1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለምአቀፉ ንግድ የሚዛን ዝቤት

ረቡዕ፣ መጋቢት 8 2002

በውጭ ንግድ ረገድ የአንዳንድ አገሮች ማየልና የሌሎች መዳከም በዘርፉ ሚዛን እንዳያዛባ ሲያሰጋ፤ በወቅቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ባይሆንም ሲያከራክር ነው የሚገኘው። ፈረንሣይ ለምሳሌ ጀርመንን ትወቅሣለች።

https://p.dw.com/p/MVAw
ምስል DW-TV

ለግንዛቤ ያህል በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ለኑሮ ከሚያስፈልገው ወጪ ይልቅ ገቢው ከፍ ብሎ ቢገኝ ጥሩ የበጀት አያያዝ ሰፍኗል ነው የሚባለው። በመንግሥት ደረጃ ግን ትርፉ አይሉ መቀጠሉ ሁሌ የሚመረጥ ላይሆን ይችላል። ይህ በተለይም በኤኮኖሚ ቀውሶች ወቅት በዙ ወደ ውጭ በማይነግዱ ወይም የበጀት ኪሣራ ባለባቸው አገሮች፤ ማለት ወደ ውጭ ከሚሸጡት ይልቅ ብዙ በሚያስገቡት አገሮች ዘንድ ቁጣን የሚቀሰቅስ ነው። ፈረንሣይ ለምሳሌ የጀርመንን የውጭ ንግድ ጥንካሬ ደከም ያሉትን የኤውሮ-አገሮች የሚጎዳ ነው ስትል ሰሞኑን ተችታለች። እና ሁኔታው እንዴት ሊጣጣም ይችላል?

የውጭ ንግዱ ድርሻ መጠናከር በዓለም ላይ በተለይ ይሄው ለሰመረላቸው አገሮች የብልጽግና ወይም የዕድገት መንኮራኩር ሆኖ ቆይቷል። በሌላ በኩል ለምሳሌ ከቻይና በገፍ ምርትን ማስገባቱን የመረጠችው አሜሪካ የኋላ ኋላ ገፍ ዕዳ ተሸካሚ ነው የሆነችው። ቻይና በአንጻሩ ወደ አሜሪካ የምታደርገውን የውጭ ንግዷን በታታሪነት በመቀጠልና እንዲያም ሲል የአሜሪካን የመንግሥት ዕዳ በመግዛትና ዕዳውን በማስተዳደር ሚዛኑ እንዲለወጥ አድርጋለች። በሌላ አነጋገር ሁኔታው ቻይናን በዓለም ላይ ታላቅ አበዳሪ አሜሪካን ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ባለ ዕዳ አድርጓል ማለት ነው።

ይህ አካሄድ በረጅም ጊዜ ጠቃሚ እንደማይሆን ገና ቀድሞ ግልጽ ነገር ነበር። በርካታ የምጣኔ-ሐብት ጠበብት ይሄው ግዙፍ የአሜሪካ የንግድና የበጀት ኪሣራ ከባድ ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ቀውስን ሊያስከትል እንደሚችል መገመታቸው አልቀረም። እርግጥ ይህ እንደሚታወቀው ዛሬ ዓለምን ላዳረሰው ቀውስ ተቀዳሚው መንስዔ አልሆነም። ግን የብራስልሱ ተመራማሪ ያኮብ-ፎን-ቫይትሴከር እንደሚሉት መነሻው የፊናንሱ መስክ ይሁን እንጂ ይህም ተጽዕኖ የለውም ሊባል አይችልም።

“የወቅቱ ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ቀውስ መንስዔ ይበልጡን የፊናንሱ ዘርፍና በከፊልም የአሜሪካ የቤት ባለቤቶች ኪሣራ ውጤት ነው። ግን በተመሳሳይ ጊዜ የውጭ ንግድ ሚዛን ያልተስተካከለበት ዓለም ለቀውስና እንደ ዶሚኖ-ድንጋዮች ሁኔታ ተከታትሎ ለመውደቅ የተጋለጠ መሆኑም ግልጽ ነው”

ይህን መሰሉ የዶሚኖ ባህርይ ያለው ተጽዕኖ ኤኮኖሚዋ በውጭ ንግድ ላይ በሰፊው ጥገኛ በሆነው በጀርመን ላይም ከባድ ሁኔታን ነበር ያስከተለው። ብሄራዊ የኤኮኖሚ አቅሟ ባለፈው 2009 ዓ.ም. ከሌሎች በኢንዱስትሪ ልማት ከበለጸጉ አገሮች አየል ባለ ሁኔታ አምሥት ከመቶ ማቆልቆሉ አይዘነጋም። ሆኖም ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ በዓለም ላይ አዲሷ የውጭ ንግድ ቀደምት ለመሆን የበቃችው ቻይናና ወደ ሁለተኛው ቦታ ሸርተት ያለችው ጀርመን ምንም እንኳ ምክንያቶቻቸው የተለያዩ ቢሆኑም አብዛኛውን የተትረፈረፈ ምርት ማውጣታቸው አልቀረም። ቫይትሴከር እንደሚሉት በተለይ ለቻይና አመራር የውጩ ንግድ ቀደምት የሆነበት መሠረታዊ ጉዳይ አለ።

“ቻይና ዛሬም ሰፊ የገጠር ነዋሪ ሕዝብ አላት። እና ከዚሁ ገና በታሙን ድሃ የሆነ ሕዝብ አብዛኛውንም በፍጥነት ከአምራቹ ዘርፍ ለማቀላቀል ትፈልጋለች። እርግጥ ታዲያ የምርቱም ተግባር በውጭ ንግድ ላይ ያተኮረ መሆን አለበት”

እርግጥ ቻይና በቂ የውጭ ምንዛሪ ዋስትና ጠፍቶ ታላቅ ቀውስ እንዳይከተል ስጋት ሳይኖራት ቀርቶ አይደለም። ቻይናውያን በሌላ በኩል በቂ ማሕበራዊ ዋስትና ባለመኖሩ ቆጣቢዎችም ናቸው። አይምሰል እንጂ በዚህ በጀርመንም ለምሳሌ የሰሜን ጀርመን ክፍለ-ሐገር ባንክ ዋና የምጣኔ-ሐብት ጉዳይ ሃላፊ ቶርስተን ቪንደልስ እንደሚያስረዱት ለነገሩ የሰከነ ማሕበራዊ ዋስትና ቢኖርም ሕዝቡ የበዛ የመቀናጣት የኑሮ ዘይቤ አይታይበትም።

“ጀርመናውያን በወቅቱ ካላቸው አቅም በታች ነው የሚኖሩት። ይህ ደግሞ እንደሚባለው ለዓመታት ሁኔታው ከሚፈቅደው በላይ ከመኖራችንና አሁን መቀነስ ከያዝነው መንግሥታዊ ዕዳ አንጻር፤ ይህም ዛሬም ከአቅም በላይ መኖርን የሚያመለክት ነው፤ በጣም ሳያስደንቅ አይቀርም። ግን አገሪቱ ካላት ከፍተኛ የውጭ ንግድ ድርሻ ወይም ትርፍ አንጻር ሲታይ ፍጆታችን አነስተኛ ነው። ስለዚህም ፍጆትና የኑሮ ማጣጣም ዘይቤያችን ከምንችለው በታች ነው ሊባል ይችላል”
የባንኩ ባለሙያ ቶርስተን ቪንደልስ የአገራቸውን ሕዝብ የሚመክሩት በብዙ ፍጆት ኑሮን እንዲያጣጥም ነው። ግን ይህ ከተጨባጩ ሁኔታ አንጻር ቀላል ሆኖ አይገኝም። የሰርቶ-አደሩ ተጨባጭ ደሞዝ ለዓመታት ከፍ ሳይል ባለበት ነው የቀጠለው። የሙያ ማሕበራቱ ለደሞዝ ጭማሪ በሚያደርጉት ድርድር ፍላጎታቸውን ማለዘባቸው ወይም ቁጥብነት ማሳየታቸው በዚሁ የተነሣ ምንም እንኳ የጀርመንን ምርቶች ለገበያ ፉክክር ቢያበቃና የውጩ ንግድም እንዲራመድ ቢረዳ በሌላ በኩል የውስጡን ገበያ ፍላጎት ደካማ ነው ያደረገው። የውስጥ ገበያን ካነሣን ቻይናም ከዓለም ኤኮኖሚ ተጽዕኖ ለመላቀቅና ሕዝቧን ከፍ ባለ መጠን የብልጽግናዋ ተካፋይ ለማድረግ ጠንካራ የውስጥ ገበያ ያስፈልጋታል።

በሌላ አነጋገር የተትረፈረፈ የውጭ ንግዷን ለማለዘብ የሌሎችን ምርቶች ይበልጥ ወደ አገር ማስገባቷ ጠቃሚ ነው። እርግጥ የብሄራዊ ምንዛሪዋን የሬንሚንቢን ዋጋም መቀነሧ ለዚህ የሚበጅ እንደሚሆን ነው የሚታመነው። ዛሬ በንግዱ መስክ ለተፈጠረው የሚዛን ዝቤት ለነገሩ አከራካሪ ሆኖ የሚቀርበው ይሄው የአገሪቱ ምንዛሪ ዋጋ ነው። ባለፈው የካቲት ወር አንድ ዓመት ቀደም ሲል ከነበረው አንጻር የውጭ ንግዱ መጠን ወደ 46 በመቶ ንሮ መገኝቱ የሚያመለክተው የምንዛሪውን ዋጋ ይበልጥ የማሳደግ ግፊት መከተሉን ነው።

ከቻይና በኩል እስካሁን የማያሻማ ጭብጥ አዝማሚያ ጎልቶ አይታይም። የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ አስተዳዳሪ ሹ-ሻዎ-ቹዋን በቅርቡ የአገሪቱ ምንዛሪ ዋጋ እንደሚቀነስ ቢጠቁሙም ጠቅላይ ሚኒስትር ዌን-ጂያባዎ በበኩላቸው በሣምንቱ በተጠናቀቀው የብሄራዊ ሸንጎ ጉባዔ ላይ በአሜሪካና በአውሮፓ አቅጣጫ ተመሳሳይ ጥሪ በመሰንዘር ጥያቄን በጥያቄ መመለሱን ነው የመረጡት። ለማንኛውም የጀርመን የፊናንስ ሚኒስቴር ባልደረባ ክሪስቲያን ካስትሮፕ እንደሚያምኑት በሃያል መንግሥትነት አቅጣጫ የምታመራው ቻይና ወደፊት ፈጠነም ዘገየ ምንዛሪዋን ከዓለም ሁኔታ የሚጣጣም ማድረጓ የማይቀር ነው የሚሆነው።

Wirtschaftsminister China Bo Xilai
ምስል AP

“ቻይና እርግጥ እኩል መብት ያላት የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም ዓባል መሆን አለባት። ይህ በኤኮኖሚ እጅግ ጠንካራ ለሆነችው ለዚህች አገር በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። አንዳንዴ እንደማስበው የቻይና ባልደረቦቼ የሕዝባዊት ሬፑብሊኳን የኤኮኖሚና የፖለቲካ አቅም ገና ዝቅ አድርገው የሚመለከቱ ነው የሚመስለኝ”

ባለሥልጣኑ እንደሚያምኑት እርግጥ መለወጥ ያለባቸው በውጭ ንግዱ ሰፊ ድርሻ ያላቸው አገሮች ብቻ አይደሉም። የንግድ ድርሻቸው ከሚዛን በታች የሆነው አገሮችም ሁኔታውን ለማሻሻል ከባድ ጥረት ይጠበቅባቸዋል።

“በተለይ ለኤውሮ-ዞን አካባቢ ለማለት የምፈልገው ነገር ቢኖር ኪሣራው ያለባቸው አገሮች ሁኔታውን የማጣጣሙን አብዛኛውን ሸክም መቀበል እንዳለባቸው ነው”

አሜሪካን በተመለከተ የባንኩ ባለሙያ ቶርስተን ቪንደልስ እንደሚያስገነዝቡት አገሪቱ በራሷ መዋዕለ-ነዋይ ለመገልገልና መንግሥታዊ ዕዳዋን በራሷ ለመቀነስ ቁጥባ መጀመር ይኖርባታል። ለነገሩ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማም የአገሪቱን የውጭ ንግድ ለማጠናከር ጥረት እንደሚያደርጉ በቅርቡ አስታውቀዋል። ኦባማ አሜሪካ ወደ ውጭ የምትሸጠውን ምርት በሚቀጥሉት አምሥት ዓመታት ውስጥ በእጥፍ ለማሳደግ ነው የሚያስቡት። ከተሣካ ታላቅ ዕርምጃ በሆነ ነበር። በውጩ ንግድ ረገድ የሚታየው የሚዛን ዝቤት ለዓለም ንግድ አደገኛ እንዳይሆን በወቅቱ የሚሰጉት የኤኮኖሚ ጥበብት ብዙዎች ናቸው።

በሌላ በኩል የግሪክ የበጀት ዕዳ ብዙ ሲያነጋግር በከረመባት በዚህ በአውሮፓ ፈረንሣይ ደግሞ የጀርመን የውጭ ንግድ ሰፊ ድርሻ የሌሎች ደካማ የኤውሮ አገሮችን ሁኔታ እያዳከመ ነው ስትል በሣምንቱ መግቢያ ላይ በየጊዜው ሲያንዣብብ የቆየው ክርክር መልሶ እንዲቀሰቀስ አድርጋለች። የፈረንሣይ ውጭ’ ጉዳይ ሚኒስትር ክሪስቲን ላጋርድ ጀርመን ሁኔታውን ለመለወጥ በውስጥ ገበያዋ ላይ ያለውን ፍላጎትና ፍጆት ማጠናከር አለባት ባይ ናቸው። እርግጥ ይህን ማድረጉ በተለይ በዛሬው የኤኮኖሚ ቀውስ ወቅት ቀላል ነገር አይሆንም። በውስጡ ገበያ ላይ ያለውን ፍጆት ለማጠናከር የተጠቃሚውን የገንዘብ አቅም ማሳደግ ያስፈልጋል። ግን ይህ በአንድ በኩል ደሞዝ ጭማሪንና በሌላ በኩልም ግብር ቅነሣን ቅድመ-ግዴታ የሚያደርግ ነው የሚመስለው።

ግሪክን በተመለከተ የሕብረቱ መንግሥታት የፊናንስ ሚኒስትሮች አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ከበጀት ዕዳ ላይ የወደቀችውን አገር ለመርዳት ፈቃደኛ መሆናቸውን ትናንት እንደገና አረጋግጠዋል። ይሁንና የሃሣብ ልዩነቱን ደበስበስ ለማድረግ ከመሞከሩ ባሻገር ጭብጥ ነገር ገና አልተገኘም። ፈረንሣይ በጀርመን አቅጣጫ የሰነዘረችው ወቀሣ ችግሩን ይበልጥ እንዳያባብስ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የሚያሰጋ ነው።

መስፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ