1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ሠራተኞች ቀንና ኢትዮጵያ

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 23 2009

ኢትዮጵያን እስካለፈዉ ጥቅምት ድረስ ግራ-ቀኝ ሲያላጋት የቆየዉ የአደባባይ ተቃዉሞና ግጭት በሰወስት ወራት ዉስጥ ብቻ ከ660 በላይ ሰዎች መገደላቸዉን የሐገሪቱ መንግሥት ራሱ አምኗል።ፋብሪካዎች ጋይተዋል፤ኢንዱስትሪዎች ሥራ ለማቆም ተገድደዋል።ለዓለም ሠላም መታገል የሚጠበቅበት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማሕበር ሐገሩን ሥላበጠዉ ተቃዉሞ ግጭቱ ምን አለ?

https://p.dw.com/p/2cCCb
Rallies on May Day in Moskau
ምስል picture alliance/dpa/A.Korotayev

የዓለም ሠራተኞች ቀንና ኢትዮጵያ

በቀዝቃዛዉ ጦርነት ዘመን ከሠራተኛ ትግል መታሰቢያነቱ በላይ እንደ ካፒታሊስት-ሶሻሊስቱ ሽኩቻ ፍጥጫ አካልነቱ፤ በየዓመቱ፤ በየአደባባዩ ይፎከር-ይዘመር፤ ይቀነቀን-ይደሰኮርበት ነበር።ሜይ ዴይ።የዓለም ሠራተኞች ቀን።ኢትዮጵያም በአብዮት በምትናጥበት በዚያ ዘመን አደባባዮችዋ በቀይ ቀለም የሚቅላሉበት፤ «ጠላቶች» የሚወገዙ-የሠራተኛዉ አምባገነናዊነት የሚወደስበት፤ አልፎ ተርፎ የጦር ጡንቻ የሚሰጣበት ዕለት ነበር።የዓለም ወዛደሮች ቀን።ዛሬም ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ ሐገራት ብሔራዊ በዓል ነዉ።በዓሉ መነሻ፤ የኢትዮጵያ ሠራተኞች አደረጃጀት ማጣቀሻ፤ የሠራተኞች መብት ነፃነት ይዞታ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

                              

ዛሬም የሠራተኞች ትግል የደረሰበት ደረጃ፤ ያጋጠመዉ እንቅፋት፤ የማሕበራት ድክመት ጥንካሬ በየሐገሩ ይገመገማል።ሠራተኞች መብታቸዉ እንዲከበር በመጠየቅ በየአደባባዩ ይሰለፋሉ።እንደ ድሮዉ የድሮዉን የሚዘምሩም አሉ።

                            

«ተነሱ እናንት የራብ እስረኞች-----» ኢንተርናሲዮናል።ሠራተኞች እና ለሰራተኞች መብት የሚታገሉ ወገኖች ትግላቸዉን የሚያስቡ፤ ኃይላቸዉን የሚያሳዩ፤ጥያቄያቸዉን በጋራ የሚያቀርቡበት የጋራ ዕለት ማፈላለግ የጀመሩት ከ19ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ማብቂያ ጀምሮ ነበር።

Frankreich 1. Mai Ausschreitungen in Paris
ምስል Reuters/G. Fuentes

ያዘመን አዉሮጳ እና ሰሜን አሜሪካ ላይ የሠራተኞች የሥራ-ሰዓት በቀን ከስምት ሰዓት እንዳይበልጥ የሚደረገዉ ትግል የተጠናከረበት፤ የሠራተኞች ማሕበራት የተበራከቱበት፤ሶሻሊስታዊና ኮሚንስታዊ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ የተስፋፋበት ነበር።

የቺካጎ፤ ዩናይትድ ስቴትስ ሠራተኞች ግንቦት 4፤1886 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሐይማርክት አደባባይ ያደረጉት ሠልፍም በየስፍራዉ እንደነበረዉ ሁሉ መብታቸዉ እንዲከበር ለመጠየቅ ነበር።ፖሊስ ከዚያ ቀን በፊት ጓደኞቹን የገደሉበት አንድ ሠልፈኛ የጓደኞቹን ደም ለመበቀል ፖሊሶች ላይ ቦምብ ወረወረ።ከፖሊስም፤ ከሰላማዊ ሰዉም አስራ-አንድ ሰዉ ሞተ።ብዙ ቆሰሉ።

 

ቦምቧ ለአሜሪካ ገዢዎች፤አሰሪዎችና ባለሟሎቻቸዉ የሠራተኛዉን ሠልፍ ለመጨፍለቅ ጥሩ አጋጣሚ ሆነች።ሠልፈኛዉን የበተነዉ የፀጥታ ኃይሎች ርምጃ ባንፃሩ  የሰራተኞች መብትን ለማስከበር፤ የሶሻሊስትና የኮሚንስት ፖለቲካን በሕዝብ ዘንድ ለማስረፅ፤  የዓለም ሰራተኞች ትግል የሚታሰብበት ዕለትን ለመወሰንም ሰበብ ሆነች።

የቺካጎ ሠራተኞች ትግልና መስዋዕትነት ታላቅ ክብር የተሰጠዉ እንዲዘከር የተወሰነዉም ከዩናያትድ ስቴትስ ይልቅ አዉሮጳ መሆኑ ግን የአትላቲክ ባሕር የሚለያያቸዉ የካፒታሊስታዊ ሥርዓት አራማጆች ለሠራተኛዉ መደብ ያላቸዉ ክብር  ዛሬም ድረስ የተለያየ መሆኑን መስካሪ ነዉ።በ1889 ፓሪስ ፈረንሳይ የተሰየመዉ እና ሁለተኛዉ አለም አቀፋዊ የተሰኘዉ የሶሻሊስቶች  እና የሠራተኛ መብት ተሟጋቾች ሕብረት ጉባኤ ግንቦት አንድ የሠራተኞች ትግል መታሰቢያ ዕለት እንዲሆን ወሰነ።

Deutschland 1. Mai in Stuttgart Demonstration
ምስል picture-alliance/dpa/C. Schmidt

                                     

በዩናይትድ ስቴትስ ሠራተኞች ላይ በተፈፀመዉ ግፍ ሰበብ፤ ግፉ እንዲፈፀም ምክንያት የነበሩት አመፆች በተቀጣጠሉበት ዕለት ግንቦት አንድ  ዓለም የሚያከብረዉን ዕለት ዩናይትድ ስቴትስ ካናዳ አያከብሩትም።በሁለቱ ሐገራት የሠራተኞ ቀን የሚከበረዉ መስከረም ወር የመጀመሪያዉ ሰኞ ነዉ።ኢትዮጵያ በዓሉን የምታከብረዉ እንደ አብዛኛዉ ዓለም ግንቦት አንድ ነዉ።ዛሬ።ግን ዘግይታ ነዉ የጀመረችዉ።

                          

አቶ አስፋዉ አበበ የሆቴሎችና ቱሪዝም ኢንዱትሪ ፌደሬሽን ፕሬዝደንት ናቸዉ።በዓሉ ዛሬ አዲስ አበባ ዉስጥ ተከብሮ ነዉ የዋለዉ።በ1904 አምስተርዳም ኔዘርላንድስ የተሰየመዉ ዓለም አቀፍ የሶሻሊስቶች ጉባኤ ባሳለፈዉ ዉሳኔ መሠረት በመላዉ ዓለም የሚገኙ የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲዎች እና የሠራተኛ ማሕበራት ዕለቱን በደማቅ የአደባባይ ሠልፍ ማክበር አለባቸዉ።

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማሕበራት መሪዎች እንደሚሉት ግን በጎዳና ሠልፍ አያምኑም።አቶ አስፋዉ አበበ። አርባ ሁለተኛ ዓመቱን የያዘዉ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማሕበር እነ አበራ ገሙ፤ እነ ዳዊ ኢብራሒም በሚባሉ መሪዎቹ ዘመን፤ ብዙዎች እንደሚሉት፤  ሥሙ የገነነ፤ ከሠራተኛዉ አልፎ የመላዉ ኢትዮጵያዊ መብት እና ፖለቲካዊ ነፃነት እንዲከበር የሚታገል ነበር።ዛሬ ግን ያ ስም-ዝና ነበር የሚባል ይመስላል። ኢትዮጵያ ዉስጥ ወደ ሰወስት ሚሊዮን የሚጠጋ ሠራተኛ እንዳለ ይገመታል።በማሕበራት የተደራጀዉ ግን ከዘጠኝ መቶ ሺሕ አይበልጥም።

ለትምሕርት በርሊን የሚገኙት የሸራተን አዲስ የሠራተኛ ማሕበር ሊቀመንበር እና የኢትዮጵያ ሠራተኞች ኮንፌደሬሽን የምክር ቤት አባል አቶ ዳዊት ሳሙኤል እንደሚሉት ሠራተኛዉ በቅጡ ያልተደራጀዉ በሁለት ምክንያት ነዉ።

                           

የቀድሞ የሠራተኛ ማሕበራት መሪዎች እና የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ግን መሠረታዊዉ ምክንያት ሌላ ነዉ።የመንግሥት ተፅዕኖ።የየማሕበራቱ መሪዎች ራሳቸዉ የገዢዉ መደብ አባላት ናቸዉ ባዮችም አሉ። የሆቴሎችና ቱሪዝም ኢንዱትሪ ፌደሬሽን ፕሬዝደንት አቶ አስፋዉ አበበ ግን በጭራሽ ይላሉ። ዳዊት ሳሙኤል ደግሞ አይ-አዎ ነዉ መስላቸዉ።

                           

በተደጋጋሚ እንደሚባለዉ የሠራተኛ ማሕበራት የየማሕበሩን አባላት ጥቅም ከማስከበር በተጨማሪ ማሕበሩ ያለበት ሐገር  ፖለቲካዊ፤ ምጣኔ ሐብታዊ ይሁን ማሕበራዊ ጉዳዮች በቀጥታ ይመለከተዋል።የመንግሥትን መርሕ በመደገፍ ወይም በቃወም አቋም ይይዛል።ተቃዉሞ ድጋፋን ይገልፃልም።የ1904ቱ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ዉሳኔ እንደሚያመለክተዉ ደግሞ ሠራተኛ ማሕበራት ከአባሎቻቸዉ፤ ከየሕዝባቸዉና ሐገራቸዉም አልፈዉ ለዓለም ሠላም መከበር ይጥራሉ፤ ይታገላሉም።በዘመናችን ዓለም ሠላም ናት ማለት ያሳስታል።የአፍሪቃ ቀንድ ደግሞ ከደቡብ ሱዳን እስከ ሶማሊያ በግጭት ጦርነት ትታበጣለች።

Deutschland 1. Mai in Hamburg DGB-Demonstration
ምስል picture-alliance/dpa/M. Scholz

ኢትዮጵያን እስካለፈዉ ጥቅምት ድረስ ግራ-ቀኝ ሲያላጋት የቆየዉ የአደባባይ ተቃዉሞና ግጭት በሰወስት ወራት ዉስጥ ብቻ ከ660 በላይ ሰዎች መገደላቸዉን የሐገሪቱ መንግሥት ራሱ አምኗል።ፋብሪካዎች ጋይተዋል፤ኢንዱስትሪዎች ሥራ ለማቆም ተገድደዋል።ለዓለም ሠላም መታገል የሚጠበቅበት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማሕበር ሐገሩን ሥላበጠዉ ተቃዉሞ ግጭቱ ምን አለ።ምንስ አደረገ? አቶ አስፋዉ አበበ

                            

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ኮንፌደሬሽንን የመሪነት ሥልጣን ለመያዝ በ1980ዎቹ ማብቂያ ከፍተኛ ዉዝግብ፤ የፍርድ ቤት እሰጥ አገባም ነበር።ሥልጣኑን ይዞ የነበረዉ በነ አቶ ዳዊ ኢብራሒም የሚመራዉ ቡድን ተሸነፈ ተባለ።አባላቱ ተሰደዱም።

                                     

የአሳዳጆቹ ሥራ ከተሰደዱት ምግባር ቀንሷል። ምክንያቱ ብዙ ነዉ።ዛሬ እና ከዛሬ በኋላስ?ተስፋ ማድረግ ጥሩ ነዉ።ባይኖርም።ነጋሽ መሐመድ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ