1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የውሃ ሥርጭት በግል አቅራቢዎች ዕጅ?

ሐሙስ፣ መጋቢት 22 1997
https://p.dw.com/p/E0eq

ታዲያ በዚህ መልክ የውሃ አቅርቦትን ወደ ግል ዕጅ በማሻገሩ ጉዳይ ብርቱ ሙግት ተይዞ ነው የሚገኘው። በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉት ምዕራባውያን አገሮች አንዴ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ብቻ በነበሩት የትምሕርት መስክ፣ የኤሌክትሪክ ወይም የውሃ አቅርቦት ዘርፎች የግል አገልግሎት ሰጪዎች ሥር መስደድ ከያዙ ቆየት ብለዋል። ተሳትፏቸው እየጠነከረ እንደሚሄድም ነው ሁኔታው የሚያመለክተው። አሁን ደግሞ ታዳጊ አገራት መንግሥታዊ አገልግሎት ዘርፋቸውን እንዲከፍቱ እየተጠየቁ ነው። ግን ጉዳዩ ብርቱ ክርክር መቀስቀሱ አልቀረም።

ሃሣቡን የሚተቹ ተቃዋሚዎች የሰውልጅ መሠረታዊ ፍላጎት የሆኑ የተፈጥሮ ሃብቶች ትርፍ ከሚያሳድዱ ወገኖች ጥቅም በታች ሆነው ሊታዩ አይገባም ነው የሚሉት። በተለይ ውሃን በተመለከተ የሚሰማው ተቃውሞ በዓለም ዙሪያ ይበልጥ የጠነከረ ነው። “ውሃ የሁለም የሆነ የተፈጥሮ ጸጋ ነው፤ ስለዚህም እንደማንኛውም የቤት ቁሳቁስ ለጥቂት ኩባንያዎች ትርፍ ማጋበሻ ሊሆን አይገባውም።” ይህ የተነገረው ባለፈው ጥር ወር በፖርቶ አሌግሬው የዓለም ማሕበራዊ መድረክ ዓቢይ ጉባዔ ላይ ነበር።

የዶቼ ቬለ ባልደረባ ሞኒካ ሆይገን በጊዜው በፖርቶ አሌግሬ ተገኝታ ጠንካራው የበጋ ሙቀት የሚፈታተነው ነዋሪ ምን እንደሚል እዚህም-እዚያም አድምጣ ነበር። የድሆች ቀበሌዎችን ሁኔታም ተመልክታ ነበር የተመለሰችው። ለዘወትሩ ለዘብ ባለ የአየር ጠባይዋ በምትታወቀው የብራዚል ደቡባዊት ከተማ ያለፈው ጥር ሙቀት የሚቻል አልነበረም። የውሃ እጥረቱም የዚያኑ ያህል ያሳሰበ ነበር።

በብዙዎች ታዳጊ አገሮች ከፖርቶ አሌግሬ ማዕከል ወጣ ብለው እንደሚገኙ ጎስቋላ መንደሮች ሁሉ ውሃው ለዚያውም በቀጥታ ከወንዝ ነው የሚቀርበው። ታዲያ አንድ ወይም ሁለት ወር ዝናብ ካልጣለ የወንዙ ከፍታ ስለሚቀንስ ውሃው እንዲያውም የባሰ የጨቀየ ነው። ከቧምቧ የሚፈሰው ውሃ ደግሞ መጥፎ ጣዕም ስላለው ለመጠጥም ሆነ ለቅቀላ መጠቀም እንደማይቻል ነው ነዋሪው የሚናገረው። ለመጠጥ ንጹህ ውሃ መግዛት ግድ ይሆናል ማለት ነው።

በወቅቱ በብራዚልም የውሃ አቅርቦቱን ከመንግሥት ወደ ግል ኩባንያዎች ዕጅ በመሻገሩ ጉዳይ የሚደረገውን ውይይት ሕዝብ በሰፊው ያደምጠዋል። ይሁንና ለውጡ ምን ሊያመጣ ይችላል? እዚህ ላይ ነው ተሥፋም ስጋትም የሰዉን አዕምሮ ሲያስጨንቅ የሚታየው። እርግጥ የውሃ አቅርቦቱ አገልግሎት በግል ዕጅ ገብቶ ጥራቱ ቢሻሻልና ዋጋው የሚቻል ቢሆን ማንንም ባልከፋ ነበር። ግን የማይቀረው የዋጋ መናር የሚያሳስባቸው ብዙዎች ናቸው።

በፖርቶ አሌግሬ መዳረሻ መንደሮች ገና ከዛሬው አንድ ቤተሰብ ከሚያገኘው የተወሰነ የወር ገቢ ከአሥር በመቶ በላይ የሚሆነውን ድርሻ ለውሃ ነው የሚያወጣው። ለመጠት የሚሆን ንጹህ የማዕድን ውሃ መግዛቱም በተጨማሪ ግዴታ ነው። እንግዲህ በዝቅተኛ ገቢ ለሚታዳደሩት ነዋሪዎች ውሃ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ የቅንጦትን ያህል ሊሆን ብዙም አልቀረውም። እንደልብ መጸዳዳት፣ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ማርካት በቀላሉ የሚደፈር ነገር አይደለም። የልማቱም መጓተት ሌላው ችግር ነው።

በውሃ አቅርቦቱ ወደ ግል ዕጅ መሸጋገር ምናልባት ጥራት ሊከትል ይችላል የሚል ተሥፋ የጣሉ አንዳንዶች ባይታጡም ባለፈው ጥር ፖርቶ አሌግሬ ላይ የተካሄደው የዓለም ማሕበራዊ መድረክ ጉባዔ ሃሣቡን በሰፊ ድምጽ ተቃውሞታል። በጉባዔው ከተሳተፉት መካከል “Brot für die Welt”-”ዳቦ ለዓለም” በመባል የሚታወቀው የጀርመን ግብረ-ሰናይ ድርጅት ባልደረባ አኔተ ሽንፌልድም አንዷ ነበሩ። የጀርመን ወንጌላዊት ቤተ-ክርስቲያን የልማት ድርጅት ከሁለት ዓመታት በፊት ሕያው ላደረገው የውሃ ዘመቻ ሃላፊ የሆኑት ሽንፌልድ እንደሚሉት ውሃ ማግኘት መቻል የሰውልጅ ሰብዓዊ መብት ሆኖ የሚታይ ጉዳይ ነው።

በርሳቸው አተረጓጎም ውሃ ለሰውልጅ ሕልውና አስፈላጊ የሆነ የሕዝብ ንብረት ነው። ውሃ እንደማንኛውም ዕቃ ሆኖ ሊታይ አይገባውም፤ ሰው ያለሱ ሊኖር እንደማይችል መታወቅ አለበት። ለዚህም ነው ውሃ ማንም ሰው ሊገለገልበት፤ ሊደርሰው ይገባል የሚባለው። ለነገሩ አሁን የተባበሩት መንግሥታትም የውሃ መብትን ለዘብ ባለ መልክም ቢሆን ያውቃል። በሌላ አነጋገር ይህን መብት የሚያረጋግጥ ዓለምአቀፍ ሕግ ቢቀር በሃሣብ ደረጃ አለ ማለት ነው። ችግሩ አሣሪ አለመሆኑ ላይ ነው።

የጀርመኑ ግብረ-ሰናይ ድርጅት የውሃ አቅርቦቱን ዘርፍ ለመያዝ የሚጋፉትን ኩባንያዎች ለመግታት በሚያደርገው ትግል ተጨማሪ ዓለምአቀፍ ተጓዳኞችል ለማሰባበብም ይጥራል። አኔተ ሽንፌልድ እርግጥ በአንዳንድ መንግሥታዊ የውሃ ልማት መዋቅራት ማርጀትና በሙስና የተነሣ በታዳጊ አገሮች ያሉ ብዙ ከከተሞች ወጣ ያሉ ድሃ መንደሮች ከአቅርቦቱ እንደተነጠሉ አላጡትም። ቢሆንም የግል ኩባንያዎች ሁኔታውን ያሻሽላሉ የሚለውን አባባል አይቀበሉትም። በርሳቸው አስተሳሰብ የሚበጀው አማራጭ የውሃ አቅርቦቱ አገልግሎት በመንግሥት ዕጅ እንደቀጠለ ሆኖ የሕዝቡን አብሮ የመወሰንና የቁጥጥር መብት ማሻሻሉ ብቻ ነው።

ወደ ሁለተኛው ርዕሳችን እንሻገርና የዓለም ባንክ ለታዳጊ አገሮች ዋነኛው ገንዘብ አቅራቢ ተቋም እንደሆነው ሁሉ የአውሮፓን ሕብረት ዓባል መንግሥታት ልማት ለማዳበር መሠረት ሆኖ የሚገኘው በእጽሮት EIB በመባል የሚታወቀው የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ነው። ሉክሰምቡርግ ላይ ተቀማጭ የሆነው ባንክ ብዙ በይፋ ባይታወቅም ከበስተጀርባ ሆኖ በዓለምአቀፍ ደረጃ ክብደት የሚሰጠው የገንዘብ ተቋም ሊሆነ ከበቃ ቆየት ብሏል። በሚያቀርበው ብድር መጠን እንዲያውም የዓለም ባንክን አልፎ የሄደ ነው።

ከፓሪስ ተነስቶ ሽትራስቡርግን በማቋረጥ እስከ ምሥራቅ ሊዘልቅ የታቀደው የፈጣን ባቡር መረብ የአውሮፓ ኮሚሢዮን ቅድሚያ ሰጥቶ የሚያራምደው አንዱ ፕሮዤ ነው። ይህ ደግሞ ያለዚህ ባንክ የገንዘብ ዕርዳታ ጨርሶ ሊታሰብ ባልቻለ ነበር። ባንኩ ባለፈው ዓመት ብቻ የሥምንት ሚሊያርድ ኤውሮ ብድር አቅርቧል። የሉክሰምቡርጉ የገንዘብ ተቋም በሌሎች ዘርፎችም ጠቃሚ አገልግሎት የሚሰጥ ነው። ለምሳሌ በቼክ ሬፑብሊክ የጎርፍ መከላከል ፕሮዤን በማራመድ ወይም በአየርላንድ የሃይል ማመንጫ ጣቢያን በማነጽ ይተባበራል።

አፈ-ቀላጤው ጌርድ ሉዘር እንደሚሉት የባንኩ ተግባር የአውሮፓው ሕብረት የፖለቲካ ግቡ አድርጎ ላስቀመጣቸው ዓላማዎች ሁሉ በየቦታው ብድር በማቅረብ መርዳት ነው። የአውሮፓው ሕብረት በክልሉ ውስጥ የሚገኙ በዕድገታቸው ደከም ያሉ አካባቢዎችን ማልማቱን ዓቢይ ትኩረት ይሰጣል። ለዚሁ የሚሰጣቸውን የተለያዩ ዕርዳታዎች የሚያሟላውም ከባንኩ በሚገኘው ብድር ነው።

ሆኖም ፕሮዤዎችን በመምረጡ በኩል የአውሮፓው ባንክ ራሱ ነጻ ሆኖ ነው የሚወስነው። የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በዓመት 43 ሚሊያርድ ኤውሮ ብድር በማቅረብ ዛሬ ከመሰሎቹ ግዙፉ ነው። ከዓለም ባንክ እንኳ በልጦ ነው የሚገኘው። በሉክሰምቡርግ የአውሮፓ አደባባይ ሰወር ብሎ የሚገኘው ባንክ ዛሬ ከመላው አውሮፓ የተውጣጡ ከሶሥት ሺህ የሚበልጡ የፊናንስ ባለሙያዎች ተቀጥረው ይሰሩበታል። የተቋቋመው ገና በ 1958 ዓ.ም. ከሕብረቱ ቀዳሚ ከአውሮፓው የኤኮኖሚ ማሕበረ-ሕዝብ ጋር ነበር።

በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ተቀዳሚ ተግባሩ ድሃውን የደቡብ ኢጣሊያ አካባቢ ልማት ማራመድ እንደነበር ይታወሣል። ከ 1990 ወዲህ ደግሞ ይበልጡን በማዕከላዊና ምሥራቅ አውሮፓ ነው አተኩሮ የሚገኘው። ዓላማውም እነዚሁ የሕብረቱ አዳዲስ ዓባል ሃገራት ከምዕራቡ አማካይ የልማት ደረጃ እንዲደርሱ መደገፍ ነው። ይህ ደግሞ ረጅም ጊዜ የሚፈጅ ፕሮዤ እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም። በነዚሁ ሃገራት የሚንቀሳቀሱት ፕሮዤዎች ሲበዛ በባንኩ ዕርዳታ ላይ ጥገኞች ናቸው። ሆኖም ብድሩ በረጅም ጊዜ ተከፋፍሎ የሚሰጥናና የሚመለስ መሆኑ ችግሩን ያቀለዋል።