1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዐባይ ወንዝ፦ የኢትዮጵያና የግብጽ ግንኙነት

ሐሙስ፣ የካቲት 19 2007

የዐባይ ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት ፣ ወንዙን በጋራ ለልማት የመጠቀም መብታቸውን የሚያስከብር የውል ሰነድ አብዛኞቹ ከፈረሙ ወዲህ የዋናይቱ አፈንጋጭ ግብፅ ወሳኝ አቋም ምን እንደሚሆን ለማወቅ አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱ የሚታበል አይደለም።

https://p.dw.com/p/1EiNX
ምስል William Lloyd-George/AFP/Getty Images

«ግብጻውያን አንዲት ጠብታ ውሃ እንዲገታብን አንፈቅድም፣ ማንኛውንም አማራጭ እንጠቀማለን» የሚሉና የመሳሰሉ የፖለቲካም ሆነ ወታደራዊ ዝብዝብ፤ ሲብሉ ፕሬዚዳንት ሙሐመድ ሙርሲ ከሥልጣን እስከተወገዱበት ጊዜ ድረስ ደጋግመው ያሰሙ እንደነበረ የሚታወስ ነው። ይሁንና ራሳቸው ከጦር ኃይሉ የመጡት ጀኔራል አል ሲሲ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ የቀድሞው ዛቻ ረገብ ብሎ ከኢትዮጵያ ጋር የመቀራረብ ፖሊሲ የተቀየሰ ይመስላል። ስለግብፅና ኢትዮጵያ የጀርመን የፖለቲካ ሳይንስ ተቋም ባልደረባ ስቴፋን ሮል ያቀረቡትን ጽሑፍ መነሻ በማድረግና በማነጋገር ፤ የቀረበው ዘገባ የሚከተለው ነው።

ዋና ጽ/ቤቱ በበርሊን የሚገኘው የሳይንስና ፖለቲካ ተቋም ባልደረባ፣ በተለይም የግብፅ የፖለቲካና ኤኮኖሚ ጉዳዮች ጥናት ተከታታይ ሽቴፋን ሮል ፤ የግብጽ ዐባይ ነክ ፖለቲካ በኧል ሲሲ አመራር ፤ በሚል ርእስ አንድ ዘገባ አቅርበዋል። ቀደም ባለው ጊዜ የነበሩት የግብፅ መሪዎች በሆነ ባልሆነው ሲዝቱ፤ ወታደሩ ፤ ጀኔራሉ ግን ፣ የሀገር መሪነቱን ሥልጣን ከጨበጡ ወዲህ ከፍጥጫ ይልቅ ተባብሮ መሥራትን የመረጡበት ሁኔታ ነው የሚታየው ይባላል። በእርሳቸው ዘገባም ላይ ይህ ነው የተንጸባረቀው፣ ምክንያት ሰበቡ ምን ይሆን?

Malabo Gipfel Afrikanische Union Sisi Hailemariam 26.06.2014
ምስል Reuters

«ግብጽ አሁን የዐባይን ወንዝ በተመለከተ አመለካከቷን ለወጥ ያደረገችበት ሁኔታ እንደሚመስለኝ፤ በዛ ያሉ ምክንያቶች ይኖሩታል። ዐቢይ ምክንያት የሚመስለው ፤ የኢትዮጵያው «የሕዳሴ ግድብ» በአሁኑ ጊዜ ሥራው የአቅዱን እርከን ተከትሎ የቀጠለ በመሆኑ ፣ ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር ከመደራደር ሌላ አማራC እንደሌላት ግንዛቤ ማግኘቷ ነው። ወታደራዊ ርምጃ አማራጭ ሊሆን እንደማይችል አውቃለች። የኢትዮጵያውን የግድብ ሥራ፤ ቦንብ በመጣል እንዲቋረጥ ማድረግ እንደማይቻል ተገንዝባለች። በተጨባጭ ሊሳካ የሚችልም አይደለም። ይህን ደግሞ ወታደሩ አብደል ፋታሕ ኧል ሲሲ ጠንቅቀው ያውቁታል። »

የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪካዊ የመከላከል ኃይልና ጽናት እንዳለ ሆኖ፤ ግብጽ ሩቅ ቦታ ድረስ በመዝመት ጉዳት የሚያደርስ አየር ኃይልም እንደሌላት ፤ የእስካሁንም ዛቻ ፤ እንዲሁ የቃላት ጨዋታ ነበረ ያሉት ሽቴፋን ሮል የረጅም ጊዜ ተጓዳኟ ሱዳን ለግድቡ ሥራ ተጻራሪ ሳትሆን ፤ እንዲያውም ደጋፊ ሆና መገኘቷም በመጠኑም ቢሆን፤ ለግብጽ የአቋም ለውጥ ድርሻ ሳይኖረው አለቀረም ፣ ይሁንና አሉ ሽቴፋን ሮል ምክንያቶችን ሲያጠናክሩ ----

«የካይሮው የአብደል ፋታሕ ኧል ሲሲ አስተዳደር ለምን አሁን ከኢትዮጵያ ጋር መስማማቱን እንደፈለገ ሌሎች ምክንያቶችም አሉ፤ ኣንዱ ምክንያት --ኤኮኖሚ ነው። እንዳጠናሁት ግን ዋናው ዐቢይ ምክንያት፤ የጸጥታ ጉዳይ ነው። ግብጽ በደቡባዊው የቀይ ባሕር ጫፍ ካለው የፀጥታ ችግር አንጻር በሰሜን ምሥራቃዊው አፍሪቃ ጠንካራ ተጓዳኝ ትፈልጋለች። የተጠቀሰው አካባቢ የፀጥታ የጸጥታ ግብፅን እጅግ ያሳስባታልና!»

የኢትዮጵያ ሕዝብ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማግኘት እንደተቸገረ ቢሆንም፤ የኢሕአዴግ መንግሥት ከግድቡ የሚገኘውን 6,000 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለአጎራባች ሃገራት ለመሸጥ ፍልጎት እንዳለው ነው በተደጋጋሚ መግለጹ የተሰማው። በዚህ ረገድ ግብፅ ያላት ፍላጎት እስከምን ድረስ ነው ? ያጠኑትም ካለ አያይዘው ቢነግሩን--

Blauer Nil Wasserfall Äthiopien
ምስል DW/Azeb Tadesse Hahn

«ግብፅ በመሠረቱ ከደቡባውያኑ ጎረቤት ሃገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት ፍላጎት እንዳላት ይሰማኛል። እርግጥ ከመጠን በላይ የኃይል ምንጭ በመሻት ምናልባት የኢትዮጵያ ጥገኛ የመሆኑን አደጋ አትፈልገውም። ሁለቱም በእኩል ደረጃ ላይ ያሉ አገሮች ናቸው። ይሁንና ምናልባት ወደፊት በዚህ ረገድ የሚፈጸሙ ጉዳዮች ይኖሩ ይሆናል። ግብፅ ፤ ከኢትዮጵያ የኃይል ምንጭ ትገዛ ይሆናል፤ ለምንስ አታደርገውም?!

ያም ሆኖ እንዳልኩት መሠረታዊው አወዛጋቢ ነጥብ የዐባይን ውሃ የመከፋፈሉ ጉዳይ ነው። አሁን ግብጽ፤ ለዘብ ያለ አቀራረብ ይታይባት እንጂ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው የመቀራረብ አዝማሚም ሆነ ግንኙነት ገና የመጨረሻ እልባት አልተደረገለትም። የአሁኑ የግብፅ መንግሥት ፈላጭ ቆራጭ መሆኑ የሚታበል አይደለም። አመክንዮ እንደሚያስረዳው እንዲህ ዓይነቱ ውዝግብ እንዲባባስ ሲደረግ ፣ የፖለቲካ ርምጃ አይደለም ማለት የሚቻል አይደለም። ስለሆነም ይህን አሁን የምናየውን ሰላም ለዘለቄታው አስተማማኝ አድርገን መመልከት አንችልም።»

ተክሌ የኋላ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ