1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የውጭ ተማሪዎች በአውሮፓ ህብረት

ማክሰኞ፣ መጋቢት 24 2005

በአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት የተማሪ ቪዛ አሠጣጥ ደንብ የተወሳሰበ ና ግልፅነትም የሚጎድለው መሆኑ ነው የሚነገረው ። ቪዛ ማግኘት ረዥም ጊዜ ሊወስድ ከመቻሉም በላይ አሰጣጡም ከአገር አገር ይለያያል ። ከአንዱ የአውሮፓ ሃገር ወደ ሌላው መንቀሳቀስ ለተማሪዎች በጣም አስቸጋሪ አንዳንዴም ፈፅሞ የማይቻል የሚሆንባቸው አጋጣሚዎችም አሉ ።

https://p.dw.com/p/188Nr
BU Bild 2, "Fährenkämper mit Subash": Renate Fährenkämper, 67, Gründerin des Patenschaftsprojektes zwischen Seniorenstudierenden und ausländischen Studierenden an der TU Dortmund, mit Subash, einem Studenten aus Indien. Copyright: Sola Hülsewig Hiermit räume ich der Deutschen Welle das Recht ein, die von mir bereitgestellten Bilder zeitlich, räumlich und inhaltlich unbeschränkt zu nutzen. Ich versichere, dass ich die Bilder selbst gemacht habe und dass ich die hier übertragenen Rechte nicht bereits einem Dritten zur exklusiven Nutzung eingeräumt habe.
Deutschland Studierende TU Dortmund Patenschaftምስል Sola Hülsewig

ቁጥራቸው ከ 200 ሺህ የሚበልጥ ተማሪዎችና ተመራማሪዎች በየአመቱ ወደ አውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ይመጣሉ ። እጎአ በ 2011 ለትምሕርት ፣ በተማሪዎች የልውውጥ መርሃ ግብር ለሥልጠና ፣ እንዲሁም ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወደ አውሮፓ ህብረት አባል ሃገራትየመጡ የውጭ ዜጎች ቁጥር ወደ 220 ሺህ ይጠጋል ። ከነዚህም አብዛኛዎቹ ለትምህርት እንዲሁም ለጥናትና ምርምር ነው የመጡት ። በዚሁ አመት 5 የህብረቱ አባል ሃገራት በርካታ ተማሪዎችን ተቀብለዋል ። እነርሱም ፈረንሳይ 64 ,794 ፣ስፓኝ 35,037 ፣ኢጣልያ 30,260 ፣ጀርመን 27,568 እንዲሁም ኔዘርላንድስ 10,701 ተማሪዎችን ተቀብለዋል ። በዚሁ አመት በ24 ት የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ለጥናትና ምርምር የገቡት የውጭ ዜጎች ቁጥር 7 ሺህ ይደርሳል ። ከመካከላቸው 2,075 ቱን ፈረንሳይ 1,616 ቱን ኔዘርላንድስ 817 ቱ ስዊድን ፣ 510 ሩን ደግሞ ፊንላንድ እንዲሁም 447ቱ ስፓኝ ነው የሄዱት ። ይሁንና አብዛኛዎቹ ለትምህርት በመጡባቸው አገሮች ለተለያዩ ቢሮክራሲያዊ ችግሮች የተጋለጡ ናቸው። በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት የተማሪ ቪዛ ወይም የመኖሪያ ፈቃድ አሠጣጥ ደንብ የተወሳሰበ ና ግልፅነትም የሚጎድለው መሆኑ ነው የሚነገረው ። ቪዛ ማግኘት ረዥም ጊዜ ሊወስድ ከመቻሉም በላይ አሰጣጡም ከአገር አገር ይለያያል ። ከአንዱ የአውሮፓ ሃገር ወደ ሌላው መንቀሳቀስ ለተማሪዎች በጣም አስቸጋሪ አንዳንዴም ፈፅሞ የማይቻል የሚሆንባቸው አጋጣሚዎችም አሉ ።

Vorlesungsbeginn an Universität in Magdeburg
ምስል picture-alliance/dpa

ይህም ህብረቱ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች በቀላሉ እንዳያገኝ መሰናክል እንደሆነበት አስታውቋል ። የህብረቱ የሃገር ውስጥ ጉዳዮች ኮሚሽነር ሴሲሊያ ማልምስትሮም በሰጡት መግለጫ ወደ አውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ለትምሕርት ወይም ለጥናትና ምርምር መምጣት ፣ ከሚገባው በላይ አስቸጋሪ ሆኖ ተገኝቷል ። ህብረቱን ልዩ ተስጥኦ ላላቸው ተማሪዎች ክፍት ለማድረግ እነዚህ ችግሮች መወገድ እንደሚገባቸውና ይህም ህብረቱንና ኤኮኖሚውን በእውቀትና በአዳዲስ ሃሳቦች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ኮሚሽነሯ አስታውቀዋል ። እውቀት ኃይል ነው የሚሉት ማልምስትሮም በአውሮፓ ህብረት በእውቀት ላይ የተመሠረተ ስኬታማ ኤኮኖሚን ለማዳበር የውጭ ዜጎችን የሚስብ አሠራር መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል ። ምንም እንኳን በአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ውስጥ የሥራ አጡ ቁጥር 26 ሚሊዮን ቢገመትም ፣ በርካታ አባል ሃገራት እጅግ ተፈላጊ የሆኑ ሙያተኞች እጥረት ባለባቸው የሥራ መስኮች የሚጎድለውን የሠራተኛ ኃይል ለማሟላት ጥረታቸውን አላቋረጡም ። የአውሮፓ ህብረት እንደ ዩናይትድ ስቴትስ አውስትሬልያ እና ጃፓን ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣት ሠራተኞችን የሚያማልሉ አሠራሮችን ተግባራዊ ለማድረግ አቅዷል ።

ሳንድራ ሃስልሆፍ በጀርመኑ አሌክሳንደር ፎን ሁምቦልት ተቋም የሳይንስ ክፍል ሃላፊ ፣ የአውሮፓ ህብረት ያቀረባቸው አዳዲስ ሃሳቦች ጠቃሚ እምርታ መኖሩን ጠቋሚ ነው ይላሉ ።

«እንደማስበውና ተስፋ እንደማደርገው ይህ በሰፊው ችግሮችን የሚያቃልል ይሆናል ። ከነዚህም አንዱ የሚመለከተው የቪዛ ማመልከቻዎች በአፋጣኝ መልስ የሚያገኙበት፣ የከፍተኛ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ወጣቶች በአውሮፓ ህብረት ሃገራት ያለ ችግር ከቦታ ቦታ እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ በሆኑ የትምህርት ተቋማት ለምሳሌ ለዶክትሬት ማዕረግ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ሰዎች ያለ ችግር ትምሕርታቸውን መከታተል የሚችሉበት ሁኔታ ተግባራዊ እንደሚሆን ተስፋ አድርጋለሁ ። »

Ausländische Studenten an Fachhochschule Integration Greencard Spezialisten
ምስል picture-alliance/ dpa

ኮሚሽኑ ተማሪዎች ወደ ህብረቱ አባል ሃገራት የሚገቡበት ተመሳሳይ መስፈርት ማውጣት ና የወጣት ተማሪዎች አያያዝ እንዲሻሻልም ሃሳብ አቅርቧል ።የጀርመን የአካዳሚ ትምህርት ልውውጥ አገልግሎት በጀርመንኛው ምህፃር DAAD ባልደረባ ኡልሪሽ ግሮቱስ ህብረቱ የቬዛና የመኖሪያ ፈቃድ አሰጣጥን መሻሻሉ እሰየው የሚያሰኝ መሆኑን ጠቁመው ፣ ከዚያ ጎን ለጎን ከህብረቱ ውጭ ለሚመጡ ተማሪዎች ይበልጥ ሳቢና ማራኪ ሆና መገኘት እንዲሁም ፍላጎታቸውንም ማሟላት ይገባዋል ይላሉ ። እንደ ርሳቸው በዚህ ረገድ ፍላጎትና አቅርቦት ያልተጣጣሙባቸውን የትምህርት መስኮችን መፈተሽ ይገባል ።

« በአሁኑ ጊዜ ጀርመን ውስጥ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚሰጡ የድህረ ምረቃ መርሃ ግብሮችን ለመከታተል የሚቀርበው ማመልከቻ ካለው ቦታ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ነው »

ከዚህ ሌላ በግሮቱስ እምነት ተማሪዎች ዩኒቨርስቲዎች ገብተው መማር የሚያስችሏቸው ዲፕሎማዎቻቸው ፣ በአውሮፓ የሚሰጣቸው እውቅና መወሰን ያለበት በሚመጡበት ሃገር ሳይሆን በግል ችሎታቸው ምዘና መሆን ይኖርበታልም ይላሉ ። በርሳቸው አስተያየት ከአንዱ ሃገር የሚመጣው የትምህርት ማስረጃ በሌላው አለም ተቀባይነት ስለማይኖረው የሚመዘንበት መንገድ መስተካከል ይገባዋል

« ለምሳሌ ያህል አሜሪካ ውስጥ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ዲፕሎማ ካገኙ በኋላ ወደ ዩኒቨርስቲ ለመግባት ማመልከቻ ማስገባት ይችላሉ ። እንበል በአለም ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ አላቸው በሚባሉትም ሆነ በሃገር ውስጥ ዩኒቨርስቲዎችም ውስጥ አንድ ተማሪ ማመልከት ይችላል ። ያ ውጤቱ ግን ጀርመን ውስጥ ለመማር ብቁ አያደርገውም ። »

ግሮቱስ ለውጭ ዩኒቨርስቲዎች የሚያመለክቱ ተማሪዎች ፈተና እንዲሰጣቸው ነው ሃሳብ የሚያቀርቡት ። ይሁንና የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት የትምህርት ስርዓት በየሃገሩ የተለያየ በመሆኑ አውሮፓ አቀፍ ፈተና ማዘጋጀቱ ያስቸግራል ።

በህብረቱ አባል ሃገራት አሁን የሚሰራበት ደንብ ለጥናትና ምርምር ወደ አውሮፓ መምጣት የሚፈልጉ አንዳንድ አመልካቾች የሚገጥማቸውን ችግሮች የሚፈቱ ሆነው አልተገኙም ። በዚህ የተነሳም የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በመላው አውሮፓ ይበልጥ ግልፅና ከወቅቱ ሁኔታዎች ጋር የሚሄዱ ደንቦችን የህብረቱ ሚኒስትሮችና የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ እንዲያፀድቁት አዘጋጅቷል ።

Chinesische Studenten in Chemnitz
ምስል picture-alliance/ ZB

በእቅዱ መሠረት አሁን የሚሰራባቸው 2 የተማሪዎችና የተመራማሪዎች ማመልከቻዎች የሚስተናገዱባቸው ደንቦች በአንድ አጠቃላይ መመሪያ ይቀየራሉ ። አዲሱ መመሪያም ፣ የአባል ሃገራት ባለሥልጣናት ለተማሪዎች ወይም ለተመራማሪዎች ለቪዛና ለመኖሪያ ፈቃድ ማመልከቻዎች ፣ውሳኔ የሚሰጡበትን ጊዜ በ60 ቀናት ይገድባል ። ይህም ህብረቱ እንደሚለው የማመልከቻውን ሂደት ቀጥተኛና ግልፅ ያደርገዋል ። ክህሎትና እውቀትን በአውሮፓ ህብረት ውስጥ በቀላሉ ለማሻጋገር ተመራማሪዎች ፣ ተማሪዎችና ሰልጣኞች በህብረቱ አባል ሃገራት ውስጥ እንደልብ እንዲንቀሳቀሱ የሚፈቅዱ ደንቦችም ተዘጋጅተዋል ። ተማሪዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ቤተሰቦቻቸውም በተወሰነ ደረጃ የመዘዋወር መብት ይሰጣቸዋል ። ተማሪዎች በቆይታቸው ራሳቸውን ለመደግፍ በሳምንት ቢያንስ 20 ሰዓት እንዲሰሩም ይፈቀድላቸዋል ። ተመራማሪዎችና ተማሪዎች ትምህርታቸውንና ጥናታቸውን ካጠናቀቁም በኋላም በአንዳንድ የቅድመ ግዴታዎች መሠረት ሥራ ለመፈለግም ሆነ የራሳቸውን ሥራ ለመጀመር ለ12 ወራት እንዲቆዩ ይፈቀድላቸዋል ። ይህ ማለት ግን በቀጥታ ሥራ የመያዝ መብት ዋስትና አያሰጣቸውም ። ይሄ በብሔራዊ ደረጃ የሚወሰን ሃላፊነት ነው የሚሆነው ። የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ያረቀቀው ይህ ደንብ እ.ጎ.አ በ2016 ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ። በአሌክሳንደር ፎን ሁምቦልት ባልደረባ ሃስኦፍ አስተያየት የሙሉ ጊዜ ተማሪ ሆኖ 20 ሰዓት መስራቱ ብዙ ነው ። በጀርመን ህግ የውጭ ተማሪዎች መሥራት የሚፈቅድላቸው በአመት 120 ቀናት ውይም 240 ግማሽ ቀናት ብቻ ነው ።ይህም ካለ ክፍያ የሚከናወኑ የሥራ ልምምዶችን ያካትታል ። የአውሮፓ ፓርላማና የአውሮፓ ህብረት የሚኒስትሮች ጉባኤ የአውሮፓ ህብረት የሃገር ውስጥ ጉዳዮች ከሚሽነር ሲሲልያ ማልምስትሮም ባቀረቡት በዚህ እቅድ ላይ ይነጋገራሉ ። እቅዱ እንደተጠበቀው ከ 2 ዓመት ተኩል በኋላ ተግባራዊ ከሆነ የውጭ ተማሪዎች በአውሮፓ ሃገራት የሚገጥማቸውን ችግር ያቃልላል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል ።

ሂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ