1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የውጭ ዜጎችና የትምህርት ደረጃቸው

ማክሰኞ፣ ግንቦት 20 2005

በአሁኑ ጊዜ ወደ ጀርመን የሚመጡ የውጭ ዜጎች ከጀርመናውያን የተሻለ የትምህርት ደረጃ እንዳላቸው በቅርቡ የተካሄደ አንድ ጥናት አስታውቋል ። ይሁንና ጥናቱ እንዳመለከተው ጀርመናውያን አሁንም የውጭ ዜጎች የተማሩ አይደሉም ከሚለው አሰተሳሰባቸው አልተላቀቁም ። በዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን ይህን ጥናት መነሻ ያደረገ ዝግጅት ተጠናቅሯል ።

https://p.dw.com/p/18fsD
ኢጣልያዊትና ፣ህንዳዊ ሳይንቲስቶች በማግድቡርግ ከጀርመናዊ ፕሮፌሰራቸው ጋርምስል picture-alliance/dpa

በርካታ ጀርመኖች ስለ ውጭ ዜጎች የተሳሳተ አመለካከት እንዳላቸው በቅርቡ የወጣ አንድ ጥናት አስታውቋል ። እንደ ጥናቱ ቀደም ባሉት ዓመታት ወደ ጀርመን ይሰደዱ ከነበሩት የውጭ ዜጎች አብዛኛዎቹ ያልተማሩና በአመዛኙ በጉልበት ሥራ የሚሰማሩ ስለነበሩ ያ የቀድሞው የውጭ ዜጎች ምስል ከአብዛኛዎቹ ጀርመናውያን የጠፋ አይመስልም ። ይሁንና በአሁኑ ጊዜ ጀርመን የሚመጡት የውጭ ዜጎች ከዚህ በተቃራኒው በከፍተኛ ደረጃ የሠለጠኑ መሆናቸውን ጥናቱ ደርሶበታል ። ሹ ቼን ቻይናዊ ነው ። የተወለደበት ቦታና የተማረባት ከተማ በመኪና 2 ሰዓት የሚፈጅ ርቀት አላቸው ። የሹ ቼን ወላጆች ጥሩ ትምህርት እንዲያገኝ በማሰብ ዘመድ ጋ ሆኖ ትልቋ ከተማ ሻንጋይ በሚገኝ ትምህርት ቤት እንዲማር አደረጉ ። ያኔ ሹ ቼን የ 6 ዓመት ሕጻን ነበር ። ህንፃ በህንፃ ከሆነችው ሻንጋይ 19 ዓመት ሲሞላው በጀርመንዋ በራይንላንድ ፋልስ ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ስር ወድምትገኘው የጀርመንዋ የገጠር ከተማ WORM መጣ ። እዚያም የምጣኔ ሃብት ትምህርት ተከታተለ ። 

Deutschland ausländische Experten
ህንዳዊቷ የ IT ጠቢብምስል picture-alliance/dpa

ሹ ቼን ዛሬ የ35 ዓመት ጎልማሳ ነው ። በአንድ የጀርመን የመካኒካል ምህንድስና ኢንዱስትሪ ውስጥ በአመራር ደረጃ ይሠራል ። እንደ ሹ ቀንቷቸው በጀርመን ተመሳሳይ ደረጃ ላይ የሚገኙ የውጭ ዜጎች ጥቂት አይደሉም ። ቴክኖሎጂ ወይም ምህንድስና ለማጥናት ጀርመንን የሚመርጡ እስያውያን ቁጥር በርካታ ነው ። በተለይ ቻይናዎች ኮምፕዩተር ሳይንስ የንግድ ሥራ ትምህርት ወይም ምህንድስና ለማጥናት ወደ ጀርመን ይመጣሉ ። ቶብያስ ቡሽ PersonalGlobal ለተባለው ኩባንያ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ቻይናውያንንና ከፍተኛ ሃላፊዎችን ይመለምላሉ ። ቡሽ እንደሚሉት በአሁኑ ጊዜ በርካታ ቻይናውያን ጀርመን ውስጥ ከፍተኛ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው ። ይሁንና እንደ ቡሽ ከቻይና ህዝብ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር ያን ያህል ብዙ የሚባል አይደለም ።  

« እንደ ህዝቡ ብዛት ከታየ የተማረውን ቁጥር ብዙ ሊባል የሚችል አይደለም ። እኔ እንደማየው ከሆነ በተለይ በጀርመን አገር ጥቂትም ቢሆኑ ከቻይናውያን ልሂቃን መካከል በከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ አሉ ። ስኬታማ ለመሆን በጉጉት ወደ ጀርመን ለመጡት ተስጥኦ ያላቸው ተማሪዎች ይህ አንድ አዎንታዊ ክስተት ነው ።» 

Symbolbild Zuwanderung von Fachkräften
ቻይናዊቷ ሳይንቲስትምስል Darren Baker/Fotolia

ብዙዎቹ ቻይናውያን ጀርመንን ያለ ምክንያት ለትምህርት አልመረጡም ። የሃብታሞቹ ልጆች  እንግሊዝ ወይም አሜሪካን በሚገኙ ብዙ ገንዘብ በሚያስከፍሉ ዩኒቨርስቲዎች ነው የሚማሩት ። መለስተኛ ገቢ ያላቸው ደግሞ ልጆቻቸውን ጀርመን ያስተምራሉ  ። ምክንያታቸውም ጀርመን ለትምህርት የምታስከፍለው ገንዘብ እንደ እንግሊዝና አሜሪካ ብዙ አይደለም ። በዚህም ቻይናውያን ይበልጥ ተጠቃሚ ናቸው እንደ ቶብያስ ቡሽ ።

« ብዙዎች ከሚያስቡት በላይ በርካታ ቻይናውያን ምሁራን ጀርመን ውስጥ አሉ ። በአሁኑ ሰዓት በእርግጠኝነት ከ20 ሺህ እስከ 30 ሺህ የሚደርሱ የመጀመሪያና 2 ተኛ ዲግሪ ያላቸው ቻይናውያን አሉ ። በኔ አመለካከት ይህ የሆነበት ምክንያት ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነጻጸር በጀርመን ከፍተኛ ትምህርት ብዙ ገንዘብ የሚጠይቅ ባለመሆኑና አንዳንዴም በነፃ ስለሚሰጥ ነው ። የካድሬ ልጆች ግን ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታኒያ መማር ነው የሚፈልጉት ። ሆኖም ኑሮ በመጠኑም ቢሆን የሚከብዳቸውና ራሳቸውን በራሳቸው መደገፍ ያለባቸው ግን ጀርመን መምጣት ነው የሚፈልጉት ፤ ብዙዎቹም በተለይ ወደ ምህንድስና የትምህርት ክፍሎች መግባት ነው የሚፈልጉት ። »

Zuwanderung in Deutschland
ታንዛኒያዊው ተማሪምስል picture-alliance/dpa

ከጀርመን ህዝብ አብዛኛው የውጭ ዜጎች ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ አላቸው ብሎ ነው የሚያስበው ። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ጀርመን የሚመጡት የውጭ ዜጎች ግን ከጀርመናውያኑ በእጥፍ የሚልቅ የትምህርት ደረጃ አላቸው ። እውነታው ይሄ ሆኖ ሳለ ይህን መሰሉ አስተሳሰብ አሁንም በጀርመናውያን ዘንድ ያለ መሆኑን ስለ ጀርመን የሰራተኛ ፍላጎትና አቅርቦት ጥናትና ምርምር የሚያካሂዱት ሄርበርት ብሩከር ያስረዳሉ ። ቤርትልስማን በተባለ የምርምር ተቋም ድጋፍ በዚህ ጉዳይ ላይ አዲስ ጥናት ያካሄዱት ብሩከር ያገኙት ውጤት ፣ ጀርመናውያን ከሚያስቡት በተቃራኒው መሆኑን ነው የሚያስረዱት ። ጥናቱ ቅርብ ጊዜ ወደ ጀርመን ከመጡትና ፣

ከ 15 እስከ 65 ዓመት እድሜ ከሚደርስ የውጭ ዜጎች 43 በመቶው ከዩኒቨርስቲ ወይም ከቴክኒክ ኮሌጅ የማስተርስ አለያም የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው ። ይህ አሃዝ እጎአ በ2ሺህ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ገደማ ያህል ይበልጣል ያኔ ከነዚህ ዲግሪዎች አንዱ ያለው በመቶ ሲሰላ 26 በመቶ ብቻ ነበር ። በዚሁ ተመሳሳይ ጊዜ ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ሰዎች ቁጥር በግማሽ ያህል ቀንሷል ። ያኔ 40 በመቶ የነበረው አሁን ወደ 25 በመቶ ወርዷል ። በአሁኑ ሰዓት ወደ ጀርመን የሚሰደዱት ቻይናውያን ብቻ አይደለም ። አብዛኛዎቹ የሚሰደዱት ከአዳዲሶቹ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራትም ጭምር ነው ። በአሁኑ ጊዜ ሰዎች ከነዚህ ሃገራት ወደ ጀርመን የሚሰደዱበት ምክንያት ከዩሮ ቀውስ ጋር የተያያዘ ነው ። በቀደሙት ዓመታት የብዙዎች ስደተኞች ምኞት የነበሩት የአውሮፓ አገራት አሁን እንደ ቀድሞው ሰዎችን የሚስቡ አልሆኑም ። በተቃራኒው አሁን ጀርመን በርካታ የውጭ ዜጎችን የምትማርክ ሃገር ሆናለች ። በፌደራል ጀርመን ስታትስቲክስ ፅህፈት ቤት ስሌት መሠረት ባለፈው አመት ጀርመንን ለቀው ከወጡት የውጭ ዜጎች ወደ ጀርመን የገቡት በ 369 ሺህ ይበልጣሉ ። ይህ አሃዝም እንደ መሥሪያ ቤቱ እጎአ ከ 1995 ወዲህ ከፍተኛው ነው ። ኽርበርት አሁን ወደ ጀርመን የሚመጣው የውጭ ዜጋ ቁጥር ከፍ ለማለቱ ምክንያት የሚሉት አውሮፓ የገጠመውን የፋይናንስ ቀውስ ነው ።

« በርግጥ ፍልሰት በእጅጉ ከዩሮ ቀውስ ጋር የተያያዘ ነው ። በዚህ የተነሳም ከደቡባዊ አውሮፓ ሃገሮች ሰዎች በብዛት በመሰደድ ላይ ናቸው ። በተለይም ከማዕከላዊና ምሥራቅ አውሮፓ ከሚገኙት ከአዳዲሶቹ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት የሚሰደዱት ቁጥር ከፍ ብሏል ። የቀድሞዎቹ የውጭ ዜጎች መስህብ የነበሩት ስፓኝ ኢጣልያ ብሪታኒያ ና አይርላንድ አሁን እንደ ድሮው ስደተኞችን መማረካቸው ቀርቷል ። »

ጀርመን ለጊዜው የስደተኞች መስህብ ብትሆንም በብሮከር እምነት ይህ በዘላቂነት የሚቀጥል አይሆንም ። 

Herbert Brücker Institut für Arbeitsmarkt und Berufsforschung
ኽርበርት ብሮከርምስል privat

« የዩሮ ቀውስ ጋብ ካለ ወደ ጀርመን የሚፈልሰው ህዝብ ቁጥር በጣም መቀነሱ አይቀርም ። ስለሆነም በዚህ ጉዳይ ላይ ከወዲሁ ልናስብበት ይገባል ። ወደፊት በቀጣይነት ወደ ዚህ ሃገር የሚመጡትን እንነማን ይሆናሉ  የሚለውንም ማጤን አለብን ። ወደፊት ስደተኞች ከአውሮፓ ህብረት ውጭ ከሆኑ አገራት ነው የሚመጡት ። በዚህ ሁኔታ ከሃገር አገር የሚዘዋወሩት ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ቅድመ ግዴታ የሚያስቀምጠው የፖለቲካ አመራር ለውጥ ማድረግ ይኖርበታል ። »

የቤርትልስማን የምርምር ተቋም የጀርመን የፍልሰት መርህ እንዲለወጥ ይጠይቃል ። ተቋሙ በጀርመን ባንዲራ ቀለም ጥቁር ቀይ ወርቅማ ብሎ የሰየመውን የሥራ ና የመኖሪያ ፈቃድ  ጀርመን ውስጥ የሠራተኛ እጥረት ባለባቸው የሥራ መስኮች በከፍተኛ ደረጃ ለሠለጠኑ የውጭ ዜጎች መንግሥት እንዲያዘጋጅ ይጠይቃል ። ተቋሙ የተጠየቀው ያልተገደበ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ የሚያሰጠውን ፈቃዱ የውጭ ዜጎችን የሥልጠና ደረጃና የጀርመን ቀጣሪዎችን የሠራተኛ ፍላጎት ግምት ውስጥ እንዲያስገባ ያሳስባል ።

« በርግጥ ከ አሜሪካ ከካናዳና አውስትራሊያ ጋር እንወዳደራለን እነዚህ ሃገሮች ወደ ሃገር የሚገቡትን ሰዎች የሚቀበሏቸው የነጥብ አሰጣጥ ስርዓትን የመሳሰለውን ካስተካከሉ በኋላ ነው ። እነዚህ ሃገሮች ወደሃገር የሚገቡ ሰዎችን ሁኔታ የሚያስተካክሉት ባወጡት ደንብና በተመሳሳይ የማጣራት ሂደት ነው ። እኛ የሚያስፈልገን ይህን የመሰለ የህግ ለውጥ ብቻ አይደለም ። ከዚህ ጎን ለጎን ግልፅ የሆነ የማወዳደሪያ ስልት መከተል ይኖርብናል ። ጀርመን ሰዎች ገብተው የሚሰፍሩባት ሃገር መሆንዋንም በግልፅ ማስቀመጥ አለብን ። ከውጭ የሚገቡትን ሰዎች  በጥርጣሪ የሚታዩ እንዲያደርግ ሳይሆን የምንከተለው ከውጭ የሚገቡ ሰዎችን የሚመለከተው ደንብ የተፍታታ ና ወደ ጀርመን እንኳን ደህና መጣችሁ የሚያሰኝ መሆን አለበት ። »

ተቋሙ እንደሚለው የውጭ ዜጎች ጀርመን ውስጥ መሥራታቸው ጥቅሙ ለጀርመን ብቻ አይደለም ። የስደተኞቹም ምንጭ ለሆኑ አገሮችም ጭምር ነው ።

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ