1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮንጎ ብራዛቪል ፕሬዚደንታዊው ምርጫ ዝግጅት

ቅዳሜ፣ ጥር 14 2008

የኮንጎ ብራዛቪል መንግሥት ባለፈው ታህሳስ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት፣ የፊታችን ሀምሌ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው ፕሬዚደንታዊው ምርጫ ከሁለት ወር በኋላ እአአ የፊታችን መጋቢት 20፣ 2016 ዓም ይደረጋል።

https://p.dw.com/p/1Hicz
Kongo Brazzaville
ምስል Getty Images/AFP

[No title]

ይህም ሂደቶች መፋጠን እንደሚኖርባቸው ነው የሚያሳየው። ከገዚው ፓርቲዎች፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ከሲቭሉ ማህበረሰብ የተውጣጡ ቡድኖች የተጠቃለሉበት አንድ አስመራጭ ኮሚሽን የቀድሞውን ከመንግሥት አካላት የተዋቀረውን አስመራጭ ኮሚሽን እንዲተካም ይፈለጋል።
«ሕገ መንግሥታዊውን ስርዓት አስከባሪው እና ዴሞክራሲያዊው ለውጥ አራማጅ ሬፐብሊካዊ ግንባር»፣ በምህፃሩ «ፍሮካድ» እና በኮንጎ ዴሞክራሲ ለማስፈን የሚጥረው ቡድን፣ በምህፃሩ «አይዲሲ» ግን ራሳቸውን ከመጋቢቱ ምርጫ እንደማያርቁ ፣ በዚህ ፈንታ፣ አንዳንድ ቅድመ ግዴታዎች እስከተሟሉ ድረስ፣ ለምርጫው ዘመቻ እስከ ሳምንቱ ማብቂያ ድረስ ኃይላቸውን በጋራ ለማስተባብሩ መወሰናቸውን የ«ፍሮካድ» ቃል አቀባይ ጊሮሜ ኪፉሲያን አስታውቀዋል።
« ነፃ አስመራጭ ኮሚስዮን ሊኖር ይገባል። የመራጩ ስም ምዝገባም በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ መሆን ይኖርበታል። በወቅቱ ይህን ማድረግ የሚቻል ይመስለኛል። እና ይህ እስከተሟላ ድረስ መሳተፉ አይከብድም። »
የተቃዋሚ ወገኖች ያቀረቡትን ጥያቄ ገዢው የኮንጎ የስራ ፓርቲ መልስ ያገኙ መሆናቸውን የገዢ ፓርቲ ዋና ጸሐፊ ፒየር ንጉሎ ገልጸዋል።
« በወቅቱ ያለው የሀገሪቱ አስመራጭ ኮሚሽን ገለልተኛ ነው። የተቃዋሚው ወገኖች ያነሱዋቸው ሌሎቹም ጥያቄዎች ቢሆኑ መልስ ያገኙ ናቸው። ስለዚህ የሚያነሱዋቸው ጥያቄዎች ሁሉ በምርጫው ስርዓት ሂደት እና ተዓማኒነት ላይ ጥርጣሬ ለመፍጠር የታሰበ ብቻ ነው። »
የምርጫው ጊዜው በመቃረቡ የተቃዋሚ ቡድኖች እጩዎቻቸውን ባፋጣኝ ማቅረብ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ በቂ ጊዜ ባለማግኘታቸው ቅሬታቸውን ከወዲሁ እያሰሙ ነው። በርግጥም፣ ለምርጫው በቂ የዝግጅት ጊዜ ማግኘት መቻላቸው በሀገሪቱን ሕዝብ ማነጋገር ይዞዋል። ትልቁ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ህብረት አንድ ወይም በርካታ እጩዎችን ማቅረብ አለማቅረቡ ገና በግልጽ አልታወቀም። ይሁንና፣ በጋራ አንድ እጩ ሊያቀርቡ ይችሉ ይሆናል በሚል በሕዝብ ዘንድ ያደረውን ተስፋ ለማህበራዊ ዴሞክራሲ የተቋቋመው ቡድን ፕሬዚደንት እና የ«ፍሮካድ» ዋና አስተባባሪ ፓስካል ቲያቲ ማቢያላ ሁለቱ ቡድኖች ለጊዜው ተስፋ ብቻ መሆኑን አመልክተዋል።
«በአፍሪቃ አንድ እጩ ብቻ ይዞ ለመቅረብ የተስማማ አንድም የተቃዋሚ ፓርቲ አላውቅም። እንደ ጋቦ፣ እንደ ቶጎ ፣ እንደ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ አንድ ብቻ ይዘን አንቀርብም። አንድ እጩ ብቻ ወይም ብዙ እጩዎች ይዞ መቅረቡ ያዋጣል አያዋጣም የሚለውን ጉዳይ እየመረመርን ነው። በዚህ ጥያቄ ላይ ሂደቶችን አስፍተን ለማየት ነው የምንሞክረው። እና የትኛውን መስመር እንደምንከተል አሁን ልነግርህ አልችልም። »

በ« ፍሮካድ» ውስጥ የሚጠቃለሉት አምስት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ባለፈው ጥቅምት ፣ 2015 ዓም የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት በማሻሻል የፕሬዚደንት ዴኒ ሳሱ ንጌሶን የስልጣን ዘመን ለማራዘም የቀረበውን ሕዝበ ውሳኔ ለማከላከል ከፍተኛ ጥረት አድርገው ሳይሳካላቸው መቅረቱ የሚታወስ ነው። ብዙዎቹ የኮንጎ ዴሞክራሲ ለማስፈን የሚጥረው ቡድን፣ በምህፃሩ «አይዲሲ» አባላት በብዛት የፕሬዚደንት ንጌሶ ፓርቲ አባላት የነበሩ ሲሆኑ፣ ሕዝበ ውሳኔውን በጥብቅ ተቃውመውታል።
የተቋቋሚ ኮሚቴ ወይም በምህጻሩ «ክራክ» በሚል መጠሪያ የሚታወቅ የተቃዋሚ ፓርቲ ያቋቋሙት ሮመ ቤዴል ሱሳ ራሳቸውን ከ«ፍሮካድ» በማራቅ፣ ባለፈው ታህሳስ ወር ራሳቸውን ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ እጩ አድርገው አቅርበዋል። ሱሳ አምስት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስለተጠቃለሉበት «ፍሮካድ» ያን ያህል ቀና አመለካከት እንደሌላቸው በግልጽ ነው የሚናገሩት።
« በሀገሪቱ እጎአ ከ1997 ዓም ወዲህ አምባገነን አገዛዝ ነው ነው ያለው። በዚህ ዓይነት ስርዓት ውስጥ የተቃውሞ ቡድኖች እንቅስቃሴ አለ ለማለት አይቻልም። »
ሱሳ በምርጫ ቢያሸንፉ በኮንጎ ብራዛቪል እርቀ ሰላም ለማውረድ እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።
« የኮንጎ ተወላጆች እርስ በርስ አይስማሙም። በሀገሪቱ ክፍፍል እና ጎሰኝነት ተስፋፍቷል። በደቡቡ የሀገሪቱ ከፊል የሚኖሩት ሰዎች በሰሜኑ ካሉት ጋር አይግባቡም። እና ይህ በሀገሪቱ ልማት ላይ ስጋት ደቅኖዋል። »
እንደሚታወሰው፣ በ1990ኛዎቹ ዓመታት በቀድሞው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እጩዎች ፓስካል ሊሱባ እና ዴኒ ሳሱ ንጌሶ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ሀገሪቱን ከፋፍሏታል። የኮንጎ ተወላጆችን ችግር እና ፍላጎት በሚገባ እንደሚያውቁ የገለጹት ሱሳ በምርጫ ፕሮግራማቸው ውስጥ ለጤና፣ ለትምህርቱ እና ለመሰረተ ልማቱ ማሻሻል ተግባር ቅድሚያ ሰጥተዋል።
ይሁን እንጂ፣ የ71 ዓመቱን ዴኒ ሳሱ ንጌሶን ከፕሬዚደንቱ መንበር ማውረዱ አዳጋች እንደሚሆን አላጡትም። የሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ ሬፈረንደም 90% የመራጩን ድምፅ አግኝቶ ነው ያለፈው፣ ምንም እንኳን ዓለም አቀፍ ወቀሳ ቢፈራረቅበትም። ሕዝበ ውሳኔው በተካሄደበት ሰሞን በታየው ተቃውሞ ወቅት በተፈ,ጠረ ግጭት፣ ቢያንስ አራት ሰዎች ሲሞቱ፣ በርካታ የተቃዋሚ ቡድኖች ፖለቲከኞች በቁም እስር ውለዋል። ሳሱ ንጌሶ ኮንጎ ብራዛቪልን እጎአ ከ1979 ዓም ወዲህ፣ ብሎም ካለፉት 31 ዓመታት ወዲህ በመምራት ላይ ይገኛሉ።
ስርዓተ ዴሞክራሲን እከተላለሁ የሚለው የኮንጎ ብራዛቪል መንግሥት ባለስልጣን አላ ሞካ እንዳስታወቁት፣ ወሳኙ መራጩ ሕዝብ እንደመሆኑ መጠን፣ ሕዝቡ ከፈለገ በፕሬዚደንታዊው ምርጫ የስልጣን ለውጥ ሊኖር ይችላል።

Denis Sassou Nguesso Kongo Afrika Präsident
ምስል picture-alliance/dpa/A. Ammar

ኤሪክ ቶፖና/አርያም ተክሌ

ልደት አበበ