህነት ዝቅተኛ መስፈርት በታች እንደሚገኝ ሳያመላክት አላለፈም። ቁልፉም ያለው እዚህ ላይ ነው።

በአፍሪቃ በጎ አስተዳደርን በማስፈኑ ረገድ በተገባዳጁ ዓመት እዚህ ወይም እዚያ ዕርምጃ ታይቶ ነበር ብሎ ለማስታወስ በጣሙን ያድግታል። ሙስና ባለበት ተንሰራፍቶ መቀጠሉን፤ ማሕበራዊ ፍትህ መጓደሉንና መብት ረገጣው ያለፈ ታሪክ አልሆን ማለቱን ለማሰብ ግን ጊዜና ድካም አያስፈልግም። ያለፉት ጦርነቶች በአዳዲስ መተካታቸው ወይም መልሶ ለማገርሸት የሚቃጣቸው መሆኑንም እንዲሁ!

አፍሪቃ ውስጥ ባለፈው ዓመት ታየ ለተባለው ጠንካራ ዕድገት ከውስጣዊው ዕርምጃ ወይም የሕብረተሰብ መዋቅራዊ ተሃድሶ ይልቅ ጊዜያዊ ሁኔታዎች ድርሻ ነበራቸው። ሱዳንን በመሳሰሉት አገሮች የታየው ከፍተኛ ዕድገት ከነዳጅ ሐብት ጋር የተያያዘ ሲሆን ቀደም ያለው ዓመት የዕዳ ስረዛ ጊዜያዊ አስተዋጽኦ ማድረጉ አልቀረም። በተረፈ ጥቂቶች ይበልጥ እየካበቱ፤ ብዙሃኑ ይበልጥ እየደኸዩ መሄዳቸው መቀጠሉ ነው ሃቁ። በዓለም ባንክ ዘገባ ለአፍሪቃ የአሠርተ-ዓመት የዕድገት ዕርምጃ የተሰጠው አንዱ ምክንያት፤ የእርስበርስ ጦርነቶች እየተወገዱ መሄዳቸው ጽናት እንደሌለው የሰሞኑ ሁኔታ በሚገባ እያሣየ ነው።

የደቡብ ሱዳን፤ የሢየራሌዎንና የላይቤሪያ የእርስበርስ ጦርነቶች ቢያከትሙም የዳርፉር ችግር ማሰሪያ አላገኘም፤ ከኡጋንዳ እስከ ቻድ፤ አሁን ደግሞ በአፍሪቃ ቀንድ ላይ ተተኪው ቀውስ ብዙዎች አገሮችን ማጣቀሱን ጀምሯል። የዓለም ባንክ ዕድገት አሣይተዋል ሲል ከዘረዘራቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን አሁን ምናልባትም መውጫው በሚከብድ የሶማሊያ ጦርነት ውስጥ መነከሯ በልማት ጥረት መቀጠሉን የሚያከብድ ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል ከዚህ አዙሪት ሳይላቀቅ የተባበሩት መንግሥታትን የሚሌኒየም የልማት ዕቅድ በተጣለው የጊዜ ገደብ በሙሉ ቀርቶ በከፊል እንኳ ማሟላት መቻሉ አጠያያቂ ሆኖ ይቀጥላል።

እርግጥ አፍሪቃ ከተጣለው የልማት ግብ እንዳትደርስ ከራሷ የገዢዎች ብልሹ አስተዳደር ሌላ በዓለም ንግድ አኳያ ያለው ፍትህ-ዓልባነትም አንዱ ዓቢይ ችግር ነው። ማለቂያ ያጣውን የዶሃ የዓለም ንግድ ድርድር ዙር ባለፈው ዓመትም ከግቡ በማድረስ የታዳጊ አገሮችን የገበያ ተሳትፎ ለማሻሻል የተጣለው ተሥፋ ዕውን ሣይሆን ቀርቷል። ለዚህም ምክንያቱ በአመዛኙ ምዕራቡ ዓለም የእርሻ ድጎማ ፖሊሲውን በሚገባ በመለወጥ ጭኖ ካቆየው ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ስርዓቱ ስንብት ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆኑ ነው።

2006 ዓ.ም. ቻይና በአፍሪቃ የያዘችው የመስፋፋት ፖሊሲ ታሪካዊ ግምት የተሰጠው ደረጃ ደርሶ የታየበትም ነበር። በአፍሪቃ የተፈጥሮ ሃብት ላይ ያተኮረችው ሕዝባዊት ቻይና ቤይጂንግ ላይ ታሪካዊ ግምት የተሰጠው የሳይኖ-አፍሪቃ የመሪዎች ጉባዔ በማስተናገድ ትስስሩን ለማስፋፋት ቆርጣ እንደተነሣች አሣይታለች። ቻይና 48 የአፍሪቃ መሪዎችን በአንድ ላይ ለማሰባሰብ በቅታለች። ቤይጂንግ ከበለጸጉት መንግሥታት ለመስተካከል በያዘችው የተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት የነዳጅ ዘይትና ሌላም የተፈጥሮ ሃብት ጥሟ ከፍተኛ ነው። ለዚህ ደግሞ አድጎ ማሳደግ በሚል ፖሊሲ ጥቅሟን ከአፍሪቃ ማስተሳሰሩን ነው የመረጠችው።

ያለፈው ዓመት ቤይጂንግ ከተለያዩ የአፍሪቃ አገሮች ጋር በርካታ የወዳጅነትና የትብብር ውሎች የተፈራረመችበት ነበር። ከነዳጅ ዘይት ማመንጨት እስከ አጠቃላይ መዋቅራዊ ግንባታ፤ ዛሬ የቻይና ሙያተኞች በተግባር ያልተሰማሩበት የአፍሪቃ አገር አይገኝም። በቤይጂንጉ ጉባዔ የሁለቱን ወገን የንግድ ልውውጥ በእጥፍ ለማሳደግ መወሰኑም የሚታወስ ነው። ቻይና በሰው አገር ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት በሚል ፖሊሲዋ ለዴሞክራሲም ሆነ ለሰብዓዊ መብት ከበሬታ ቅድመ-ግዴታ የማታስቀምጥ መሆኗና የቀድሞ ቅኝ ገዥ አለመሆኗ በአፍሪቃ አምባገነኖች ዘንድ ከምዕራቡ ዓለም ይልቅ ተመራጭ ሳያደርጋት አልቀረም፤ ባለፈው ዓመት ይህ በያጋጣሚው ጎልቶ የታየ ሃቅ ነበር።
የቻይና በአፍሪቃ በሰፊው መቆናጠጥ በዘልማድ አፍሪቃን በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ የቆየውን ምዕራቡን ዓለም ማብከንከኑ በተለይ እየተገባደደ ባለው ዓመት ከመቼውም ጎልቶ ነው የታየው። ምዕራቡ ዓለም የቻይና ፉክክር በቀላሉ የተዋጠለት አይመስልም። የ 2006 ዓ.ም. የዓለም ኤኮኖሚ ሂደት በጥቂቱ ይህን የመሰለ ነበር።